1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የጀርመን ጉብኝት

ማክሰኞ፣ ጥቅምት 5 2017

ጀርመን፣ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደንን በቀይ ምንጣፍ ለመቀበል ሽርጉድ እያለች ነው።ባይደን በዚህ ጉብኝታቸው የጀርመን ፌደራል መንግሥት «የመልካም ሥራ የታላቅ መስቀል ኒሻን» ከጀርመን ፕሬዝዳንት ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየር ይበረከትላቸዋል። የሚሸለሙትም ለጀርመንና አሜሪካን ወዳጅነት እንዲሁም ለአትላንቲክ ወዲያ ማዶ ኅብረት ላበረከቱት አስተዋጽኦ ነው።

https://p.dw.com/p/4lq4U
ባይደን ባለፈው ዓመት የካቲት ዋይት ሀውስ ውስጥ ከጆ ባይደን ጋር ሲነጋገሩ
ባይደን ባለፈው ዓመት የካቲት በዋይት ሀውስ ከጆ ባይደን ጋር ሲነጋገሩ ምስል Andrew Harnik/AP Photo/picture alliance

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የጀርመን ጉብኝት

የሥልጣን ዘመናቸው ሊያበቃ ጥቂት ወራት የቀሯቸው የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አሁን ስንብት ላይ ናቸው። ሥልጣናቸውን በመጪው ጥር ለአሸናፊው ፕሬዝዳንት ከማስረከባቸው በፊት ባለፈው ሳምንት ጀርመንን ለመጎብኘት አቅደው ነበር። አሜሪካንን በመታው በሚልተን ማዕበል ምክንያት ግን ጉብኝቱ ወደዚህ ሳምንት ተሻግሯል ። በደፈናው ባይደን በዚህ ሳምንት መጨረሻ ጀርመንን እንደሚጎበኙ ቢነገርም እስከ መቼ እንደሚቆዩ ግን ይፋ አልሆነም። የሚታወቅ ነገር ቢኖር ባይደን በዚህ ሳምንት መጨረሻ ጀርመን ሲመጡ በከፍተኛ ፕሮቶኮል ፣የክብር አቀባበል እንደሚደረግላቸው ነው። የዶቼቬለዋ ካርላ ቢከር እንደዘገበችው፣ ከጎርጎሮሳዊው 1985 ወዲህ አንድ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ጀርመንን በይፋ ሲጎበኝ ባይደን የመጀመሪያው መሪ ናቸው። በ1985 ጀርመንን በይፋ የጎበኙት የቀድሞው የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ሮናልድ ሬገን ነበሩ።ከሬገን በኋላ ሌሎች የአሜሪካን ፕሬዝዳንቶች በተለያዩ አጋጣሚዎች ጀርመን ቢመጡም ጉብኝታቸው ግን ይፋዊ አልነበረም። 


እናም ጀርመን ተሰናባቹን ባይደንን በቀይ ምንጣፍ ለመቀበል ሽርጉድ እያለች ነው። ባይደን በዚህ ጉብኝታቸው የቀድሞውን የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ሮናልድ ሬገን እንደተኩት እንደ ፕሬዝዳንት ጆርጅ W ቡሽ የፌደራል መንግሥቱ «የመልካም ሥራ የታላቅ መስቀል ኒሻን» ከጀርመን ፕሬዝዳንት ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየር ይበረከትላቸዋል። የፌደራል ጀርመን ፕሬዝዳንት ይህን ሽልማት ፣ለፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የሚያበረክቱት ለጀርመን እና አሜሪካን ወዳጅነት እንዲሁም ባለፉት 5 አሥርት ዓመታት ይህን ወዳጅነትና ግንኙነት ቅርጽ ባስያዙበትና ባጠናከሩበት ከአትላንቲክ ውቅያኖስ ወዲያ ማዶ ላለው ኅብረት ለሰጡት አገልግሎት ክብር ነው ሲል የፌደራል ጀርመን ፕሬዝዳንት ቢሮ በቅርቡ አስታውቋል።

