1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአማራ ክልል ውጊያ ወቅታዊ መረጃ

ረቡዕ፣ ጳጉሜን 1 2015

በአማራ ክልል ሰሞኑን ብርቱ ውጊያ ሲደረግባቸው ከነበሩ አካባቢዎች መካከል በምዕራብ ጎጃም ዞን ደጋ ዳሞት መከላከያ መግባቱን የአካባቢው ነዋሪዎች ተናገሩ ። በተለያዩ አካባቢዎች በተለይ ትናንት በከባድ ጦር መሣሪያ ጭምር የታገዘ ጦርነት ተጠናክሮ መቀጠሉን የየአካባቢው ነዋሪዎች ገልጸው ነበር ።

https://p.dw.com/p/4W1SX
የፋኖ ታጣቂ-በአማራ ክልል ላሊበላ ከተማ
የፋኖ ታጣቂ-በአማራ ክልል ላሊበላ ከተማ ምስል Solan Kolli/AFP/Getty Images

በአማራ ክልል ያለው ሁኔታ ምን ይመስላል?

የአማራ ክልል ውጊያ

በአማራ ክልል ሰሞኑን ብርቱ ውጊያ ሲደረግባቸው ከነበሩ አካባቢዎች መካከል በምዕራብ ጎጃም ዞን ደጋ ዳሞት መከላከያ መግባቱን የአካባቢው ነዋሪዎች ተናገሩ ። በደጋ ዳሞት ወረዳ የተለያዩ ቀበሌዎች ውስጥ ከሰሞኑ በመከላከያ ሰራዊት እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ሲደረጉ የነበሩ ውጊያዎች በተለይ ትናንት በከባድ ጦር መሣሪያ ጭምር ታግዘው ተጠናክረው መቀጠላቸውን የየአካባቢው ነዋሪዎች ገልጸው ነበር ። ዛሬ ለዶይቸ ቬለ ከተሸሸጉበት ጫካ ውስጥ ሆነው የተናገሩ የዐይን እማኞች  መከላከያ ትናንት አመሻሹ ላይ ወደ ወረዳው አማካይ ፈረስ ቤት ሲገባ ነዋሪዎች ከተማዪቱን ለቅቀው በመውጣት ወደ ጫካ ገብቶዋል ብለዋል ። አብዛኞቹ መኖሪያ ቤቶችም ሰዎች እንደሌሉባቸው አስተያየት ሰጪዎቹ በስልክ ለዶይቸ ቬለ (DW) የተናገሩት ። ቁጥሩን በትክክል መግለጽ ባይችሉም የሰዎች ሕይወት መጥፋቱን፤ ቤን ንብረቶች ላይም ጉዳት መድረሱን ነዋሪዎቹ ተናግረዋል ።

የተለያዩ ከተሞች

እንደ ደብረ ማርቆስ፤ ደብረብርሃን፤ ባሉ የተለያዩ የአማራ ክልል ከተሞች እና አካባቢዎች ላይ ስላለው ወቅታዊ ሁኔታ መረጃ ለማሰባሰብ የኢንተርኔት መቋረጥ እና አንዳንድ ቦታዎች ላይም የመብራት መቆራረጥ የስልክ አገልግሎት ባለመኖሩ ከፍተኛ እክል መፍጠሩን ጠቁሟል ። ሆኖም ግን በአማራ ክልል ጅሩ እና በኦሮሚያ ክልል መንዲዳ መካከል ያለው የመጓጓዣ መስመር ከተቋረጠ ሰንበትበት ብሏል ። በአካባቢው ያለው ውጥረትም አለመርገቡ ተገልጿል ። በደብረ ታቦር ከተማ መረጋጋት ይታያል ቢባልም የባጃጅ እንቅስቃሴ ግን ከከተማ ክልል ውጪ እንደሌለ ተጠቁሟል።  ፍኖተ ሰላም በቅርብ ርቀት ላይ የመጓጓዣ አገልግሎት ቢኖርም፤ ከፍኖተ ሰላም ወደ ባሕርዳርም ሆነ ወደ ደብረ ማርቆስ ከተሞች መጓጓዣ አገልግሎት መቋረጡን አስተያየት ሰጪዎች ተናግረዋል ።

የፌደራል እና ክልል ምክር ቤት አባላትን ጨምሮ 53 ግለሰቦች አዋሽ አርባ መታሰራቸውን ኢሰመኮ አረጋገጠ።

በተያያዘ ዘገባ፦ በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ተጠሪ ራሚዝ አላክባሮቭ ዛሬ ባሕርዳር ከተማ ዉስጥ ከአዲሱ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ጋር መወያየታቸው ተዘግቧል ። በአዲሱ የአማራ ክልል መስተዳድር በኩልም የተለያዩ አዳዲስ የሥራ ኃላፊነቶች መሰጠቱም ተገልጿል ። 

ዓለምነው መኮንን

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ኂሩት መለሠ