1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ትግራይ፣በረሐብ የሚሞተዉ ሰዉ ቁጥር እየጨመረ ነዉ

ማክሰኞ፣ ሰኔ 27 2015

በጦርነቱ ምክንያት ከቀዬአቸው የተፈናቀሉ ዜጎች እንደሚሉት፥ ለመጨረሻ ግዜ የምግብ እርዳታ ያገኙት ከ4 ወር በፊት ነበር። ከምዕራብ ትግራይ ሑመራ ተፈናቅለው አሁን ላይ መቐለ የሚገኙት አቶ ገብሩ እምባየ "በየግዜው ችግራችሁ ምንድነው እያለ የሚጠይቀን እንጂ፥ መፍትሔ የሚሰጥ አካል አጥተናል" ይላሉ።

https://p.dw.com/p/4TPEW
Suspension of Food Aid in Tigray
ምስል Million Haileselassie/DW

ትግራይ፣የተቋረጠዉ የእርዳታ አቅርቦት ይቀጥላል የሚል ተስፋ አለ

   

ትግራይ ዉስጥ በረሐብ   የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መሆኑ የክልሉ አስተዳደር አስታወቀ። የትግራይ አደጋ መከላከል ኮምሽን እንዳለው፣ በተለይ ለጋሽ ድርጅቶች ይሰጡት የነበረዉን የምግብ ዕርዳታ  ከቋረጡ ወዲህ በሶስቱ የትግራይ ዞኖች ከ700 በላይ ሰዎች በረሃብ እና በተያያዥ ችግሮች ሞተዋል።ዶቼቬሌ ያነጋገራቸው በክልሉ ደቡብ ምስራቅ ዞን ሳምረ ወረዳ የምትገኝ አንዲት ገጠር መንደር የሚገኙ ነዋሪ፥ ከሰላም ስምምነቱ ወዲህ ባለው ግዜ ብቻ በመንደራቸው ስምንት ሰዎች በረሃብ እና ከረሃብ ጋር ተያያዥ በሆኑ ምክንያቶች መሞታቸው ጠቁመዋል። ወደ ትግራይ የተቋረጠው የምግብ እርዳታ አቅርቦት በአፋጣኝ እንዲቀጥልም ከተለያዩ አካላት ጥሪ ቀርቧል።

 

ከአምስት ሚልዮን በላይ ህዝብ እርዳታ ፈላጊ ሆኖባት ባለችው ትግራይ፥ ከረሃብ ጋር ተያያዥ በሆኑ ምክንያቶች የሚከሰት ሞት እየተበራከተ መሆኑ ይገለፃል። በተለይም ከቅርብ ግዜ ወዲህ የምግብ እርዳታ አቅርቦቱ መቋረጡ ተከትሎ በተፈናቃዮች መጠልያ የሚገኙ ዜጎች፣ አቅመ ደካማ ሽማግሌዎች እና ህፃናት እንዲሁም ሌሎች የማሕበረሰብ ክፍሎች የከፋ ችግር ላይ መሆናቸው ተነግሯል። በተለይም በትግራይ ገጠር አካባቢዎች ችግሩ በስፋት የሚታይ መሆኑ የሚገለፅ ሲሆን፣ ከገጠሮች በመሰደድ በመቐለ በልመና የተሰማሩ ህፃናት እና ሽማግሌዎችም እየተበራከቱ ይገኛሉ።

በክልሉ ደቡብ ምስራቅ ዞን ሳምረ ወረዳ ነዋሪ የሆኑት እና በወረዳው የምትገኝ ዓምዲወያነ የተባለች ጣብያ አስተዳዳሪ የሆኑት ያነጋገርናቸው አቶ አሸብር ተካ፥ በትንሿ መንደራቸው ከጦርነቱ ጅማሮ ወዲህ ባለው ግዜ 22 ሰዎች በረሃብ እና ተያያዥ ምክንያቶች መሞታቸው፥ ከእነዚህ መካከል 8ቱ በቅርቡ ማለትም የሰላም ስምምነት ከተደረሰ በኃላ ባለው ግዜ የሞቱ መሆናቸው ነግረውናል። አቶ አሸብር "በጣብያችን ችግር ላይ ያለ የሕብረተሰብ ክፍል በርካታ ነው። 22 ሰዎች በረሃብ ምክንያት አጥተናል። ከእነዚህ 14ቱ የሞቱት የሰላም ስምምነቱ ከመፈረሙ በፊት በነበረ ግዜ ነው። 8ቱ ግን ጦርነቱ ከቆመ በኃላ ባለው ነው" ያሉ ሲሆን፥ አሁን ላይ በመንደራቸው 621 ቤተሰብ መሪዎች አፋጣኝ የምግብ እርዳታ እንደሚፈልጉም ጠቁመዋል።