 የአሜሪካን ምርጫ ጀርመንና የአውሮጳ ኅብረት  

የጀርመን ፕሬዝዳንት ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየር
የጀርመን ፕሬዝዳንት ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየርምስል Saul Loeb/AFP/Getty Images


የዩናይትድ ስቴትስና የአውሮጳ  በተለይ ደግሞ የዩናይትድ ስቴትስና የጀርመን ግንኙነት ለባይደን በጣም አስፈላጊ ነበር።  ሚሼል ኤጋን ዋሽንግተን በሚገኘው የአሜሪካን ዩኒቨርስቲ መምህርትና የዩናይትድ ስቴትስና የአውሮጳ ግንኙነት አዋቂ ናቸው። ለዶቼቬለ በሰጡት ቃለ ምልልስ የፕሬዝዳንቱ ዘመነ ስልጣን ማብቂያ በተቃረበበት በአሁኑ ሰዓት ባይደን ከአትላንቲክ ውቅያኖስ ወዲያ ማዶው  ግንኙነት እንዲሰምር ያበረከቱትን የረዥም ጊዜ አስተዋጽኦ  ወደ ኋላ መለስ ብለው አስታውሰዋል።

«ምናልባትም ከሰሜን አትላንቲክ የጋራ መከላከያ ቃል ኪዳን ድርጅት በምህጻሩ ኔቶ በኩል ፣ በሙኒክ የፀጥታ ጉባኤ ፣በውጭ ጉዳዮች ኮሚቴ በኩል ለረዥም ጊዜ የነበራቸው ተሳትፎ እና ፕሬዝዳንት ከመሆናቸው በፊት በርካታ የአውሮጳ መሪዎችን ማወቃቸው ትክክለኛ ግምገማ የሚሆን ይመስለኛል።»

ከአትላንቲክ ወዲያ ማዶው ግንኙነት ባይደን ለምን ታዋቂ ሆኑ?



የ81 ዓመቱ ባይደን ያደጉት ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ለጀርመን መልሶ ግንባታ እርዳታ ታደርግ በነበረች ሀገር በአሜሪካን ነው። ባይደን በጎርጎሮሳዊው 1961 የበርሊን ግንብ ከተገነባ በኋላ በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት ምዕራብ ጀርመን የዩናይትድ ስቴትስ ጠቃሚ አጋር መሆንዋን ተመልክተዋል ይላሉ ፒተር ስፕራዲንግ የፕሬዝዳንታዊና የምክር ቤት ጉዳዮች ጥናት ማዕከል ምክትል ፕሬዝዳንት «ከጎርጎሮሳዊው 1972 አንስቶ ፖለቲካ ውስጥ ናቸው።በኔ እምነት ጀርመን የግጭቱ ማዕከል ከሆነችበት  ከቀዝቃዛው ጦርነት ልምድ ቢያንስ በውጭ ፖሊሲ መስክ ቀደም ካለ ጊዜ አንስቶ እንዲቀረጹ ተደርገዋል»
በባራክ ኦባማ የፕሬዝዳንትነት ዘመን ምክትል ፕሬዝዳንት የነበሩት ባይደን በውጭ ፖሊሲ ያላቸው ልምድ ታላቅ ቦታ የሚሰጠው ነበር። ኤጋን ለዶቼቬለ እንደተናገሩት ያኔ የኦባማ ልምድ አናሳ ነበር። 
«ኦባማ በውጭ ፖሊሲ ረገድ እውቀታቸው በጣም ውስን ነበር። ባይደን ምክትል ፕሬዝዳንት ለመሆን የበቁበት ምክንያትም ይህ ነበር። ባይደን ግንኙነቱ፣እውቀቱ እንዲሁም በሴናተርነት ሚናቸው የሚሰጧቸው ገለጻዎችም ነበሯቸው።»

