የህወሓት ጉባኤ ዳግም ጦር ያማዝዝ ይሁን?
ሰኞ፣ ሐምሌ 29 2016ህወሓት በተለያዩ ወቅቶች ያጋጠሙት ቀውሶች
በ1969 ሕወሐት ገና በለጋ ዕድሜው እንዳለ በውስጥ ቀውስ መታመሱ ትግሉን መሄድ በሚገባው አቅጣጫና ፍጥነት እንዳይሄድ እግር ከወርች ያሰረውን ገመድ ለመበጠስና በተሻለ ፖለቲካዊ ቁመና ለመሄድ እንደ አንድ መፍትሄ የወሰደው ሰፊውን የድርጅቱን አባላት በማወያየትና ሐሳብን በሐሳብ በማሸነፍ እንደነበር ነባር የድርጅቱ አባላት በተለያዩ ጊዜያት የከተቧቸው ድርሳናት ያመላክታሉ።
በ1977ም ድርጅቱ አጋጠሙት ከሚባሉ ቀውሶች ሌላኛው የሚጠቀስበት ዓመት ነበር። በወቅቱ የሚመራበት ርዕዮተዓለም እና ወታደራዊ እንቅስቃሴው አቅጣጭ ጠፍቶበት የዕውር ድንብሩን የተጓዘበት ሁኔታ መፈጠሩንም እንዲሁ ነባር የድርጅቱ አባላት ይገልጻሉ። በወቅቱ እነ ዶክተር አረጋዊ በርኸ እና ኢንጅነር ግደይ ዘርአጽዮን የተባሉ ከፍተኛ የድርጅቱ አባላት ከድርጅቱ እንዲሰናበቱበት ያደረገ ጉባኤ ተካሂዶ ድርጅቱ አሁንም ወደ ተሻለ መስመርና አቅጣጫ እንደገባ የድርጅቱ ድርሳናትና ነባር የድርጅቱ አባላት ይናገራሉ።
ሌላው ህወሓት ያጋጠመው ትልቅ ተብለው ከሚጠቀሱ ቀውሶች ደግሞ ከኢትዮ ኤርትራ ጦርነት በኋላ በ1993 ዓም የተከሰተው ነው። በዚህ ጊዜም የነበሩ ችግሮቼ ያላቸውን ገምግሞ እነ አቶ ገብሩ አስራት፣ አቶ ስዬ አብርሃን ጨምሮ በርካታ የድርጅቱ ከፍተኛና መካከለኛ አመራር አባላትንና ተራ አባላትን በማግለል ድርጅቱ እየተንገዳገደ አሁን ያለበት ደረጃ ደርሷል።
የሕወሓት ምርጫና መዘዙ
2012 በዓለማችን በነበረው የኮረና ተሐዋሲ ስርጭት ምክንያት የፌደራል መንግሥት ምርጫ ሲያራዝም በአንድ ሀገርና ሰንደቅ አላማ ሥር የሚገኘው ህወሓት ግን በክልሉ ምርጫ አካሂዳለሁ በማለት የራሱን ምርጫ ቦርድ አቋቁሞ ምርጫ በመካሄዱ የሚልዮኖችን ሕይወት የፈጀ፣ ያፈናቀለ፤ በቢልዮን ብር የሚገመት ንብረትን ያወደመ ጦርነት እንዲካሄድ ምክንያት እንደሆነ ተነግሯል።
የጉባኤ ዝግጅትና ውዝግቡ
ጦርነቱ የሚበላውን በልቶ የተረፉ መሪዎችን በማጨባበጥ ለጊዜው ቢቆምም አሁንም ህወሐት በምርጫ ቦርድ ሕጋዊ ዕውቅና ሳያገኝ ጉባኤውን አካሂዳለሁ ማለቱን እና በምርጫ ቦርድ እንደ አዲስ ፓርቲ እንዲመሰረት የቀረበለትን ጥያቄ ባለመቀበሉ በፓርቲው ውስጥና ከፌደራል መንግሥት ጋር ድሮውንም በቋፍ ላይ የነበረው ግኑኝነት ወደ ለየለት ጦርነት እንዳያመራ ብዙዎችን አስግቷል።
