1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

መንግሥት በአማራ ክልል አለመረጋጋት ከስጋት ደረጃ ወርዷል ማለቱ

ዓርብ፣ ጥቅምት 23 2016

የአስቸኳይ ጊዜ መምሪያ ዕዝ ስለክልሉ አሁናዊ ይዞታ መገምገሙን አንስተው ትናንት ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን መግለጫ የሰጡት የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶ/ር ለገሰ ቱሉ፤ ለመፍረስ ተቃርቦ የነበረውን ክልል ከመፍረስ መታደግ ተችሏል ብለዋል፡፡

https://p.dw.com/p/4YNJH
የአባይ ድልድይ አማራ ክልል
የአባይ ድልድይ አማራ ክልል ምስል Seyoum Getu/DW

የመንግስት ዋና ትኩረት የህዝብን ጥያቄ መመለስ ላይ ሊሆን ይገባል

የአስቸኳይ ጊዜ መምሪያ ዕዝ ስለክልሉ አሁናዊ ይዞታ መገምገሙን አንስተው ትናንት ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን መግለጫ የሰጡት የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶ/ር ለገሰ ቱሉ፤ ለመፍረስ ተቃርቦ የነበረውን ክልል ከመፍረስ መታደግ ተችሏል ብለዋል፡፡ አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡ የክልሉ ነዋሪዎች እና የፖለቲካ ተንታኝ ግን የክልሉን ዘለቄታዊ ሰላም ለማረጋገጥ ህዝብን ላስኮረፈው ነገር ምላሽ መስጠት ተገቢ ነው ይላሉ፡፡

አማራ ክልል ውስጥ ላለፉት ጥቂት ወራት በተከሰተው የለየለት አለመረጋጋት መንግስት ቢያንስ ለስድስት ወራት የሚቆይ ያለውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማወጅ የተለያዩ ወታደራዊ እርምጃዎችን በክልሉ ሲወስድ መቆየቱ ይታወቃል፡፡ ወደ ክልሉ መግባትና ከክልሉ መውጣትን ፈተና ውስጥ የከተተው የተፈጠረው የጸጥታ ችግሩ በክልሉ የማጓጓዣ አገልግሎትን ጨምሮ የተለያዩ መገልገያዎችን ፈትኗልም፡፡በአማራ ክልል ግጭት የተኩስ አቁም ጥሪ በአፍሪቃ ኅብረት

ነዋሪነታቸውን በአማራ ክልል የደብረማርቆስ ከተማ ያደረጉና ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁን አንድ አስተያየት ሰጪ ክልሉን ለዚህ አለመረጋጋት አብቅቷል ስላሉት ምክኒያት ሲያስረዱ፤ “ለረጂም ጊዜ የቆየ የመገፋት ስሜት ነው ህዝቡ ላይ አለ ብዬ የማስበው፡፡ ተበድያለሁ ተገልያለሁ የሚል ስሜት ህዝቡ ላይ ይነበባል፡፡ እነዚህን ቅሬታዎች ህዝቡ በሰልፍ እና በተለያዩ መንገዶች ሲገልጽ ቆይቶ በዚያ አልመለስለት ስላለው ነው ጠመንጃ ወዳነገበ ትግል ገብቷል ብዬ የማስበው” ብለዋል፡፡

በክልሉ የታጠቁ የፋኖ አካላትና የመንግስት ጸጥታ ኃይሎች ከቅርብ ወራት ወዲህ በተለይም ከሚያዚያ 2015 ዓ.ም. የክልሉ የልዩ ኃይል አባላት መልሶ ማደራጀትን ተከትሎ በገጠመው ተቃውሞ ወደ ለየለት ግጭት በመገባቱ የክልሉ መንግስት ጸጥታውን ለማረጋጋት ከአቅሜ በላይ ነው በሚል ለፌዴራል መንግስት ጥያቄ ማቅረቡም ይታወሳል፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ ትናንት የመንግሰት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶ/ር ለገሰ ቱሉ የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ ወደ ተረጋጋ አውድ መመለሱን የሚያወሳ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡  ሚኒስትሩ በመግለጫቸው ሊፈርስ የነበረውን ክልል መታደግ ተችሏልም ብለው ነበር፡፡ “አጠቃላይ የአማራ ክልል አሁናዊ ሁኔታን የአስቸኳ ጊዜ አዋጅ መምሪያ ዕዝ ሲገመግም ሊፈርስ የነበረው ክልል ከመፍረስ መታደግ መቻሉ ተረጋግጧል፡፡ አብዛኛው የክልሉ አከባቢዎች ወደ ሰላማዊ ሁኔታ ተመልሰዋል፡፡ ህዝቡ ከጸጥታ ሃይሎች ጋር ያለው ቁርኚት በእጅጉ ጨምሯል፡፡ ቀደም ሲል በተወናበደ መረጃ መከላከያን አታምጡብን ሲል የነበረው ኢሰመኮ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በአማራ ክልል ብቻ እንዲወሰን ለመንግስት ጥሪ አቀረበህዝብ አሁን መከላከያን አታውጡብን በማለት ለጸጥታ ሃይሉ የሚሰጠው የመረጃ ትብብርም በእጅጉ ጨምሯል፡፡ ክልሉን በብቁ አመራሮች የማደራጀት ስራም ተከናውኗል፡፡”