ጀርመን እና ዩናይትድ ስቴትስ በዩክሬኑ ውዝግብ
ኤርጋን እንደሚሉት ኦባማ በስልጣን ዘመናቸው በአውሮጳ በጣም ታዋቂ ነበሩ። ይህ የሆነውም ከፕሬዝዳንት ጆርጅ W ቡሽ በኋላ የአትላንቲክ ውቅያኖስ ወዲያ ማዶ ግንኙነት እንደገና እንዲያንሰራራ በማድረጋቸው ነው ይላሉ ኤርጋን። ይሁንና በኤርጋን አባባል  ስሜታዊ ግንኙነት የነበራቸው ግን ባይደን እንጂ ኦባማ አልነበሩም። 

የጀርመን መራኄ መንግሥት ኦላፍ ሾልዝ ስልጣን በያዙ በጥቂት ወራት ውስጥ ዋሽንግተንን በጎበኙበት ወቅት ከጆ ባይደን ጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሰጡ
የጀርመን መራኄ መንግሥት ኦላፍ ሾልዝ ስልጣን በያዙ በጥቂት ወራት ውስጥ ዋሽንግተንን በጎበኙበት ወቅት ከጆ ባይደን ጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሰጡ ምስል Anna Moneymaker/Getty Images


ዩናይትድ ስቴትስንና ጀርመንን የሚያመሳስሏቸው በርካታ ጉዳዮች 

 

ዛሬም በባይደን የፕሬዝዳንትነት ዘመን ጀርመን የዩናይትድ ስቴትስ ዋነኛ አጋር ሆና ቀጥላለች።  ሁለቱም ሀገራት ዩክሬን ከሩስያ ጋር በምታካሂደው ጦርነት ዋነኛዎቹ ደጋፊዎች ናቸው። ከዚህ ሌላ ዩናይትድ ስቴትስና ጀርመን በተለየ በወቅቱ የመካከለኛው ምሥራቅ ግጭት የእሥራኤልን ራሷን የመከላከል መብት በጣም አጠናክረው አጽንኦት ከሚሰጡ ሀገራት መካከል ናቸው። 
ሁለቱ ሀገራት በዓለም አቀፍ መድረኮች ከሚይዙት ተመሳሳይ አቋም በተጨማሪ በሀገር ውስጥም ተመሳሳይ  ፖለቲካዊ ተግዳሮቶች ውስጥ ይገኛሉ።ኤርጋን እንደሚሉት በጀርመን የቀኝ ክንፍ ህዝበኞች እና በከፊልም የቀኝ ጽንፈኛው AFD መነሳት በህዝቡ መካከል ልዩነቶች የመኖራቸው ምልክት ነው። በአሜሪካም የፖለቲካው መሰነጣጠቅም እንዲሁ፤

«በዩናይትድ ስቴትስም በጀርመንም የፖለቲካ መሰነጣጠቅ እየታየ ነው። ይህ በአማራጭ ለጀርመንና በአዲሱ የሳራ ቫግንክኔሽት ኅብረት ፓርቲዎች እየተጠናከሩ መምጣት በግልጽ እየታየ ነው።ባይደን የስልጣን ዘመናቸው መጨረሻ ላይ ደርሰዋል። ሾልዝ ደግሞ በሀገር ውስጥ ያላቸው የህዝብ ድጋፍ አጠራጣሪ ሆኗል። በመጪው ምርጫ የፓርቲያቸው እጣ ፈንታ ከወዲሱ አስግቷል። ባይደንን የተኩት የዴሞክራቶች እጩ ተወዳዳሪዋ ካማላ ሀሪስ መመረጥ አለመመረጣቸው በእንጥልጥል ያለ ጉዳይ ነው። ሁለቱም በዚህ ሳምንት የሚገናኙት የፖለቲካ ህልውናቸው በየሀገራቸው ድጋፍና ተቀባይነት እየቀነሰ በመጣበት የፖለቲካ መሰነጣጠቅ ወቅት ነው »

