1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

«የምወደውን ሙያዬን ትቼ ወደ ሌላ ለመሄድ እያሰብኩ ነው»

ልደት አበበ
ዓርብ፣ ነሐሴ 24 2016

በዛሬው የወጣቶች ዓለም ዝግጅት መምህራን ምን አይነት የኢኮኖሚ ፈተናን ተጋፍጠው እያስተማሩ እንደሆነ ጠይቀናል። ያነጋገርናቸው መምህራን ወጣት እንደመሆናቸው ገና ረዥም የሥራ ዘመን ይጠብቃቸዋል። ሁሉም ለተሰማሩበት ሙያ ትልቅ ፍቅር ቢኖራቸውም የኢኮኖሚው ጉዳይ ግን ትልቅ ፈተና ደቅኖባቸዋል።

https://p.dw.com/p/4k5Kf
Doktorhut auf einem Bücherstapel
ምስል picture.alliance/blickwinkel/BilderBox/McPHOTO

መምህራን ለምን ሌሎች የስራ አማራጮችን መፈለግ ተመኙ?

መምህር ዲሪባ ዋቅጅራ ፣ መምህር ጌታቸው ስንቁ እና መምህርት ሄለን መሰል ፤  ሦስቱም በሠላሳዎቹ መጀመሪያ ላይ የሚገኙ የዩንቨርሲቲ መምህራን ናቸው።  ሁሉም ለተሰማሩበት ሙያ ትልቅ ፍቅር ቢኖራቸውም የኢኮኖሚው ጉዳይ ግን ትልቅ ፈተና ደቅኖባቸዋል። መምህራን በየጊዜው በክፍያ የተነሳ አቤቱታ ሲያሰሙ ተደምጠዋል። አሁን ደግሞ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ከተደረገ በኋላ ኑሮ ይበልጥ ፈተና ሆኖባቸዋል። በዚህ ዝግጅት ያነጋገርናቸው መምህራን ወጣት እንደመሆናቸው ገና ረዥም የሥራ ዘመን ይጠብቃቸዋል። 

መምህራን ለምን ሌሎች የስራ አማራጮችን መፈለግ ተመኙ?

በጅማ ዩንቨርሲቲ መምህር ከሆነው ዲሪባ ዋቅጅራ እንጀምር ፤  ለስድስት ዓመታት ያህል በመምህርነት እና የምርምር ስራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል።  የከፍተኛ ተቋም መምህር መሆን ምኞቱ ነበር። « የከፍተኛ ተቋም መምህር መሆን በማኅበረሰቡ ዘንድም በጣም ተቀባይነት ያለው ሙያ ነበርና እኔም ህልሜ ከፍተኛ ውጤት አምጥቼ እዚህ የዩንቨርሲቲ መቅረት ወይም ሌላ ቦታ ማስተማር ነበር። እንደአጋጣሚ ስጨርስ ጥሩ ውጤት አምጥቼ መቅረት ቻልኩኝ።»
ይሁንና ባለፉት ተከታታይ ዓመታት የከፍተኛ ተቋም መምህራን ደሞዝ ሳይሻሻል መቆየቱ በተለይ በአሁኑ ወቅት የኢኮኖሚ ማሻሻያውን ለመቋቋም ትልቅ ጫና ፈጥሮበታል።  ይህም ሌሎች የሥራ እድሎችን እና አማራጮችን እንዲመለከት እያስገደደው ነው። «እኔ የማስተርስ ዲግሪ ነው ያለኝ። ከፍተኛ ተቋም ውስጥ የሚሠራ የማስተርስ ምሩቅ መምህር የሚያገኘው የተጣራ ደሞዝ 10000 ብር ገደማ ነው፣ አሁን ባለው ሁኔታ ወደ 94 ዶላር ገደማ ማለት ነው በወር የሚያገኘው። በዚህ ሁኔታ ኑሮን መምራት አይቻልም። እኔ ወደዚህ ሙያ ስገባ ሌሎች አማራጮችን ትቼ ነው ። ያኔ NGO የመግባት እድልም ነበረኝ። አሁን ግን የምወደውን ሙያዬን ትቼ ወደ ሌላ ለመሄድ እያሰብኩ ነው»

አማራ ክልል ጊራና ውስጥ ተማሪዎች ቁጭ ብለው ሲማሩ፣ መምህሩ ሲፅፉ
አማራ ክልል ጊራና ውስጥ ገጠራማ አካባቢ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥምስል picture-alliance/ dpa

«PHD ከያዝኩም በኋላ ይህን ያህል የደሞዝ ጭማሪ የለውም»

ልክ እንደ መምህር ዲሪባ  31 ዓመቱ  የሆነው የደባርቅ ዩንቨርሲቲ መምህር ጌታቸው ግን አማራጭ የለውም።  በአሁኑ ሰዓት እንደ መምህር እየተከፈለው ለPHD ወይም ለዶክትሬት ትምህርቱ ባህርዳር ከተማ የሚገኝ ሲሆን፤ በቅርቡ ትምህርቱን እንደጨረሰ ውል እና ግዴታ ስላለበት ወደ ደባርቅ ዮንቨርሲቲ ተመልሶ ማስተማር ይኖርበታል። «እንጂ ከዛ ውጪማ ኑሮ ብዙ አማራጮች አሉት። ስመለስ  የግድ መምህር ሆኜ ስድስት ዓመት ማስተማር አለብኝ። ከአሁን በፊትም ያልጨረስኩት ውል አለ። ማስተርስ ያስተማረኝ መንግሥት ነው። ውጭ ሀገር እንኳን የትምህርት እድል አግኝቼ ለመሄድ መረጃ እጄ ላይ የለም። ችግሬን ውስብስብ የሚያደርገው እንደዚህ አይነት ውል እና ግዴታዎች ናቸው።» ስለሆነም የመምህራን ደሞዝ በደንብ ካልተሻሻለ ጌታቸው በሚያገኘው ደሞዝ ኑሮን ማሸነፍ አለመቻሉ  በጣም ስጋት ደቅኖበታል።  « ደሞዝ የተጣራ 9ሺ እና የተወሰነ ተጨማሪ ነገር አለው። 4000 ብሩን ለቤት ኪራይ እከፍላለሁ። በቀረው ነው ኑሮውን የምንመራው። ትዳር አለኝ፤ ልጅ አለኝ። በዚህ ደሞዝ ራሴንም ሆነ ቤተሰቤን ማስተዳደር ተስኖኛል። PHD ከያዝኩም በኋላ ይህን ያህል የደሞዝ ጭማሪ የለውም ግን ታይትሉ ይጠቅመኛል ብዬ አስባለሁ»