ሕወሓት በቅርቡ ባወጣው መግለጫ ድርጅቱ በ50 ዓመት ታሪኩ አጋጥሞት የማያውቅ ቀውስእንዳጋጠመው ገልጿል። የድርጅቱ የሕዝብ ግኑኝነት ሃላፊ አቶ አማኑኤል አሰፋ ለDW በሰጡት አስተያየት ፓርቲው ወራት በፈጀ ስብሰባ የውስጥ ችግሩን ፈትሾ፤ ሂስና ግለሂስ በማካሄድ አጠቃላይ ችግሩን ለመፍታት ጉባኤ ለማካሄድ መወሰኑን ገልጸዋል። ለዚህም ሦስት የቁጥጥር ኮሚሽን አባላት ያሉበት አዘጋጅ ኮሚቴ ተቋቁሞ የስብሰባው መሰናዶም ዴሞክራሲያዊና ትክክለኛነቱ ተገምግሞ የጉባኤ ዝግጅት መካሄዱን አክለዋል። ብቸኛ የድርጅቱ ችግሮች የመፍቻ ቁልፍ ጉባኤ ማካሄድ መሆኑን በማከል።
በዚህ ዝግጅት የትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደር የሕዝብ ግኑኝነት ሃላፊን አግኝተን ለማነጋገር ያደረግነው ተደጋጋሚ ጥረት ባይሳካም የድርጅቱ ምክትል ሊቀመንበርና የጊዚያዊ አስተዳደሩ ፕረዚደንት አቶ ጌታቸው ረዳ ግን ለክልሉ መገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ ተከታዩን ብለዋል።
«በውስጣችንም ቢሆን በተካሄደ ውይይት ጉባኤ አይካሄድ ያለ የለም። ሐሳብ የሚንሸራሸርበት ጉባኤ ይሁን፤ የተደረገውን ዝግጅት ደግሞ ምን ይመስላል ብለን እንየው። አንድ ነገር ግን እንዲህ ዓይነት ጉባኤ ሰው የማይድንበት፤ ወደ ቀውስ ያስገባን ሃይል ተመልሶ ወደ ሥልጣን እርካብ የሚቆናጠጥበት፤ ሌላውን የሚቀጠቅጥበት መድረክ ለመፍጠር ነው።“
የቀድሞው የድርጅቱ ነባር ከፍተኛ የአመራር አባልና የቀድሞው የትግራይ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ ገብሩ አስራት በቅርቡ በሰጡት መግለጫ ተከታዩን ብለው ነበር።
«የችግሩ መንስኤ ውስጣዊ እንጂ ውጫዊ አደለም። የቆየ ችግር አለ፤ ይህም የሥርዓት ችግር ነው። አመራሩ ማዕከሉን ጥቅምና ሥልጣን አድርጓል። በድርጅቱ ውስጥ በጉልህ የሚታይ ሁለት የድር መተሳሰር ተፈጥሯል። ይህ ነው ሁሉንም ነገር ያበላሸው።» ይላሉ አቶ ገብሩ አስራት።
በሕወሓት ውስጥ በድርጅቱ ጽሕፈት ቤት እና የጊዜያዊ አስተዳደሩ ቡድን ተቧድነው በድርጅቱ ሊቀመንበርና ምክትል ሊቀመንበር መካከል በማሕበራዊ መገናኛ ብዙኀን ሠራዊቶቻቸው ጭምር ከፍተኛ የሆነ የስም መጠፋፋትና ጥልልፍ እየተስተዋለ ይገኛል። ይህም የርዕዮተ ዓለም ልዩነት፣ የፖሊሲና የስትራተጂ ልዩነት ያመጣው ጤናማ የውስጥ ፖለቲካዊ ትግል ሳይሆን ለወንበር የሚደረግ የዝሆኖች ፍትግያ እንደሆነ የፖለቲካ ተንታኞች ይገልጻሉ። የሕወሓት ጽሕፈትቤት ሃላፊ አቶ አማኑኤል አሰፋ ግን ይህን አይቀበሉም።