ፋኖ ላሊበላ አብያተ ክርስትያናት
ፋኖ ላሊበላ አብያተ ክርስትያናት ምስል Solan Kolli/AFP/Getty Images

በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ፍልስፍና ረዳት ፕሮፌሰር ሲሳይ አሰምሬ በዚሁ የመንግስት መግለጫ ላይ በሰጡን አስተያየት ግን የመንግስት ዋና ትኩረት የህዝብን ጥያቄ መመለስ ላይ ሊሆን ይገባል ብለዋል፡፡ “የሚመጣው ሰላም በግድ ሳይሆን በሰላም መሆን አለበት፡፡ እንደነ መንግስት ማተኮር ያለበት የህዘቡን ጥያቄ መመለስ ነው፡፡ የህዝቡ ጥያቄ ግልጽ ነው፡፡ እኩልነት እጂ የበላይነትም አይደለም፡፡ ህዝቡ የሚጠይቀውን የማንነት፣ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ጥያቄዎችን መመለስ ዘላቂ ሰላምን ያሰፍናል ብዬ አስባለሁ፡፡”

የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ ዶ/ር ለገሰ ቱሉ ግን በትናንት መግለጫቸው “ጽንፈኛ ዘራፊ ኃይል” ያሉት በክልሉ በትጥቅ የሚንቀሳቀሰው ቡድን ህገመንግስትን የመናድ ውጥን የነበረው በማለት ከሰዋል፡፡ ሚኒስትሩ የመንግስት የጸጥታ ሃይል ዜጎች ወደ መደበኛ ህይወት እንዲመለሱ ብሎም መሰረታዊ መብታቸው እንዲጠበቅ በሰሩት ስራ አሁን ላይ አንጻራዊ መረጋጋት ሰፍኗልም ብለዋል፡፡ በክልሉ ሰላምን ለማስፈን በተደረገው ጥረትም 3 ሺህ 200 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው በመጀመሪያው ዙር 1 ሺህ ያህሉ ጉዳያቸው ተጣርቶ የተፀፀቱ የተሃድሶ ስልጠና ወስደው ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዲቀላቀሉ ሆኗል ብለዋል፡፡አማራ ክልል አንፃራዊ ሠላም ሠፍኗል-ርዕሰ መስተዳድር

ዶ/ር ለገሰ በዚሁ መግለጫቸው ከሰሞኑ በመንግስታዊው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አማራ ክልል ውስጥ በመንግስት ጸጥታ ኃይሎች ሰላማዊ ዜጎች ላይ ጉዳት መድረሱን የገለጸበትን መግለጫ አጣጥለው ነቅፈውታል፡፡ “ከሰሞኑ የሰብዓዎ መብቶች ኮሚሽን ያወጣው መግለቻ አስተማማኝ መረጃ ላይ ያልተመሰረትና ሚዛናዊት የሚጎድለው ነው፡፡ በህገመንግስቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም ስልጣን የተሰጠው መርማሪ ቦርድ ባለበትና ቦርዱ ኃላፊነቱን እየተወጣ ባለበት ሁኔታ የኮሚሽኑ መግለቻ ገንቢና ሰብኣዊ መብትን ለማረጋገት አዎንታዊ ሚና ያለው አይደለም፡፡ በዚህ ላይ ኮሚሽኑ ተገቢውን እርምት እንዲወስድ ተስፋ እናደርጋለን፡፡ መንግስት የተቋሙን ገለልተንነት አበክሮ ይሻል፡፡ ገለልተኝነቱ ግን ከመንግስት ብቻ ሳይሆን ከባዕዳንም ጭምር ነው፡፡”

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ባወጣው መግለጫ አማራ ክልል ውስጥ ከሐምሌ ወር 2015 ዓ.ም. ጀምሮ በተካሄደው በከባድ መሣሪያ እና በአየር/ድሮን ድብደባ የታገዘ የትጥቅ ግጭት ሲቪል ሰዎች ላይ ሞት እና የአካል ጉዳት ማድረሱን ብሎም ለመፈናቀል ዳርጓል ማለቱ ይታወሳል፡፡ ኢሰመኮ ትናንት የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ በሰጡት መግለጫ ላይ ግን እስካሁን ያለው ነገር የለም፡፡ ዶይቼ ቬለ ለተቋሙ ኮሚዩኒኬሽን ክፍል ደውሎም በዚህ ላይ ምላሽ አላገኘም፡፡

ሥዩም ጌቱ

አዜብ ታደሰ

ኂሩት መለሰ