1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዓለም አቀፍ ለጋሾች ለትግራይ ርዳታቸዉን እንዲቀጥሉ ጥሪ ቀረበ

ዓርብ፣ ግንቦት 11 2015

በትግራይ የሚንቀሳቀሱ 72 ሲቪል ማሕበራት ዓለምአቀፍ ሰብአዊ እርዳታ ለጋሽ ድርጅቶች ለትግራይ ያቀርቡት የነበረዉን የምግብ እርዳታ እንዲጀምሩ ጥሪ አቀረቡ። ሲቪል ተቋማቱ በትግራይ እርዳታ ላይ የተፈፀመ ስርቆት ካለ እንዲጣራ እና ጥፋተኞች ለሕግ ሊቀርቡ ይገባል፤ ለትግራይ እርዳታ ያቆሙ ለጋሽ ተቋማትም ውሳንያቸውን ደግመው እንዲያጤኑ ጠይቀዋል።

https://p.dw.com/p/4RZcz
Tigray I Lastwagen des Internationalen Komitees vom Roten Kreuz (IKRK)
ምስል International Committee of the Red Cross/Handout/REUTERS

"የትግራይ ግዝያዊ አስተዳደር በሰብአዊ እርዳታ ላይ የሚፈፀም ሕገወጥ ተግባር ለመከላከል በትኩረት እየሰራ ነው።"

በትግራይ የሚንቀሳቀሱ 72 ሲቪል ማሕበራት ዓለምአቀፍ ሰብአዊ እርዳታ ለጋሽ ድርጅቶች ወደ ትግራይ ማቅረብ ያቋረጡት የምግብ እርዳታ ዳግም እንዲጀምሩ ጥሪ አቀረቡ። ሲቪል ተቋማቱ በትግራይ እርዳታ ላይ የተፈፀመ ስርቆት ካለ እንዲጣራ እና ጥፋተኞች ለሕግ ሊቀርቡ ይገባል ያሉ ሲሆን በአንፃሩ ለትግራይ እርዳታ ያቆሙ ለጋሽ ተቋማትም ውሳንያቸው ደግመው ያጢኑ ብለዋል። የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር በበኩሉ ተፈፀመ የተባለው የእርዳታ ዝርፍያ እና ሽያጭ እያጣራ መሆኑ የሚገልፅ ሲሆን የተቋረጠው የእርዳታ ምግብ አቅርቦት ግን በአፋጣኝ ሊቀጥል ይገባል ይላል።

በትግራይ ለሚገኙ ከ5 ሚልዮን በላይ እርዳታ ፈላጊ ህዝብ ይቀርብ የነበረው የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት ከወር በፊት ጀምሮ የቆሙ፣ ለተቸገሩ ዜጎች ሊደርስ ይገባው የነበረ የምግብ እገዛ በተደጋጋሚ በመዘረፉ እና ለገበያ በመቅረቡ መሆኑ ከለጋሽ ድርጅቶቹ በኩል ይገለፃል። ለትግራይ ከሚቀርበው ሰብአዊ እርዳታ ከፍተኛ መጠን የሚይዘው የምግብ አቅርቦት የሚሸፍኑት ዩኤስኤአይዲ እና የዓለም ምግብ ድርጅት፥ በትግራይ አለ ያሉት የእርዳታ ምግብ ሽያጭ እና ዘረፋ እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል። ለክልሉ የሚቀርብ የምግብ እርዳታ መቋረጡ በትግራይ ያለው ሰብአዊ ቀውስ ይበልጥ እንዳይባባስ በበርካቶች ዘንድ ስጋት ፈጥሯል።

Äthiopien Tigray Konflikt Symbolbild
ለትግራይ ርዳታዉ እንዲቀጥል ተጠየቀምስል Eduardo Soteras/AFP/Getty Images