የህወሓት የቁጥጥር ኮሚሽን ተቃውሞ
አቶ አማኑኤል የድርጅቱ ማዕከላይ ኮሚቴና ሰፊው አባላቱ የተሳተፉበት ዴሞክራሲያዊ የጉባኤ ዝግጅት መካሄዱን ቢገልጹም የድርጅቱ የቁጥጥር ኮሚሽን ግን አካሄዱ ዴሞክራሲያዊ አይደለም በማለት ሦስት አባላቱን ከዝግጅት ኮሚቴው እንደሳበ ገልጿል። የኮሚሽኑ ሊቀመንበር አቶ ተክለብርሃን አርአያ በቅርቡ ለክልሉ የመገናኛ ብዙሃን ከተናግሩት ይህ ይገኝበታል።
«ግልጽ የሆነ መርሐግብር ይቀመጥ ተብሎ ነበር። እስከ አሁን ግልጽ የሆነ መርሐ ግብር አልተቀመጠም። በጉባኤው ዝግጅት የወከልናቸው አባሎቻችን እየተቃጠሉም ቢሆን ሲታገሉ ቆይተዋል። እኛ የቁጥጥር ኮሚሽንም ይህ ነው የሚባል የዝግጅት መርሐ ግብር የለንም። መርሐ ግብሩን አምጡ እንላቸዋለን ነገ ከነገ ወድያ እያሉ ይጨቃጨቃሉ።»
ሕወሓትና የምርጫቦርድ ፍጥጫና የጠቅላይ ሚኒስትሩ ምላሽ
ሕወሓት ከምርጫ ቦርድ ሕጋዊ ዕውቅና ሳያገኝ ጉባኤ አካሂዳለሁ፤ እንደ አዲስ ተመዝገቡ የሚል የምርጫ ቦርድን ሀሳብ አልቀበልም ማለቱ በውስጥ ሽኩቻ ብቻ የሚያበቃ ቢሆን በቀላሉ የሚታለፋ ሊሆን ይችል ነበር የሚሉ የፖለቲካ ተንታኞች ወደፊት ከሚካሄደው ምርጫና መንግሥት የመሆን አካሄድ ጋር ተያይዞ ግን ከፌደራል መንግሥት ጋር የሚያጋጭ ሊሆን እንደሚችል ያክላሉ። የተሰጋውም አልቀረ፤ የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ በቅርቡ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር በነበራቸው የምክክር መድረክ ጉዳዩ ተነስቶ ተከታዩን ብለዋል።
«ከዚህ ቀደም ምርጫ ቦርድ ምርጫ አራዝማለሁ ሲል ብዙዎቻችን ስንስማማ TPLF አልስማም ብሎ የገባንበት ቀውስ ይታወሳል። ምን ያክል ሰው እንደወደመ ምን ያክል ሐብት እንደወደመ መገመት ትችላላችሁ። ያ የወደመ ሐብትና የወደመ የሰው ሕይወት በትክክል ሳይገመገም እንዴት ጠፋ ሳይባል ሌላ ጥፋት ማምጣት ጥሩ አደለም። ሕዝብ ይጎዳል። እኔ ብፈልግም ባልፈልግም ዋጋ የለውም። ምርጫ ቦርድ ካልተቀበለው TPLFን፤ ሕጋዊ ፓርቲ ካላለው ምርጫ ሊሳተፍ አይችልም፤ መንግሥት ሊሆን አይችልም። ምን ማለት ነው? ተመልሰን ደግሞ ጦርነት እንገባለን ማለት ነው።»
ይህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አባባል ብዙ ትችቶችን አስተናግዷል። አንድ ህወሐት የምርጫ ቦርድን ሕግ አላከበረም ተብሎ ወደ ጦርነት እንገባለን ማለት «አይጥ በበላ ዳዋ ተመታ» እንዲሉ በፓርቲው ጥፋት የትግራይ ሕዝብ ዳግም በጦርነት የሚጎዳበት ምክንያት አይኖርም በሚልም ብዙ ተቃዎሞ ደርሶታል። የሕወሐት የሕዝብ ግኑኝነት ሐላፊ አቶ አማኑኤል አሰፋም ይህን ይጋራሉ።