ሌላው የሚያመሳስላቸው ጉዳይ ደግሞ የድንበር ቁጥጥር ነው። ጀርመን በሸንገን ስምምነት ነጻ የህዝቦች ዝውውር ቢኖርም የድንበር ቁጥጥርን ተግባራዊ ማድረግ ጀምራለች።አንድ ስደተኛ ዞሊንገን በተባለችው ከተማ ባለፈው ነሐሴ ሦስት ሰዎችን በስለት ወግቶ ከገደለ በኋላ የፍልሰት ፖሊሲዋን አጥብቃለች። ከዚሁ ጋርም በሁሉም የጀርመን ድንበሮች ከአውሮጳ ኅብረት አባል ሀገራት ጋር የሚያዋስኗትን ጨምሮ የድንበር ቁጥጥሯን አጠናክራለች። የድንበር ቁጥጥር ጉዳይ የባይደን አስተዳደር በተለይም የዴሞክራቶች ፓርቲ እጩ ፕሬዝዳንትና የምክትል ፕሬዝዳንት ካማላ ሃሪስ የምርጫ ዘመቻ ትኩረትም ነው።

 የጆ ባይደን የአውሮጳ ጉብኝት ና ፋይዳው 
« ሁለተኛው የሚያመሳስላቸው ጉዳይ ሁለቱም በድንበር ጉዳይ መጠመዳቸው ነው። ምንም እንk/ን የሸንገን ስምምነትና የአውሮጳ ኅብረት ቢኖርም ጀርመን የድንበር ቁጥጥር ታካሂዳለች። ባይደንም እርግጥ ነው ወይም በተለይ ፕሬዝዳንታዊ እጩዋ ካማላ ሀሪስ የድንበር ቁጥጥር ጉዳይ እና ጥያቄ የምርጫ ዘመቻቸው አንዱ ክፍል ሆኗል። 



ዩናይትድ ስቴትስ ፊትዋን ወደ ሌሎች አጋሮች እያዞረች ነው

 

የስልጣን ዘመናቸው ማብቂያ የተቃረበው የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ከአትላንቲክ ውቅያኖስ ወዲያ ማዶው ግንኙነት የመጨረሻው ታላቅ ሰው ተደርገው ይታያሉ። ምክንያቱም ጀርመን በዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ፖለቲካ ውስጥ ከቀድሞው ያነሰ ሚና ነው የሚኖራት ተብሎ ነው የሚታሰበው።ከዚህ በተጨማሪ በፒተር ስፓርዲንግ አስተያየት  ከአሁን በኋላ ዩናይትድ ስቴትስ እንደቀድሞው ጀርመን የምትተማመንባት ጠንካራ የአውሮጳ ጸጥታ አስከባሪ ልትሆን አትችልም።የወደፊቱ ግንኙነታቸውም የተለየ መሆኑ አይቀርም።

የቀድሞዋ የጀርመን መራኂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ከዛሬ 3 ዓመት በፊት አሜሪካንን በጎበኙበት ወቅት ከጆ ባይደን ጋር ሲነጋገሩ
የቀድሞዋ የጀርመን መራኂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ከዛሬ 3 ዓመት በፊት አሜሪካንን በጎበኙበት ወቅት ከጆ ባይደን ጋር ሲነጋገሩ ምስል Evan Vucci/AP Photo/picture alliance


« ማንም ፕሬዝዳንት ይሁን ማን ወደፊት የጀርመንና የአሜሪካን ግንኙነት የተለየ ነው የሚሆነው።ዩናይትድ ስቴትስ ፊቷን ወደ ኢንዶ ፓስፊክ እና ከፍ ወዳለችውና ትልቅ ተፎካካሪዋ አድርጋ ወደምታያት ወደ ቻይና ነው የምታዞረው። ስለዚህ ጀርመን  በአውሮጳ ውስጥ ወይም በአውሮጳ ዙሪያ የበለጡ ሃላፊነቶችን መውሰድን የመሳሰሉ የሚጠበቁ አንዳንድ ነገሮች ይኖራሉ።»

ኂሩት መለሰ

ሸዋዬ ለገሠ
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