ጀርመንና ኬንያ በሰለጠኑ ሞያተኞችና ፍልሰተኞች ጉዳይ ስምምነት ተፈራረሙ
እሑድ፣ መስከረም 5 2017ጀርመንና ኬንያ በሰለጠኑ ሞያተኞችና ፍልሰተኞ ጉዳይ ስምምነት ተፈራረሙ
የጀርመን መራሔ መንግሥት ኦላፍ ሾልዝ እና የኬንያዉ ፕሬዚዳንት ዊልያም ሩቶበሞያ የሰለጠኑ እና ችሎታ ያላቸው ኬንያዉያን ወደ አውሮጳ እንዲመጡ የሚያስችል ስምምነት ተፈራረሙ። ስምምነቱ በጀርመን ተቀባይነት ያላገኙ ስደተኞች በፍጥነት ወደ አገራቸው እንዲመለሱ የሚያስችል ነዉ።
ጀርመን እና ኬንያ ከምስራቅ አፍሪቃዊትዋ ሃገር ሞያተኞች በምጣኔ ሐብት ወደበለፀገችዉ ወደ አዉሮጳዊትዋ ሃገር ጀርመን መምጣት እንዲችሉ የሚያስችል ስምምነት ከትናንት በስትያ አርብ ተፈራርመዋል።
ሁለቱ አገራት የተፈራረሙት “ሞያተኛ ሰራተኞች እና የፍልሰት ስምምነት” በጀርመን የመቆየት መብት የሌላቸው ኬንያውያን ወደ አገራቸው እንዲመለሱ የሚያደርግም ነዉ። በርካታ በእድሜ የገፉ ሠራተኞች ያላት ጀርመን የወጣት ሰራተኛ ኃይል እንደሚያስፈልጋት ተመልክቷል። እንደ ምሁራን ገለፃ ጀርመን በየዓመቱ ወደ 400,000 ባለሞያ ሰራተኞች ያስፈልጓታል። ስምምነቱ የሃገራቱን እና የህዝብን ግንኙነት እንደሚያጠናክር የኬንያዉ ፕሬዚዳንት ተናግረዋል።
«ዛሬ በስደተኞችና በሰራተኞች ኃይል ጉዳይ ላይ የተፈራረምነዉን የትብብር ስምምነት እያከበርን ነዉ። ይህ ስምምነት በሁለቱ ሀገሮች እና በህዝብ መካከል ያለውን ግንኙነት ለማስፋት የሚያስችል ማዕቀፍን ይፈጥራል። የወጣት ኃይል ያላት ኬንያን ይዘን የጀርመንን የቴክኖሎጂ አቅም ለመጠቀም እድል ይሰጠናል። ብዙ የተማሩ እና ትጉህ ሰራተኛ ወጣቶች አሉን» ብለዋል።
ሾልዝ 'ለዓለም ክፍት' መሆናትን ለብልፅግናችን ዋናዉ ቁልፍ ነዉ
የጀርመኑ ቻንስለር ኦላፍ ሾልዝ ከኬንያውፕሬዝዳንት ዊልያም ሩቶ ጋር ባደረጉት ውይይት የሰራተኛ እጥረት ተፅዕኖ "ለሚመጡት ዓመታትና አስርት ዓመታት ከእኛ የሚቆይ ይሆናል" ሲሉ ተናግረዋል።
«ይህ ስምምነቱ በሞያ የተካኑ ሠራተኞችን እጥረት ለማካካስ ሊረዳን ይችላል» ሲሉም አክለዋል። «በሌላ በኩል ስምምነቱ ኬንያ ለመጡና ግን እዚህ የመቆየት መብት የሌላቸዉ ወይም መቆየት ለማይችሉ ውጤታማ መልስን ይዟል፤ እነዚህ ዜጎች አሁን በቀላሉና በፍጥነት ወደ ቤታቸው መመለስ ይችላሉ።" »