«አንድ ፓርቲ ችግሮቹን ለመፍታት አንድ አዳራሽ ውስጥ ገብቶ ስብሰባ ስላደረገ ጦርነት ሊታወጅበት አይችልም። ማለት ያደረገው እኮ ስብሰባ ነው። ዓመቱን ሙሉ ወራትን የወሰዱ ስብሰባዎችን እናደርግ ነበር። ምንም የተፈጠረ ነገር የለም። ጉባኤ ከዛ በላይ የሆነ ስብሰባ አይደለም። ከፍተኛ ሥልጣን ስላለው በድርጅቱ ላይ ድርጅቱ የሠራቸውን ሥራዎች የገመገማቸውን ውጤቶች የመጨረሻ ውሳኔ ለመስጠት የሚያስችል ስብሰባ ከመሆኑ በስተቀር ምንም ነገር የለውም ።
ሕጋዊ አይደለም ዕውቅና አንሰጠውም ከሆነ ደግሞ ጉዳዩ ከምርጫ ቦርድ ጋር የሚያልቅ ነው። በጣም ቴክኒካልና ሕጋዊ የሆነ የአድሚኒስትሬሽን ጉዳይ ነው የሚሆነው። በዚህ ደረጃ ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ ፓርቲ ስብሰባ ስላደረገ ወደ ጦርነት ይገባል የሚል ጭራሽ ሊታሰብ አይችልም።»
የተቃዋሚ ፓርቲዎች ስጋት
ሕወሓት በውስጡ እየተካሄደ ያለው ሽኩቻና ከፌደራል መንግሥት ጋር የፈጠረው አታካሮ ወደ ከፋ ደረጃ እንዳይደርስ ብዙዎች የክልሉ ነዋሪዎች ስጋታቸውን እየገለጹ ይገኛሉ። ይህ ያሰጋቸው ሦስት በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ይህንኑ በመግለጽ ከሰጡት መግለጫ ተከታዩን ይገኝበታል።
«ይህ ሃይል የትግራይ ሚድያ፣ ፖለቲካ፣ የጸጥታ መዋቅር፣ ኢኮኖሚ፣ ማኅበራዊ ኑሮ ሳይቀር የተቆጣጠረአፋኝ ሃይል ነው። ይህ ጸረ ሕዝብ ሃይል የራሱን ውስጣዊ መናጨት ወደ ሕዝቡ ለማስረግና በሕዝባችን አንድነት ስንጥቅ ለመፍጠር የሚሄደውን አካሄድ እንዳይበቃው በውስጥና በውጭ ያሉ ተጋጣሚዎቹ ላይ የሃይል ሚዛንን ለማግኘት ሲል ሕዝባችንን ጭዳ የሚያደርጉ የተለያዩ አደገኛ አካሄዶችን እየታዘብን ነው። ስለሆነም በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚኖር ትግራዋይ በአንድነት ወግድ ሊለው ይገባል።»
የተጠያቂነት ጉዳይ
