1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሕወሓት በ50 ዓመት ታሪኩ አጋጥሞት በማያውቅ ፈተና ውስጥ እንዳለ ዐሳወቀ

ረቡዕ፣ ሐምሌ 10 2016

በዓመቱ ውስጥ ተደጋጋሚ እና ረዥም ስብሰባዎችን በማድረግ ያሳለፈው ሕወሓት በትናንቱ መግለጫውም ወደ ሌላ ስብሰባ ወይም ጉባኤ ለማምራት ዝግጅት ላይ መሆን ዐሳውቋል ። በተያዘው ሐምሌ ወርም 14ኛው መደበኛ ጉባኤው ለማድረግ ውሳኔ ማስተላለፉንም ይፋ አድርጓል።

https://p.dw.com/p/4iQrv
Äthiopien | Flagge Tigray People’s Liberation Front (TPLF
ምስል Million Haileyessus/DW

የህወሐት የውስጥ ፖለቲካዊ ችግር

ህወሓት በ50 ዓመት ታሪኩ አጋጥሞት በማያውቅ ፈተና ውስጥ እንዳለ አስታወቀ። ህወሓት የከፍተኛ አመራሮቹ ስብሰባ ካጠናቀቀ በኃላ ትላንት ባሰራጨው መግለጫ ቡድናዊነት፣ ፀረ ዴሞክራሲ አመለካከቶች እና ህዝበኝነት ፈተናዎቹ  እንደሆኑ አመልክቷል። አስተያየት ሰጪዎች በበኩላቸው የህወሓት አመራሮች በክፍፍል ላይ መሆናቸው የሚያነሱ ሲሆን ይህም ለህዝቡ ተጨማሪ ችግር እንዳያስከትል ይሰጋሉ።

ከ 1,000 በላይ የህወሓት የተለያየ እርከን አመራሮች የተሳተፉበት እና ለ11 ቀናት "ብሄራዊ ህልውናችን ማረጋገጥ፣ ቀዳሚ ተግባራችን ነው" በሚል መሪ ሐሳብ ተደረገ ከተባለው ስብሰባ በኃላ፥ ትላንት መግለጫ ያወጣው ህወሓት ቡድናዊነት፣ ፀረ ዴሞክራሲ አመለካከቶች፣ ጎጠኝነት እና ህዝበኝነት ፈተናዎቹ ሆነው እንዳለ አመልክቷል። ህወሓት እንዳለው  በ50 ዓመት ታሪኩ እንደ የአሁኑ ዓይነት ፈተና ገጥሞት እንደማያውቅ የሚያምን ሲሆን እነዚህ ፈተናዎች ፓርቲው በሚገባው ደረጃ እንዳይንቀሳቀስ ያደረጉ እና ወደ መፍረስ አደጋም ሲመሩ የነበሩ መሆናቸው አውስቷል።

በህወሓት መግለጫ አሁን ላይ በፓርቲው ውስጥ እየተደረገ ያለው ትግል በኪራይ ሰብሳቢነት እና ልማታዊ ፖለቲካል ኢኮኖሚ መካከል ነው በማለት የሚያነሳ ሲሆን፥ ህወሓት ለማዳን ደግሞ  ትግል  እናደርጋለን ይላል። ከፌደራል መንግስቱ ጋር ሁለት ዓመት ለቆየ እና ለበርካቶች ሞት፣ ጉዳት፣ ስደት እና መፈናቀል ምክንያት በሆነ ጦርነት የቆየው፥ ቀጥሎም በፕሪቶሪያ በተደረሰ የሰላም ስምምነት ወደ ሰላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ የተመለሰው ህወሓት፥ በሰላም ስምምነቱ የእስካሁን አፈፃፀም  ጥሩ ጅማሮዎች ቢኖሩም የውሉ ይዘት በሙሉእነት በመተግበር፣ እንዲሁም በተያዘለት የግዜ ገደብ በመተግበር ረገድ ግን ክፍተት አለ ብሏል።

ዓመቱ በተደጋጋሚ ረዥም ስብሰባዎችን በማድረግ ያሳለፈው ህወሓት በትላንቱ መግለጫውም ወደ ሌላ ስብሰባ ወይም ጉባኤ ለማምራት ዝግጅት ላይ መሆኑ በተያዘው ሐምሌ ወርም 14ኛው መደበኛ ጉባኤው ለማድረግ ውሳኔ ማስተላለፉም አስታውቋል።

ህወሓት "14ተኛ ጉባኤያችን ለማካሄድ ምቹ ሁኔታ መፈጠሩ አረጋግጠናል። ስለዚህ የህወሓት ጉባኤ አዘጋጅ ኮሚቴ ከሚመለከተው አካል ጋር ተነጋግሮ በሐምሌ ወር 2016 ዓመተምህረት ውስጥ እንዲካሄድ ወስኖ በቅርቡ ይፋ እንዲያደርግ ጥሪ እናቀርባለን ። በዚህ ግዜ ጉባኤ እንዳይደረግ የሚያደርግ ምክንያት አለመኖሩ ተስማምተናል" ብሏል።

የህወሐት ጽህፈት ቤት
የህወሐት ጽህፈት ቤትምስል Million Hailesilassie/DW

በአደባባይ በሚታይ ግልፅ ፍጥጫ እና ክፍፍል እንዳለ በሚነገርለት ህወሓት፥ በወቅታዊ ሁኔታው፣ የውስጠ ፓርቲ ፍጥጫው እንዲሁም የትላንቱ መግለጫው ዙርያ ከተለያዩ አካላት የተለያየ አስተያየት እየተሰጠ ይገኛል። አስተያየታቸው ያጋሩን ፖለቲከኛው አቶ ሃፍታይ ገብረ ሩፋኤል በህወሓት ውስጥ እየታየ ያለው የቡድን ፍጥጫ፥ ህዝብን ለአደጋ የሚያጋልጥ ይሉታል።

ፖለቲከኛው አቶ ሃፍታይ ገብረሩፋኤል "ለስልጣን ሲባል ይህ ያክል ህዝብን ወደ አደጋ የሚመራ መፋጠጥ ውስጥ መግባታቸው የሚያሳዝን ነው። ይበልጥ አሳሳቢ የሚያደርገው ደግሞ እነዚህ ሰዎች ስልጣን ላይ ያሉ መሆናቸው እና እንደ የአሁን በፊቱ ህዝብን የሚጎዳ መዘዝ ሊያስከትል የሚችል መሆኑ ነው። ስለዚህ የትግራይ ህዝብ፣ ምሁራን፣ ልሂቃን ይሁን ዳያስፖራው የስልጣን ሽኩቻ የፈጠረው አደጋ በወቅቱ ሊገነዘቡ እና ይህ ለማስቆምም በጋራ ሊሰሩ ይገባል። በተለይም ደግሞ የትግራይ ጀነራሎች ከሆነ ፖለቲከኛ ይሁን የህወሓት ክንፍ ከመተባበር ተቆጥበው በህዝብ ድህንነት ብቻ ሊሰሩ ይገባል" ይላሉ።

ሌሎች አስተያየት ሰጪዎች በበኩላቸው የህወሓት መሪዎች፥ ከጦርነት መልስ የህዝብ ችግሮች ለመቅረፍ ከመስራት ይልቅ  ስልጣናቸው ለማስጠበቅ ባለመ የቡድን ግጭት ዓመቱ ሙሉ ማሳለፋቸው ይወቅሳሉ። በዚህ ጉዳይ ዙርያ ከህወሓት ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት የተደረገ ጥረት አልሰመረም።

ሚልዮን ኃይሥስላሴ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር
ታምራት ዲንሳ