የቻንስለር ሾልዝ መንግሥት በቅርቡ በጀርመንዋ ዞሊንገን ከተማ የተፈፀመዉን የስለት ጥቃት እና ፀረ-ስደተኛ ጠል የሆነዉ አማራጭ ለጀርመን (AfD) ፓርቲ በሁለት ምሥራቃዊ ጀርመን ግዛቶች በተካሄደዉ ምርጫ ያገኘዉን ስኬት ተከትሎ ህገወጥ ስደተኞች ላይ ጠንካራ አቋም ለመውሰድ እየሞከረ መሆኑን እያሳየ ነዉ ተብሏል። የጀርመኑ ቻንስለር ሾልዝ ሕጋዊ ፈቃድን በመጠቀም ወደ ሀገር ዉስጥ የሚገቡትን ዜጎች አመስግነዋል። "የብልፅግናችን መሰረት ለዓለም ክፍት መሆናችን ነው" ሲሉ ሾልዝ ተናግረዋል።
« የኢኮኖሚ ብልጽግናችን መሠረት ለዓለም ክፍት መሆናችን ነው። ይህ በመላው ዓለም ወደ ውጭ የምንልከውን ሸቀጦቻችንን እንዲሁም ከመላው ዓለም የምናስገባዉን ሸቀጦች ሁሉ ይመከታል ። ጀርመን በብዙ የዓለም አገሮች የምታፈሰዉን መዋዕለ ንዋይ እና ኩባንያዎችን ይመለከታል። ይህ የኢኮኖሚያችን ጥንካሬ አንዱ ክፍል ነው ። ይሁን እንጂ ብልጽግናችንን ለማስቀጠል የሚያስችል በቂ ሠራተኛ ኃይል አለን ወይ የሚለው ጥያቄ ሌላዉ ነዉ። እናም ይህን ለማስቀጠል በተመሳሳይ ሰዓት ህገወጥ ፍልሰት መቀነስ ያስፈልጋል፤ እኛም ይህን እያደረግን ነዉ።»
የኬንያዉ ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ በበኩላቸዉ ሁለቱ አገራት የፍልሰተኞች እና የሠራተኛ ኃይል የወዳጅነት ስምምነቱን በደስታ ተቀብለዋል። "ከፍተኛ ህዝብ በሚኖርባት በኬንያ፤ በርካታ ወጣቶች የሚጠቀሙበት ይሆናል » ሲሉም ስምምነቱን አወድሰዋል።
«ከጀርመን ጋር በመተባበር፣ የወጣቶችን አዲስ ፈጠራ፣ የፈጠራ ችሎታ፣ ኃይል እና አቅም ፣ ተሰጥኦ እና እውቀት ከጀርመን ኢንቨስትመንት፣ ቴክኖሎጂ እና ሀብት ጋር በማቀናጀት ትልቅ ውጤት ማግኘት እንችላለን።»
ሩቶ በተጨማሪ የሕገወጥ ፍልሰትን አስመልክቶ "ለእኛም ሆነ ለጀርመን ችግር" በመሆኑ ፈጣን ምላሽ ማግኘት አለበት ሲሉ ለስምምነቱ ድጋፋቸዉን አክለዋል።
የሁለቱ ሃገራት ባለስልጣናት ስምምነትን በርካታ ኬንያዉያን በይሁንታ ቢቀበሉትም፤ ትችት የሰነዘሩ ጥቂቶች አይደሉም። ናይሮቢ ላይ የሪል ስቴት መኖርያ ቤቶች አጫራች የሆነዉ ወጣት፤ በመጀመርያ በቤታችን ስራ እንፍጠር ይላል።
«በመጀመሪያ በቤታችን ውስጥ ሥራ መፍጠር ይኖርብናል፤ ከዚያ ሥራን ሌላ አገር መፍጠር ይቻላል። ቅድምያ የሥራ ገበያችንን ማሻሻል ይኖርብናል፤ ከዚያ ወደ ሌሎች እንሄዳለን። ዉጭ አገር ላይ እርዳታ በመስጠት ከተጠመድን ትውልዳችንን ማስተማር የምንችልበት ምንም መንገድ አይኖረንም። የምንፈጥረዉ ሥራም ሞያዊ ቢሆን ጥሩ ነው። ካልሆነ ግን ጥሩ አይመስለኝም።»
የግብር እቅድ ይዘዉ በህዝብ ተቃዉሞ የተሻረባቸዉ የኬንያዉ ፕሬዚዳንት ዊልያም ሩቶ፤ ስልጣን ከያዙ ባለፈዉ ሳምንት ሁለት ዓመት ሆናቸዉ።
አዜብ ታደሰ
ነጋሽ መሐመድ