በትግራይ የደረሱት የሰው ሕይወትና ንብረት ውድመት እንዲሁም አሁን ያሉት ሥር የሰደደ ሙስናና የመልካም አስተዳደር ችግሮች መፈታት ያልቻሉት ተጠያቂነት ባለመስፈኑ እንደሆነ የክልሉ ነዋሪዎች በተለያዩ መድረኮች በምሬት ሲገልጹ ተደምጠዋል። የሕወሓት ሊቀመንበር ዶክተር ደብረጺዮን ገብረሚካኤል በቅርቡ በሰጡት መግለጫም የተጠያቂነት ጉዳይ ከከፍተኛ አመራሩ ጀምሮ ፖለቲካዊና አስተዳደራዊ እርምጃ እንዲወሰድ የድርጅቱ ፍላጎት መሆኑን ገልጸዋል። ለዚህም ሲባል ኮሚቴ ተዋቅሮ ዋና ዋና አጥፊዎች የተባሉ መለየታቸውን በድርጅቱም ሆነ በጊዜያዊ አስተዳደሩ በኩል ቢገለጽም እስካሁን ተጠያቂነት አለመስፈኑ ግን ብዙዎችን አስቆጥቷል። ይህን አስመልክተን ላነሳንላቸው ጥያቄ አቶ አማኑኤል አሰፋ «ለሁሉም ፖለቲካዊና አስተዳደራዊ ችግሮቻችን መፍቻው ጉባኤ መካሄድ አለበት የምንለው ለዚሁ ነው» የሚል ምላሽ ሰጥተውናል። ጉባኤ ካልተካሄደ ተጠያቂነት አይሰፍንም እያሉ ነው? ለሚል ተከታይ ጥያቄያችንም፤ «የለም በድርጅቱ ውስጥ የጉድለቶቹ አተያይ የተለያየ መልክ ስላለው ጉባኤው ይዳኘን እያል ነው» ብለዋል።
«በጣም ጉባኤው አስፈላጊ የሆነው ችግሮቻችንን ለመፍታት እኛ አንድ አይደለንም ነው። ችግሮቻችንን የምናይበት መነጸር አንድ አይደለም። በአንድ ድርጅት ውስጥ ታቅፈን ይሄ ነው ችግሩ ለማለት ተቸግረናል። ስለዚህ ዝም ብለን እየተሳሳብን መኖር አለብን? እንዴት ይሆናል ? አይሆንም እኮ። የሚያስታርቀን አንድ አካል አለ፤ ሁላችንም ተጠሪ የሆንበት ጉባኤ የሚባል አካል አለ። ስለዚህ ማን እንደተሳሳተና ማን ትክክል እንደሆነ ይነግረናል።»
በትግራይ ለተፈጸሙ ችግሮችና ላስከተሉት ጉዳት ተጠያቂነትን በተመለከተ በድርጅቱም ሆነ በጊዜያዊ አስተዳደሩ ልዩነት ያለ አይመስልም። እስካሁን ባለው ሂደት ግን አንዱ ሌላኛውን ከመውቀስና ችግሮችን ከመዘርዘር የዘለለ ጠብ የሚል ተጠያቂነት አልሰፈነም። በቅርቡ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ባዘጋጀው የውይይት መድረክ የሣልሳይ ወያነ ሊቀመንበር አቶ አሉላ ሃይሉ፤ አሉ የተባሉ ችግሮችን የሚዘረዝሩት ባለሥልጣናቱ መሆናቸውን በማመልከት፤ ሥልጣን የያዙ ሰዎች ሐላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።
«እኔን በጣም የሚያሳዝነኝ ነገር አለ። በትግራይ ችግሮች ተዘርዝረው እየተነገሩ ያሉት ችግሮቹን እንዲፈቱ ሥልጣን በያዙ ሰዎች ነው። ሐላፊነታችሁን ልትወጡ ይገባል “
ሕወሓት በውስጡና ከፌደራል መንግሥት ጋር የገባውን እሰጥ አገባ እንደተባለው ተጠያቂነትን በሚያስከትል መልኩ ጉባኤ በማካሄድ ይፈታ ይሁን? ወይስ በተቃራኒ ይጓዝ ይሆን? ጊዜ የሚፈታው ይሆናል።
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር
ሽዋዬ ለገሰ