1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

«ከእርዳታ አውጡን» የአማራ ክልል ተፈናቃዮች

ረቡዕ፣ ጥቅምት 13 2017

በአማራ ክልል የሚገኙ አንዳንድ ተፈናቃዮች መንግሥት በቋሚነት እንዲያቋቁማቸው አሊያም ወደ ቀደመ ቀያቸው እንዲመልሳቸው ጠየቁ። መንግሥት በበኩሉ በተፈናቃዮቹ ፍላጎት መሠረት ችግራቸውን ለመፍታት ጥናት አጠናቅቄያለሁ ይላል።

https://p.dw.com/p/4m9Rw
ተፈናቃዮች በአማራ ክልል
በአማራ ክልል የሚገኙ ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ወገኖች ከተረጂነት ለመውጣት እየጠየቁ ነው። ፎቶ ከማኅደር፤ ምስል Alemenw Mekonnen/DW

«ከእርዳታ አውጡን» የአማራ ክልል ተፈናቃዮች

መንግሥት በዘላቂነት እንዲያቋቁማቸው ተፈናቃዮች ጠየቁ

ከኦሮሚያና ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ተፈናቅለው በአማራ ክልል በተለያዩ መጠለያ ጣቢያዎች ከሦስት ዓመት በላይ ያስቆጠሩ ወገኖች በመጠለያ መቆየት እንደሰለቻቸውና መንግሥት በዘላቂነት ገቢ በሚያስገኝ ሥራ እንዲያሰማራቸው፣ አሊያም ወደ ቀደመ ቀያቸው እንዲመልሳቸው ጠይቀዋል።

«መንግሥት በዘላቂነት ያቋቁመን» ተፈናቃዮች

ይህን ያሉት አስተያየታቸውን ከሰጡን ተፈናቃዮችመካከል በሰሜን ወሎ ዞን የጃሪ መጠለያ ጣቢያ ተፈናቃይ አንዱ ናቸው። እንደ አስተያየት ሰጪው፣ ባለፉይ ሦስት ዓመታት ይህ ነው የተባለ መፍትሔ አልተሰጣቸውም። እናም ባሉበት አካባቢ ሠርተው የሚለወጡበት ሁኔታ እንዲመቻችላቸው ነው የጠየቁት፣ «የሚነግደውም እንዲነግድ፣ የሚያርሰውም እንዲያርስ፣ የመንግሥት ሥራተኛውም ወደ ሥራው እንዲመልስ ይደረግ» ይላሉ።

ወደ ቀደመው ቀየ ስለመመልስ

ተፈናቃዩ ወገን ባሉበት አካባቢ ከተረጅነት ተላቀው ለመኖር ያቀረቡት ጥያቄ የማይሆን ከሆነ ደግሞ ቀድሞ ወደ ነበሩበት አካባቢ መመለስ እንደሚፈልጉ ነው የተናገሩት። በደቡብ ወሎ ዞን ጃራ የመጠለያ ጣቢያ የሚገኘው ሌላው ተፈናቃይ በበኩሉ አብዛኛው ተፈናቃይ ወደ ቀደመ ቀየው መመለስ እንደሚፈልግ ጠቁሟል። ወይም ደግሞ ሌሎች የሥራ አማራጮች በዚሁ በአማራ ክልል ቢፈጠርላቸው መልካም እንደሚሆን ተናግሯል።

ከወለጋ ከሦስት ዓመት በፊት ተፈናቅለው በመካነ ሠላም አካባቢ በአንድ የተፈናቃይ መጠለያ ጣቢያየሚገኙ ተፈናቃይ ግን ወደ ቀደመው ቀየ መመልስ የማይታሰብ ነው ብለዋል፣ መንግሥት በአማራ ክልል ያቋቁመን ሲሉ ነው የጠየቁት።

«ወደዚያ መመለስና መንግሥት ደህንነታችን ጠብቆ ያኖረናል ማለት ከእውነት የራቀ ነው፣ እኛ ወደዚያ መመለስ አንፈልግም” ነው ያሉት። መቋቋሚያ በዚሁ በአማራ ክልል ከተሰጣቸው እንደማነኛውም ሰው ሰርተው ገቢ እንደሚያገኙ ነው ያስረዱት።

«ከእርዳታ አውጡን»

«ከእርዳታ አውጡን» ያሉት ደግሞ በሰሜን ሸዋ ዞን ደብረብርሃን ከተማ አካባቢ ከሚገኙ የተፈናቃይ መጠለያ ጣቢያዎች በአንዱ የሚገኙ ወገን ናቸው። መንግሥት በተናጠልም ይሁን በቡድን እንዲያቁቁማቸው የጠየቁት እኚህ አስተያየት ሰጪ፣«ከእርዳታ፣ ከጭቃ፣ ከፀሐይ፣ ከአረጀ ሸራ ቤት ያውጣን» ብለዋል።

በዋግህምራ የተፈናቃዮች መጠለያ
በአማራ ክልል የስደተኞች መጠለያ ከሆኑት አንዱ ፎቶ ከማኅደር ምስል Waghemra Disaster Prevention Office

«ከእርቅ በኋልም ወደ ቀያችን አልተመለስንም”» የአበርገሌ ተፈናቃይ

ቀደም ሲል በራሱበአማራ ክልል በአገው ዴሞክራሲ ንቅናቄና በመንግሥት መካክለ በነበረ ግጭት በዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር አበርገሌ ወረዳ ከሚገኝ አንድ ቀበሌ ተፈናቀልው በወረዳው ማዕከል ኒሯቅ ከተማ አካባቢ የሚገኙት ተፈናቃይም ወደ «ቀያችሁ ትመለሳላችሁ ብንባልም እስካሁን በችግር ላይ ነን» ይላሉ። ታጣቂው ቡድን ከመንግሥት ጋር እርቅ ፈጥሯል ቢባልም ተፈናቁዩ ግን ወደ ቀየው እንዳልተመለስ ነው ያስረዱት።

ተፈናቃዮችን በዘላቂነት ለማቋቋም ጥናት ስለመደረጉ

የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ፕሮግራሞች፣ ማስተባበሪያ ኮሚሽን ኮሚሽነር ዲያቆን ተስፋው ባታብል፣ ጉዞ ላይ በመሆናቸው ሰፊ ማብራሪያ ለመስጠት ቢቸገሩም የተፈናቃዮችን ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት ግን ጥናት መጠናቀቁን በአጭሩ ነግረውናል።

እሳቸው እንደገለጹት ኮሚሽነሩ፣ «ጥናት ተጠንቷል፣ የተፈናቃዮቹ አጠቃላይ አማራጮች ምንድን ናቸው? የሚለው መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር በጋራ ተጠንቷል፣ ጥናቱ ሰሞኑን ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ባሉበት ቀርቦ ወደ ተግባር ይገባል»።

በአማራ ክልል በሰው ሠራሽና በተፈጥሮ አደጋዎች ምክንያት ከሁለት ሚሊዮን በላይ የዕለት እርዳታ ፈላጊ ወገኖች መኖራችውን ከአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ፕሮግራሞች፣ ማስተባበሪያ ኮሚሽን ያገኘነው መረጃ ያሳያል።

ዓለምነው መኮንን

ሸዋዬ ለገሠ

ማንተጋፍቶት ስለሺ