የ32 አመቷ ሄለን ባህርዳር ዩንቨርሲቲ ውስጥ የጂኦግራፊ እና የአካባቢ ጥናት መምህርት ናት። ላለፉት 10 ዓመታት በሥራ ዓለም ላይ ትገኛለች። « ከፍተኛ ተቋም ውስጥ ማስተማር ማለት እድለኛ እንደመሆን ነው የምቆጥረው። ትውልድ ነው የምንቀርፀው። እነሱ ደግሞ ደህና ቦታ ደርሰው ሕይወታቸው ሲቀየር ማየት ትልቅ ርካታ ነው።  ነገር ግን አሁን ካለው ከኢኮኖሚው ጫና አንፃር  የምንሰራው ስራ እና የሚከፈለን አይገናኝም። በኑሮ ውድነት እየተሰቃዩ ለማስተማር ያለው ዝግጁነት ውጤታማ ላይሆን ይችላል።
ይህ ብቻ አይደለም።  «መምህራን ከዚህ ቀደም በማህበረሰቡ ዘንድ ከፍተኛ ከበሬታ ነበራቸው» የሚለው ጌታቸው ዛሬ ግን ገንዘብ ማጣታቸው ከበሬታቸውን  እየነጠቃቸው እንደሆነ እና ከስም ያለፈ ክብደት እንደሌለው በብሶት ይናገራል።

ሐዋሳ የአንድ መኖሪያ ቤት እጣ የወጣላቸው መምህርት በደስታ ሲፈነድቁ
ሐዋሳ የአንድ መኖሪያ ቤት እጣ የወጣላቸው መምህርት በደስታ ሲፈነድቁምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

«ያልሆነ ሸሚዝ ፣የተንሻፈፈ ጫማ አርገን በዚህ ሁኔታ ማንም ሊያከብረው አይችልም።»

አሁን ላይ መምህር መሆንን እንደ ስድብ ሆኗል የሚቀምበት። ለትዳር እንኳን እሱ ይቅርብሽ መምህር ነው ይባላል። ሰው የሚለካው ባለው ነው። ሰው እንዲያከብረን ደግሞ የሆነ ነገር ሊኖረን ይገባል። ያልሆነ ሸሚዝ ፣የተንሻፈፈ ጫማ አርገን በዚህ ሁኔታ ማንም ሊያከብረው አይችልም። የመምህር ክብሩ ወርዷል። 
ምንም እንኳን መምህርት ሄለን ከወንድ ባልደረባዎቿ አንፃር በሥራው ዓለም ብዙ ጊዜያትን ያስቆጠረች ቢሆንም ደሞዟ ተመሳሳይ እንደሆነ ገልፃልናለች። « በየትኛው ደረጃ ያለ መምህር ምንም ያህል ጊዜ ቢያገለግል የሚከፈለው ገንዘብ ተመሳሳይ ነው። ወንድ ከሆኑት መምህራን ይልቅ ኑሮ ውድነቱ ትልቅ ተፅዕኖ አለው።  ምክንያቱም ቤት ውስጥ ማስተዳደር ፣ ልጅ ማሳደግ፣ ማስተማር አለ።  እናከስራ ይልቅ ስለ ኑሮ ነው የምናስበው።  ከሚመለከታቸው አካላት የምንፈልገው የሰራተኛውን ኑሮ ማሻሻል እና ገበያውን መቆጣጠር ቢቻል ጥሩ ነው። » 

መምህር ዲሪባ የኢኮኖሚ ጫናዎችን በተመለከተ በተለያየ ጊዜ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ንግግር መካሄዱን ያስታውሳል። በተለይ ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ከመምህራን ተወካዮች ጋር ጋደረጉትን እና በሚዲያ የተላለፈውን ውይይት እንደ ምሳሌ ያነሳል። ነገር ግን እስካሁን ድረስ ምንም አይነት ለውጥ ባለመገኘቱ መንግሥት «ዳግም ቢያጤነው» ይላል ።« የሚያስታውሱ ከሆነ በዚህ ጉዳይ ላይ ጥር 15 ቀን፣ 2015 ዓ.ም ከመምህራን ተወካዮች ጋር ስብሰባ ነበር። ያኔ ያሉን ነገር ነበር። እኛም ተስፋ ያደረግነው። እሳቸው ያሉን የቤት መሥሪያ ቦታ በክልሎች አስተዳደሮች እና በከተማ ከከንቲባዎች በኩል ይመለሳል ነበር። ነገር ግን እነዚህ አካላት ግን ለዚህ ምላሽ ሊሰጡን አልቻሉም እና መንግሥት አፋጣን ምላሽ ቢሰጠን» 

ልደት አበበ

ማንተጋፍቶት ስለሺ