«በትግራይ 1411 ሰዎች በረሃብ ሞተዋል» የትግራይ አስተዳደር
ሐሙስ፣ ነሐሴ 4 2015የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት ከተቋረጠ ወዲህ ባለው ግዜ ብቻ በትግራይ 1411 ሰዎች በረሃብ ምክንያት ሞተዋል ሲል የክልሉ አስተዳደር አስታወቀ። በእርዳታ የሚቀርብ ምግብ ላልተፈለገ ዓላማ ውሏል በሚል ምክንያት ከአምስት ወራት በፊት አለም አቀፍ ለጋሾች የምግብ እርዳታ አቅርቦት ለትግራይ ክልል ቀጥሎም ለመላዉ ሀገሪቱ ያቋረጡ ሲሆን ይህ እርምጃ ከፍተኛ ሰብአዊ ቀውስ መፍጠሩን የትግራይ ክልል አደጋ ስጋት ስራአመራር ኮሚሽን አስታውቋል።
ዕድሜ እና ድህነት የተጫናቸው የ82 ዓመት የዕድሜ ባለፀጋ አቶ ገብረእግዚአብሔር ገብሩ፥ በዓብይ ዓዲ ከተማ ጎዳና ከፕላስቲክ በተሰራች መጠለያ ከባዱ የክረምት ወቅት በችግር እያሳለፉ ያሉ አዛውንት ናቸው። ትግራይ፣ በረሐብ የሚሞተዉ ሰዉ ቁጥር እየጨመረ ነዉከጦርነቱ በፊት በነበረ ግዜ በትግራይ ምዕራባዊ ዞን ፀገዴ ወረዳ በነበረ ቦታቸው ማሳቸው እያረሱ፣ ከብት እና ንብ እያረቡ፣ መልካም ሕይወት ይኖሩ እንደነበረ ያጫወቱት አዛውንቱ አቶ ገብረእግዚአብሔር፥ በነበሩበት የተፈናቃይ መጠልያ ተቀምጠው የሚያገኙት ምግብ ስለሌለ ወደጎዳና ወጥተው ለመለመን መገደዳቸው ነግረውናል። "እንደምታዩት እህል የለኝም፣ የምበላው የለኝም። ስለምን ነው ያረፈድኩት። በለሊት ነው የወጣሁት፣ እየለመንኩኝ ከተማው ስዞር ነው ያረፈድኩት። እየው ፥ ይህ ዳቦ አገኘሁ። ለዛሬ ይህች እበላለሁ። ስድስት ወር እርዳታ የሚባል አልተሰጠንም። መንግስትም ረስቶናል። እናትቶች ህፃናት በረሃብ ምክንያት እየተሰቃዩ ነው" ይላሉ አዛውንቱ።
ከቤተሰባቸው መለየት የፈጠረው ጭንቀት፣ የዕለት ምግብ ማጣት የወለደው ብሶት የሚያሰቃያቸውን እኝህ አባት፥ በበሽታ የቆሰለ እግራቸው እየጎተቱ በየዕለቱ ለልመና የዓብይዓዲ ከተማ ጎዳናዎች ይዞራሉ። በትግራይ ይካሄድ የነበረው ጦርነት ከቆመ ወራት ቢያልፉም፥ ጦርነቱ የፈጠረው ማሕበራዊ ቀውስ ግን አሁንም በጉልህ ይታያል። እንደ ክልሉ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮምሽን መረጃ በትግራይ ከ6 ሚልዮን በላይ የሚሆን ህዝብ የምግብ እርዳታ ፈላጊ ነው። ለዚህ ከፍተኛ መጠን ያለው እርዳታ ፈላጊ ህዝብ፥ ሕይወት አድን ድጋፍ ያደርጉ የነበሩ ዓለምአቀፍ ለጋሾች የእርዳታ እህል ላልተፈለገ ዓላማ ውልሏል በሚል ምክንያት ካለፈው የካቲት ወር ጀምሮ የዕርዳታ አቅርቦት ማቋረጣቸው ተከትሎ ደግሞ ሰብአዊ ቀውሱ ይበልጥ መባባሱ ተገልጿል። በትግራይ አስተዳደር የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮምሽን እንደሚለው፥ ለጋሾች ለትግራይ የምግብ እርዳታ ካቆሙ ወዲህ በለው ግዜ ብቻ የ1411 ሰዎች ሕይወት በረሃብ ምክንያት ማለፉ አስታውቋል።
