በአማራ ክልል ግጭት የተኩስ አቁም ጥሪ በአፍሪቃ ኅብረት
ሐሙስ፣ ነሐሴ 11 2015በኢትዮጵያ መንግስት እና በአማራ ክልል የሚገኙ ታጣቂዎች ባላቸው አካላት የተፈጠረው እና የብዙዎችን ሕይወት ቀጥፎ በርካቶችን ለጉዳት ያጋለጠው ግጭት እንዳሳሰበው እና ችግሩ በውይይት እንዲፈታ የአፍሪቃ ኅብረት ጠየቀ።
ሕብረቱ የኢትዮጵያ መንግሥት የተከሰተውን ጦርነትና የፀጥታ ችግር ለመቀልበስ በአማራ ክልል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከደነገገ በኋላ ባወጣው መግለጫው የሕብረቱ ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት የኢትዮጵያን ሁኔታ በቅርበት እና በከፍተኛ ሥጋት እየተከታተሉት መሆኑን ገልፀዋል።
በሀገሪቱ እና በአካባቢው መረጋጋትን ለማረጋገጥ የአፍሪቃ ኅብረት ከኢትዮጵያን ሕገ መንግስታዊ ሥርዓት፣ የግዛት አንድነት እና ሉዓላዊነት ጋር ያለውን ትስስር እንደሚያረጋግጥ የገለፀት ፋኪ ሁለቱም ወገኖች ጦርነቱን በአስቸኳይ እንዲያቆሙና የዜጎችን ከለላ እንዲያረጋግጡ ጠይቀዋል።
ሕብረቱ ያቀረበውን ጥሪ መነሻ በማድረግ ያነጋገርናቸው አንድ የአለም አቀፍ ሕግ እና የዲፕሎማሲ ተንታኝ "በአፍሪካ ሕብረት በኩል እድገት እያዩ" መሆኑን ገልፀው ነገር ግን የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ግልጽ አለመሆን አሁን ለተፈጠረው ግጭት መነሻ ምክንያት መሆኑን አስረጂ በመጥቀስ ሕብረቱ "ግጭትን ሊያስነሳ በማይችል መልኩ ድርድርን ማመቻቸት የማይችል ነው" ብለዋል።//
የአፍሪቃ ኅብረት በኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈንየሚደረገውን ተነሳሽነት ለመደገፍ ዝግጁ መሆኑን የሕብረቱ ኮሚሽን ሊቀመንበሩ ሙሳ ፋኪ ባወጡት መግልጫ አረጋግጠዋል። ግጭቱ እንዳሳሰባቸው የገለፁት ፋኪ ጉዳዩ በውይይት እንዲፈታም ጥሪ አቅርበዋል።
አሁን ያለው ግጭት በትግራይ ከነበረው ግጭት በመሠረታዊነት የሚለይባቸው ባህርያት አሉት ያሉት ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ አንድ የአለም አቀፍ ሕግ እና የዲፕሎማሲ ጉዳዮች ተንታኝ ፣ የትግራዩ አስቀድሞ መንግሥት የነበረ አካል አሁን ካለው መንግሥት ጋር ያደረጉት ፣ አሁን በአማራ ያለው ግን አስቀድሞ መንግሥት ከነበረ አካል ጋር ሳይሆን የሕዝብ በሆነ ኃይል እና በመንግሥት መካከል የሚደረግ ግጭት ነው ብለዋል። በትግራይ የነበረውን ጦርነት የሚመራው የታወቀ አካል ነበር ያሉት እኒሁ ሰው የአማራው ግን የተደራጀ አይደለም ማለት ባይቻልም ማዕከላዊ እና ይሄ ነው ተብሎ የሚመራው አካል የሚጠቀስለት አይደለም ብለዋል።
"የትግራዩ ግልጽ የሆነ የፖለቲካ አጀንዳ ነበራቸው። የቅቡልነት ጥያቄ ላይ የተነሳ ጥያቄ ነው የነበረው። ይሄኛው ግን የቅቡልነት ጥያቄ አይደለም አስቀድሞ የመጣው። አስቀድሞ የመጣው የመተማመን ጥያቄ ነው"
የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ያስከተላቸው ችግሮች የአፍሪካ ሕብረት አሁን ላቀረባቸው የሰላም ጥሪዎች መተማመኛ የሚነፍጉት ጉዳዮች ስለማስከተላቸው እኒሁ ሰው ገልፀዋል።
"የፕሪቶሪያ ስምምነትራሱ አሁን ላለንበት የቀውስ ሁኔታ መንገድ ከፍቷል። የግልጽነት ችግር ስለነበረበት። ሕብረቱ ሌላ ግጭት ሊያስነሳ በማይችል ምልኩ ድርድርን ማመቻቸት ይችላል የሚል እምነት የለኝም ። ምክንያቱም በትግራይ ኃይሎች እና በመንግሥት በኩል ያደረገው የማደራደር ሥራ ለሌላ ችግር ጥንስስ ሆኖ ስላገለገለ ነው" ብለዋል። ይህ ሲባል ግን የሕብረቱ ጥረት ሙሉ በሙሉ የሚናቅ እንዳልሆነም ተንታኙ ገልፀዋል።
"በአፍሪካ ሕብረት በኩል እድገት እያየሁበት ነው ብየ እወስዳለሁ። በእንደዚህ አይነት ገዳዮች ላይ ምንም የማይል ተቋም ነበር። ይሄ ተቋም በትግራይ የተዋጣ ሥራ ሠርቷል።
አሁንም እንደዚህ አይነት ነገሮችን የመቀጠል እድል አለው።"
በመንግሥት እና በፋኖ መካከል በአማራ ክልል የተደረገው ግጭት በዘላቂነት በሰላም እንዲፈታ ብዙ የምዕራብ ሀገራት፣ የተለያዩ የሀገር ውስጥ የሲቪክ እና የፖለቲካ ድርጅቶች በመወትወት ላይ ናቸው።
ሰለሞን ሙጬ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
አዜብ ታደሰ