አቶ ገብረእግዚአብሔር አረጋዊ የትግራይ የአደጋ ዝግጁነት ኮሚሽን ባለስልጣን
አቶ ገብረእግዚአብሔር አረጋዊ የትግራይ የአደጋ ዝግጁነት ኮሚሽን ባለስልጣንምስል Million Haileselassie/DW

ሌላ "ተርበናል" የሚል ድምፅ የሚያሰሙ የማሕበረሰብ ክፍሎች ተፈናቅለው በየመጠልያው ያሉ ዜጎች ናቸው። በትምህርት ቤቶች፣ ግዚያዊ ካምፖች እንዲሁም በየመንገዱ ኑሮአቸው ያደረጉ በጦርነቱ ምክንያት ከቀዬአቸው የተፈናቀሉ ዜጎች እንደሚሉት፥ ለመጨረሻ ግዜ የምግብ እርዳታ ያገኙት ከ4 ወር በፊት ነበር። ከምዕራብ ትግራይ ሑመራ ተፈናቅለው አሁን ላይ መቐለ የሚገኙት አቶ ገብሩ እምባየ "በየግዜው ችግራችሁ ምንድነው እያለ የሚጠይቀን እንጂ፥ መፍትሔ የሚሰጥ አካል አጥተናል" ይላሉ።

 

በትግራይ አደጋ መከላከል ኮምሽን የአስቸኳይ ምላሽ ዳይሬክቶሬት፥ በተለይም ወደ ትግራይ የእርዳታ አቅርቦት ከተቋረጠ ወዲህ ባለ ግዜ በክልሉ በረሃብ እና ተያያዥ ምክንያቶች የሚሞቱ ዜጎች ቁጥር መበራከቱ ይገልፃል። ኮምሽኑ እንዳስታወቀው፣ በትግራይ 3 ዞኖች ከሚገኙ ወረዳዎች የተሰበሰበ መረጃ እንደሚያመለክተው የምግብ እርዳታ አቅርቦቱ ከተቋረጠ ወዲህ ከ700 በላይ ሰዎች በረሃብ እና ከረሃብ ጋር ተያያዥ በሆኑ ምክንያቶች መሞታቸው ማረጋገጡ ይገልፃል። በክልሉ አደጋ መከላከል ኮምሽን የአስቸኳይ ምላሽ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ገብረእግዚአብሔር አረጋዊ "ከዞን፣ ከወረዳ አስተዳደሮች፣ ከማሕበረሰቡ እንዲሁም ከተፈናቃዮች ከራሳቸው የመጣ መረጃ ስናየው ከ728 በላይ ወገኖች እንዳጣን፣ አሁንም እየቀጠለ መሆኑ ነው የሚያመለክተው" ሲሉ ለዶቼቬለ የገለፁ ሲሆን በተለይም ህፃናት እና አዛውንቶች፣ የቆየ በሽታ ያለባቸው ሰዎች ከረሃብ ጋር ተዳምሮ ለሕይወት ማጣት እየተጋለጡ መሆኑ ተናግረዋል።

 

የክልሉ አስተዳደር ለጋሾች ያቋረጡት ሰብአዊ ድጋፍ በሐምሌ ወር አጋማሽ ዳግም ሊጀምር እንደሚጠብቅ የሚገልፅ ሲሆን፥ ከውጭ ለጋሾች በተጨማሪ የኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት በትግራይ ያለው ሰብአዊ ቀውስ ለማቃለል ሊንቀሳቀስ ይገባል ብሏል።

ሚሊዮን ኃይለስላሴ

ነጋሽ መሐመድ

ኂሩት መለሰ