የትግራይ ክልል አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮምሽን ኮምሽነር ዶክተር ገብረሕይወት ገብረእግዚአብሔር "እስካሁን 1411 ሰዎች በረሃብ ምክንያት ሕይወታቸው እንዳለፈ፣ እነዚህ ሕይወታቸው ያለፈ ደግሞ ሽማግሌዎች፣ ሴቶች፣ ህፃናት መሆናቸው ፥ የምግብ እርዳታው ከቆመ በኃላ ከዞኖች፣ ወረዳዎች ሪፖርት ተደርጎልናል። ይህ የሟቾች ቁጥር ምዕራብ ትግራይ ዞን፣ የደቡብ ትግራይ ዞን 6 ወረዳዎች፣ የማእከላዊ ዞን 22 ወረዳዎች እንዲሁም የመቐለ 7 ክፍለከተሞች እንደማይጨምር የትግራይ ክልል አደጋ ስጋት አመራር ኮምሽነር ዶክተር ገብረሕይወት ገብረእግዚአብሔር ለዶቼቬለ ተናግረዋል።ትግራይ፤ የተቋረጠዉ የምግብ እርዳታ እንዲቀጠል ተጠየቀ ለተቸገሩ ዜጎች የሚቀርብ የምግብ እርዳታ ተዘርፏል በሚል ምክንያት ከአምስት ወራት በፊት በትግራይ ጨምሮ በአጠቃለይ በሀገሪቱ ለሚገኙ እርዳታ ፈላጊዎች ያቀርበው የነበረ የምግብ አቅርቦት ማቋረጡ የገለፀው የዓለም የምግብ ድርጅት ቀስበቀስ የምግብ እርዳታ ማቅረብ መጀመሩ በትላንትናው ዕለት የተዘገበ ቢሆንም እንደ የትግራይ ክልል አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮምሽን ገለፃ ግን የተጀመረው፥ ለረዥም ግዜ በትግራይ ተቋርጦ የነበረ የሴፍትኔት ፕሮግራም እንጂ የአስቸኳይ ሕይወት አድን ሰብአዊ እርዳታ አለመሆኑ ተገልጿል። ኮምሽነሩ ዶክተር ገብረሕይወት፥ ዓለምአቀፍ ለጋሾች እስካሁን በትግራይ ላሉ እርዳታ ፈላጊዎች ያቀረቡት እገዛ የለም ይላሉ።
"ይህ የተጀመረው 'food for work' ምግብ ለስራ የሴፍትኔት ፕሮግራም ነው። እንደሚታወቀው ከጦርነቱ በፊትም የነበረ፣ ከ700 ሺህ እስከ 1 ሚልዮን የሚጠጋ የትግራይ ህዝብ ይሳተፍበት የነበረ ፕሮግራም ነው። ለተቸገረ የሕብረተሰብ ክፍል ወይ ለተፈናቃይ የሚሆን የተጀመረ የምግብ እርዳታ ግን የለም። ሴፍቲኔት፥ ፕሮግራም እንጂ አስቸኳይ የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት አይደለም" የሚሉት ኮምሽነሩ "በመቐለ እና ሌሎች ወረዳዎች መጋዝን ያለ እርዳታ ግን ለህዝቡ እንዲሰራጭ የተሰጠ ፍቃድ የለም" ሲሉ አክለዋል።
በዚህ ጉዳይ ዙርያ በዓለም የምግብ ድርጅት (WFP) የመቐለ ማስተባበሪያ ፅሕፈት ቤት በአካል ተገኝተን እንዲሁም በአዲስአበባ ከሚገኙ የድርጅቱ ተወካዮች በስልክና ኢሜይል ምላሽ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ለግዜው አልተሳካም። ዓለም አቀፍ ለጋሾች ለትግራይ ርዳታቸዉን እንዲቀጥሉ ጥሪ ቀረበተዘርፏል በሚል ምክንያት ይሰጣቸው የነበረ ሰብአዊ እርዳታ እንደቆመ እንደሰሙ የነገሩን አሁን ላይ በልመና እየተዳደሩ ያሉ እርዳታ ፈላጊው አዛውንት አቶ ገብረእግዚአብሔር፥ የዘረፉት ተለይተው ለሕግ እንዲቀርቡ፣ በእነሱ ሰበብ ግን ሌላው መቀጣት እንደሌለበት ይናገራሉ። የትግራይ ክልል አስተዳደር ሰብአዊ እርዳታ ዘርፈዋል ያላቸው አካላት እየለየ ሕጋዊ እርምጃ እየወሰደ መሆኑ ይገልፃል።
ሚሊዮን ኃይለሥላሴ
ኂሩት መለሰ
እሸቴ በቀለ