የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር እና የህወሃት ውዝግብ
ረቡዕ፣ ሐምሌ 24 2016የህወሓት ምክትል ሊቀመንበር እና የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት አቶ ጌታቸው ረዳ ወቅታዊ ጉዳዮችን አስመልክተው ለድምፅ ወያነ ትግራይ የሰጡት ቃለመጠይቅ፥ በህወሓት ውስጥ ያለው ክፍፍል አጉልቶ ያሳየ ተደርጎ በበርካቶች እየተጠቀሰ ይገኛል። አቶ ጌታቸው በንግግራቸው የህወሓት ከፍተኛ አመራሮችን የጊዜያዊ አስተዳደሩን ሥራዎች ሆን ብሎ በማደናቀፍ እና በማጥላላት ላይ መሰማራታቸውን የገለፁ ሲሆን፥ በየደረጃው ያሉ አመራሮች እና የአስተዳደር መዋቅርም በሕገወጥ የማዕድናት ዝርፍያ፣ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር፣ የመሬት ወረራ፣ የጦር መሳርያዎች ሽያጭ እና ሌሎች ወንጀሎች ተሳትፎ እንዳለው አንስተዋል። አቶ ጌታቸው ህወሓት በየጊዜው የሚያካሂዳቸው ረዣዥም ስብሰባዎች የትግራይ ወቅታዊ ሁኔታን ገምግሞ የመፍትሔ አቅጣጫ የሚያስቀምጡ ሳይሆኑ የሥልጣን ሽኩቻ መድረኮች መሆናቸውን አጋልጠዋል።
አቶ ጌታቸው «የተደረጉ ስብሰባዎች፣ አንዴ 60 ቀን ተከታታይ ትሰበሰባለህ፥ ይሁንና አንድም ቀን ቢሆን ስለትግራይ ሕዝብ ወሳኝ አጀንዳ ተነጋግረን አናውቅም። ሁሌም የሥልጣን ሽኩቻ ነው። ማን ለምን ወደዚህ ሥልጣን ወጣ፣ በዚህ አጋጣሚ ማን ይውረድ የሚል ብቻ ነው» ብለዋል።
በተለይም በቅርቡ አወዛጋቢ ከሆነው የህወሓት ጉባኤመካሄድ እና ማዘግየት በሚል አጀንዳ ዙርያ ሐሳባቸው የሰነዘሩት አቶ ጌታቸው ረዳ፥ የህወሓት ጉባኤ አሁን ላይ ለማድረግ የተፈለገው የተወሰነ የፓርቲውን ክፍል ቆርጦ ለማስወገድ እና የአንድ የፓርቲው ኔትዎርክ አሸናፊነትን ለማረጋገጥ ነው ብለዋል።
በሌላ በኩል በትግራይ የሚንቀሳቀሱ ሦስት ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ በሰጡት መግለጫ ህወሓት የውስጥ ሽኩቻውን ወደ ሕዝብ ለማስገባት እየሠራ ነው በማለት የወቀሱ ሲሆን፥ በህወሓት አመራሮች መካከል ባለው ሽኩቻ ሕዝብ ይሁን በትግራይ ያሉ ታጣቂ ኃይሎች ከውግንና ራሳቸው እንዲያረቁ ባይቶና፣ ሳልሳይ ወያነ ትግራይ እና የትግራይ ነፃነት ፓርቲ በጋራ በሰጡት መግለጫ ጥሪ አቀርበዋል። የሳልሳይ ወያነ ትግራይ ሊቀመንበር አቶ አሉላ ሐይሉ «እየታየ ያለው የሥልጣን ውድድር ነው። በዋነኝነት በትግራይ አንድነት ላይም አደጋ የሚፈጥር ነው። ሁሉም ከእነዚህ ኃይሎች ጋር የሚያደርገውን ውግንና ማቆም አለበት። ሁሉም መሰለፍ ያለበት ለሕዝብ ጥቅም፣ አንድነት ወንድማማችነት ነው» ሲሉ ገልፀዋል።
የትግራይ ነፃነት ፓርቲ ሊቀመንበር ዶክተር ደጀን መዝገበ በበኩላቸው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስቴር ህወሓትን አስመልክተው ሲናገሩ ከትግራይ ሕዝብ ያገናኙትን አስተያየት ኮንነዋል።
ዶክተር ደጀን «የኢትዮጵያ መንግሥት ትግራይን በሚመለከቱ ጉዳዮች ግንኙነቱን ከህወሓት ብቻ አድርጎ ሲያበቃ፣ በመካከላቸው ግጭት ሲፈጠር ግን የትግራይ ሕዝብ ዋጋ ይከፍላል እያሉ ማስፈራራት፣ ተቀባይነት የሌላው እና ሀላፊነት የጎደለው፣ ፖለቲካ ፓርቲ እና ሕዝብን አንድ ያደረገ ትርክት በአፋጣኝ እንዲታረም ጥሪ እናቀርባለን» ብለዋል።
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስቴር አብይ አሕመድ ህወሓት በምርጫ ቦርድ ሕጋዊ እውቅና ሳያገኝ ወደ ጉባኤ የሚገባ ከሆነ ወደ ዳግም ጦርነት ሊመራ ይችላል ማለታቸው ይታወሳል። የህወሓቱ ሊቀመንበር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል በበኩላቸው ይህን አስተያየት በተመለከተ ከጠቅላይ ሚኒስቴሩ ጋር መነጋገራቸው እና ተገቢ አስተያየት አለመሆኑ እንደገለፁላቸው ከቀናት በፊት ሰጥተውት በነበረ መግለጫ አመልክተዋል።
ሚሊየን ኃይለ ሥላሴ
ሸዋዬ ለገሠ
አዜብ ታደሰ