በትግራይ የመምህራንና መንግሥት ሠራተኞች የ18 ወራት ውዝፍ ደሞዝ አቤቱታ
ሰኞ፣ ታኅሣሥ 8 2016
የ18 ወራት ውዝፍ ደመወዝ እላልተከፈላቸው ለችግር ተጋልጠው እንደሚገኙ የትግራይ ክልል መምህራን እና ሌሎች የመንግሥት ሠራተኞች ገለፁ። ይኽን ቅሬታ ያነሳው የመምህራን የተቃውሞ ሰልፍ ትናንት በክልሉ ሽረ ከተማ ተካሂዷል። መምህራን ውዝፍ ክፍያ ባለማግኘታቸው በአንዳንድ አካባቢዎች ትምህርት ቤቶች እየተዘጉ እንደሆነ ተገልጿል።
የ2014 በጀት ዓመት ሙሉ እና የ2015 ዓ,ም አምስት ወራት ደሞዝ አልተሰጠንም የሚሉ በትግራይ የሚገኙ መምህራንን ጨምሮ አብዛኛው የመንግሥት ሠራተኞች ደሞዛቸው እንዲከፈላቸው በተለያዩ ጊዜያት ቅሬታቸው ሲያቀርቡ ቆይተዋል። ውዝፍ ደሞዛችንን መንግሥት አልከፈልንም ያሉ በትግራይ ክልል ሽረ ከተማ የሚገኙ አስተማሪዎች ትናንት እሑድ በከተማዋ ጥያቄ እና ቅሬታዎቻቸውን ያቀረቡበት ሰልፍ አካሂደዋል። የሽረ መምህራን ማሕበር ሊቀመንበር መምህር ተክላይ በላይ፤ የ18 ወራት ደሞዛችን እንዲሰጠን በተደጋጋሚ ጥያቄ ብናቀርብም ምላሽ በማጣታችን ሰልፍ አድርገናል ይላሉ። የመምህራኑ ሰላማዊ ሰልፍ እንዳይካሄድም አስቀድመው የመንግሥት አካላት በተደጋጋሚ ለማደናቀፍ ሞክረው እንደነበርም መምህር ተክላይ ጨምረው ገልፀዋል።
«የትግራይ መምህራን እያቀረቡት ያለው የመኖር ጥያቄ ነው» ያሉት የትግራይ መምህራን ማሕበር ምክትል ፕሬዝደንት መምህርት ንግሥቲ ጋረድ፥ «አስተማሪው ውዝፍ ደሞዙ ሳይከፈለው ውዝፍ ዕዳ እንዲከፍል እየተገደደ ነው፥ በዚህም ለከፋ ኢኮኖሚያዊ እና ማሕበራዊ ቀውስ ተዳርጎ ይገኛል» ሲሉ ለዶቼቬለ ገልፀዋል። የትግራይ መምህራን ማሕበር እንደገለፀው አስተማሪዎች የ18 ወር ውዝፍ ክፍያቸው ባለማግኘታቸው ሰላማዊ ሰልፍ ከማድረግ ውጭ በአንዳንድ አካባቢዎች ሥራ ማቆም ጀምረዋል።
የትግራይመምህራን ማሕበር የአስተማሪዎች ውዝፍ ክፍያ እንዲከፈል በተደጋጋሚ ለመንግሥት በተደራጀ መንገድ ጥያቄ ሲያቀርብ መቆየቱን ያነሱት የትግራይ መምህራን ማሕበር ምክትል ፕሬዝደንት መምህርት ንግሥቲ ጋረድ፥ ይሁንና ምላሽ ባለመሰጠቱ አስተማሪዎች በራሳቸው መንገድ የተለያየ እርምጃ መውሰድ መጀመራቸውን ገልፀዋል። የሽረ መምህራን ማሕበር ሊቀመንበሩ መምህር ተክላይ እንደሚሉት ከሆነ አስተማሪዎች ክፍያቸውን የማያገኙ ከሆነ በቀጣይ ሥራ እስከ መልቀቅ የሚደርስ እርምጃ ሊወሰድ ይችላል።
ከመምህራን በተጨማሪ ሌሎች በክልሉ ያሉ የመንግሥት ሠራተኞችም ውዝፍ ክፍያችንን አላገኘንም የሚል ቅሬታ በተደጋጋሚ ያቀርባሉ። የመንግሥት ሠራተኛው ሀብቱ ወልደሐዋርያት ይከፈላል ተብሎ ቃል የተገባው ጭምር የመንግሥት ሠራተኛው አላገኘም ነው ያሉት።
እየቀረበ ያለውን የአስተማሪዎች የመብት ጥያቄ በሀገር ደረጃ ያለው የኢትዮጵያ መምህራን ማሕበር እንደሚያውቀው ጨምረው የገለፁት መምህርት ንግሥቲ በበኩላቸው፥ የኢትዮጵያ መምህራን ማሕበርም በፌደራሉ መንግሥት ላይ ጫና ለመፍጠር መሠራት አለበት ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል። በዚሁ የመምህራን እና ሌሎች የመንግሥት ሠራተኞች የውዝፍ ደሞዝ ክፍያ ጉዳይ ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ምላሽ ለማግኘት በተደጋጋሚ ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።
ሚሊየን ኃይለ ሥላሴ
ሸዋዬ ለገሠ
እሸቴ በቀለ