በትግራይ የሚንቀሳቀሱ 72 ሲቪክ ማሕበራት እንዳሉት፥ በትግራይ ተፈፀመ የተባለው የሰብአዊ እርዳታ ዝርፍያ እንዲሁም መሸጥ ተግባራት ተጣርቶ አጥፊዎች ለሕግ ሊቀርቡ እንደሚገባ ያነሱ ሲሆን ይህ በሂደት ላይ እያለ ግን የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦቱ ሊቀጥል፣ ለተቸገሩ ወገኖች ሊደር እንደሚገባ ጠይቀዋል። በመቶ ሺዎች የሚቋጠሩ አባላት ያልዋቸው የሴቶች እና ወጣቶች አደረጃጀቶች ጨምሮ የሙያ፣ ግብረሰናይ እንዲሁም ሌሎች ነፃ ማሕበራት ያካተተው የትግራይ ሲቪክ ማሕበረሰብ ተቋማት ሕብረት እንዳለው፥ ጥፋተኞች ለሕግ ከማቅረብ ጎን ለጎን የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት እንዲቀጥል ዓለምአቀፉ ማሕበረሰብ እና ለጋሽ ተቋማት ገንቢ ሚናቸው መጫዎት አለባቸው ሲል ገልጿል። የትግራይ ሲቪክ ማሕበረሰብ ተቋማት ሕብረት ስራአስኪያጅ አቶ ያሬድ በርሃ ለዶቼቬለ እንዳሉት "ችግሩ መፈጠሩ ያስከፋል፣ መፍትሄው ግን እርዳታ ማቆም አይደለም። ያልተገቡ ተግባራት መጣራት አለባቸው። ነገር ግን ይህ መሆን ያለበት እርዳታ እየቀረበ ነው ምርመራው መከወን የሚገባው" ያሉ ሲሆን "ከዚህ አንፃር የለጋሽ ድርጅቶቹ ውሳኔ ህዝባችን ላይ ትልቅ ጉዳት የሚያደርስ ነው" ሲሉ አክለዋል።

የተቋረጠው የሰብአዊ እርዳታ እንዲቀጥል ከመጠየቅ በተጨማሪ የተፈፀሙ የማጭበርበር ተግባራት ለማጣራት እየሰራ መሆኑ የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ይገልፃል። በሰብአዊ እርዳታ ጉዳዮች ማብራሪያ የሰጡት በክልሉ አደጋ ስጋት መከላከል ኮምሽን የአስቸኳይ ምላሽ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ገብረእግዚአብሔር አረጋዊ ለትግራይ የተቋረጠው የምግብ እርዳታ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል። አቶ ገብረእግዚአብሔር "የትግራይ ግዝያዊ አስተዳደር በሰብአዊ እርዳታ ላይ የሚፈፀም ሕገወጥ ተግባር ለመከላከል በትኩረት እየሰራ ነው። ይህ ግምት ውስጥ በማስገባት፣ የሰው ሕይወት ማዳን ስራ ቅድሚያ ሊሰጠው ስለሚገባ፣ በአዲሱ የተደራሽነት አሰራር መሰረት፣ የቆመው እርዳታ ቶሎ ተለቆ መድረስ ለሚገባው እንዲደርስ ነው ጥሪ የምናቀርበው" ብለዋል።

ከዚህ በተጨማሪ የትግራይ ሲቪክ ማሕበረሰብ ተቋማት ሕብረት ሰብአዊ እርዳታ እንዳይጭበረበር ድጂታል አሰራሮች እንዲተገበሩ አማራጮች ሲያቀርብ መቆየቱ ያነሳ ሲሆን፣ የተሻሻሉ የስርጭት እና ቁጥጥር ስርዓት በመገንባት እንዲሁም ባለድርሻ አካላት በማሳተፍ ክፍተቶች መሙላት ይገባል ብሏል። የ72ቱ ሲቪል ተቋማት ሕብረት እንደሚለው የእርዳታ አቅርቦት ያቋረጡ ለጋሽ ተቋማት ውሳንያቸው ዳግም ሊያጤኑ ይገባል።

የክልሉ አስተዳደር እንዲሁም የዓለምአቀፍ ተቋማት ቁጥራዊ መረጃዎች እንደሚያሳዩት በትግራይ ከ5 ሚልዮን በላይ ህዝብ እርዳታ ፈላጊ ነው።

 

ሚሊዮን ኃይለሥላሴ

አዜብ ታደሰ

ኂሩት መለሰ