ህወሓት «በልዩ ሁኔታ» በፓርቲነት እንዲመዘገብ ፍትሕ ሚኒስቴር ጠየቀ
ዓርብ፣ ሰኔ 21 2016ህወሓት "በልዩ ሁኔታ" በፓርቲነት እንዲመዘገብ ፍትሕ ሚኒስቴር ጠየቀ
ህዝባዊ ወያነ ርነት ትግራይ (ህወሓት) "ኃይልን መሠረት ያደረገ የአመጽ ተግባሩን በማቆም፤ ሕገ መንግሥታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን አክብሮ ለመንቀሳቀስ የተስማማ በመሆኑ በልዩ ሁኔታ" መመዝገብ እንዲችል ፍትሕ ሚኒስቴር ብሔራዊ ምርጫ ቦርድን ጠየቀ። በፍትሕ ሚኒስትሩ ጌድዮን ጢሞትዮስ ፊርማ ሰኔ 17 ቀን 2016 ዓ.ም ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተጻፈው ደብዳቤ "በልዩ ሁኔታ የፖለቲካ ፓርቲ ምዝገባን ይመለከታል" የሚል ርእስ የተሰጠው ሲሆን ደብዳቤው ለቦርዱ መድረሱን ከተቋሙ ለማረጋገጥ ችለናል። ፍትሕ ሚኒስቴር ጥያቄውን ያቀረበው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ግንቦት 27 ቀን 2016 ዓ.ም ባካሄደው መደበኛ ጉባኤው አሻሽሎ ያፀደቀውን የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና ሥነ ምግባር አዋጅን መሠረት አድርጎ ስለመሆኑ ለምርጫ ቦርድ በተፃፈው ደብዳቤ ተጠቅሷል።
የደብዳቤው ይዘት ምን ይላል ?
ዶቼ ቬለ የተመለከተው የፍትሕ ሚንስትሩ ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የፃፉት ደብዳቤ፣ ለኢ.ፌ.ዴ.ሪ የሰላም ሚኒስቴር፣ ለብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት አዲስ አበባ፤ እንዲሁም ለትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር መቐለ ግልባጭ ተደርጎ የተጻፈ ነው። ደብዳቤው "ሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ኃይልን መሠረት ያደረገ የዐመጽ ተግባር ውስጥ በመሳተፉ ምክንያት ጥር 10ቀን 2013 ዓ. ም የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ባሳለፈው ውሳኔ መሠረት የፓርቲው ሕጋዊ ሰውነት የተሰረዘ መሆኑ ይታወሳል" ሲል ይዘረዝርና ሆኖም ፓርቲው ኃይልን መሠረት ያደረገ የአመጽ ተግባሩን በማቆም ሕገ መንግሥታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን አክብሮ ለመንቀሳቀስ የተስማማ በመሆኑ፣ በኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና የምርጫ ሥነ ምግባር (ማሻሻያ) አዋጅ መሠረት በልዩ ሁኔታ እንደ ፖለቲካ ፓርቲ ለመመዝገብ እንዲችል በቦርዱ አስፈላጊው እንዲደረግ እንጠይቃለን" ይላል።
ይህ በደብዳቤ ቁጥር 1/1345 የተጻፈው ደብዳቤ ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መድረሱን ከቦርዱ የሕዝብ ግንኙነት ክፍል ለማረጋገጥ ችለናል። ደብዳቤው በቅድሚያ በቦርዱ የፓርቲዎች ጉዳይ ክፍል፣ ቀጥሎም በሕግ ክፍሉ ከታየ በኋላ ምርጫ ቦርድ አስተያየት እንደሚሰጥበትም ያገኘነው ምላሽ ያመለክታል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ግንቦት 27 ቀን 2016 ዓ.ም ባካሄደው መደበኛ ጉባኤውን ከታደሙ 239 አባላት መካከል በሁለት ተቃውሞ እና በአንድ ድምጽ ተዓቅቦ በአብላጫ ድምጽ ተሻሽሎ የፀደቀው የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና ሥነ ምግባር አዋጅ፤ "ኃይልን መሠረት ያደረገ የአመጽ ተግባር ውስጥ የተሳተፈ" ነገር ግን ይህንን ተግባር ማቆሙንና በሰላም ለመንቀሳቀስ መስማማቱን የገለፀ የፖለቲካ ቡድን ከሚመለከተው የመንግሥት ተቋም የሚሰጠውን ማረጋገጫ መነሻ በማድረግ "በልዩ ሁኔታ እንደ ፖለቲካ ፓርቲ" እንዲመዘገብ እድል ይሰጣል። ይህንን በተመለከተ ባለፈው ቅዳሜ በድጋሚ ምርጫ ዙሪያ መግለጫ ሲሰጡ ከጋዜጠኞች ጥያቄ የቀረበላቸው የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ "እየተመለከትነው ነው" የሚል አጭር ምላሽ ሰጥተው ነበር።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በጉዳዩ ላይ አድርጎት የነበረው ውይይት
ህወሓት ዳግም ሕጋዊ ሰውነት ያለው የፖለቲካ ድርጅት ሆኖ እንዲመዘገብ ሁኔታ እያመቻቸለት ያለው የተሻሻለው የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና ሥነ ምግባር አዋጅ፤ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ይሁንታ ቢያገኝም አንድ የምክር ቤት አባል ግን ማሻሻያው "ህወሓትን ወደ ሕጋዊ መስመር ለመመለስ ያለመ" መሆኑን በመጥቀስ እና ድርጅቱ አሁንም በአማራ እና አፋር ክልሎች ችግር እየፈጠረ መሆኑንም በመጥቀስ ማሻሻያውን በብርቱ ተቃውመውት ነበር።
በወቅቱ የአዋጁ የማሻሻያ ሀሳብ አስፈላጊነት ላይ ማብራሪያ የሰጡትና አሁን ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሕወሓት በፓርቲነት እንዲመዘገብ ደብዳቤ የፃፉት የፍትሕ ሚኒስትሩ ጌድዮን ጢሞትዮስ፣ አዋጁ "ወደ ሕጋዊ ሰላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ይመለሳሉ ብለን ተስፋ እያደረግን ላለነው ፓርቲዎች እንዲሁም በሌሎች ግጭት በሚስተዋልባቸው ክልሎች እየተንቀሳቀሱ ያሉ ቡድኖች፣ ድርጅቶችም ወደ ሀገራዊ ምክክር መድረኩ ለመምጣት ቢፈልጉ ለሁሉም መንገድ እንዲከፍት ተደርጎ የተዘጋጀ ነው" ብለው ነበር።
በተሻሻለው አዋጅ ምርጫ ቦርድ የምዝገባ ጥያቄው በቀረበለት በ15 ቀናት ውስጥ የመፈፀም ግዴታ አለበት
በተሻሻለው አዋጅ "እንደ ፖለቲካ ፓርቲ ለመመዝገብ የሚያመለክት ቡድን በሰላማዊ እና ሕጋዊ አግባብ ለመንቀሳቀስ መስማማቱን ከሚመለከተው የመንግሥት ተቋም የሚሰጠውን ማረጋገጫ" መነሻ በማድረግ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ማመልከቻው በቀረበ በ15 ቀናት ውስጥ ምዝገባ ይፈጽማል ይላል። ይህም ማለት በፍትሕ ሚኒስትሩ ጌድዮን ጢሞትዮስ ፊርማ ሰኔ 17 ቀን 2016 ዓ.ም ሕወሓት በልዩ ሁኔታ የፖለቲካ ፓርቲ ሆኖ እንዲመዘገብ በደብዳቤ ማመልከቻው ወይም ማረጋገጫው የደረሰው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በሁለት ሳምንታት ውስጥ ለሕወሓት ሕጋዊ የፖለቲካ ድርጅት እውቅና የመስጠት ግዴታ ይኖርበታል ማለት ነው።
ሰለሞን ሙጬ
አዜብ ታደሰ
ነጋሽ መሐመድ