ተፈናቃዮች ያቀረቡት የእርዳታ ጥሪ
ቅዳሜ፣ መስከረም 18 2017
በተለያዩ ጊዜያት ከተለያየ የኦሮሚያ ክልል የወለጋ ዞኖች በግጭት ምክንያት ተፈናቅለው አማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን በተለያዩ የአገር ውስጥ መጠለያ ካምፕ የሚገኙ ተፈናቃዮች ከሶሰርት ወራት ወዲህ የምግብ እርዳታ እየተቋረጠ ነው ሲሉ አማረሩ፡፡
ተፈናቃዮቹ መንግስት ወደ ተፈናቀሉበት ቀዬያቸው እንዲመለሱ በመጠየቅ ያንን የማይቀበል እርዳታ ሊቋረጥበት እንደሚችል አስረድቶናል ነው የሚሉት፡፡
ወደ ቀዬያቸው መመለስ ቀዳሚ ምርጫቸው ቢሆንም አሁንም ድረስ የሚያሰጋ ያሉትን የጸጥታ ይዞታውን መፍራታቸውን የሚገልጹት ተፈናቃዮቹ መንግስት ከራብ እንዲታደጋቸውም ጠይቀዋል፡፡
“ወደ ወለጋ ተመለሱ ተብለናል፤ ለናንተ በጀትም አልተበጀተም አሉን፤ ይህን ደግሞ ደቡብ ወሎ ላይ ብቻ ለሰፈሩ ተፈናቃዮች እንጂ በሰሜን ወሎ ላሉ ተፈናቃዮች እርዳታው እየቀረበ ነው ያለው”ከሆሮጉዱሩ ወለጋ ዞን አቤዶንጎሮ ወረዳ በግጭት ምክንያት ተፈናቅለው አሁን ላይ ደቡብ ወሎ ዞን ጃሬ ቁጥር 1 የተፈናቃዮች ካምፕ ውስጥ የሚገኙ የአገር ውስጥ ተፈናቃይ አስተያየት ሰጪ የተናገሩት ነው፡፡
እንደ አስተያየት ሰጪው በደቡብ ወሎ ዞን ብቻ ባሁን ወቅት 45 ሺህ ግድም ተፈናቃዮች በየተፈናቃዮቹ ካምፕ ተጠልለው ይገኛሉ፡፡ እንደ ጃሬ ቁትር አንድ ደግሞ 1500 ተፈናቃዮች በአባወራ 400 ያህል ይገኛሉ፡፡ “አምና ተመለሱ ተብለናል ያልተመለሳችሁ እንደሆነ ግን የእርዳታ እህል ማቅረብ አንችልም” ተብለናልም ነው አስተያየት ሰጪው ያሉት፡፡
ከምዕራብ ወለጋ ዞን ባቦጋምቤል ወረዳ በ2013 ዓ.ም. ተፈናቅለው ላለፉት ሶስት ዓመታት ገደማ በተፈናቃዮች ካመፑ የቆዩት ሌላም አስተያየት ሰጪ በንግድ ስራ ላይ ተሰማርተው ስድስት ቤተሰቦቻቸውን በደህና ሁኔታ ስያስተዳድሩ እንደነበር አስታውሰው አሁን ግን በሰው እጅ ላይ መውደቃቸውን ገልጸዋል፡፡ “አንድ ፈጣሪ በሰው እጅ ላይ ጥሎናል፤ ርሃብ ጠናብን” ያሉት አስተያየት ሰጪ በነፍስ ወከፍ የሚሰጥ 15 ኪሎ ግራም የእርዳታ እህልን ከተቀበሉ ሶስት ወራት መቆጠሩን ገልጸዋል፡፡
የተፈናቃዮቹን ሁኔታ እና መልሶ ማቋቋምን በተመለከተ በቅርበት እንደሚሰራ የሚገልጸው የኦሮሚያ ቡሳ-ጎኖፋ (አደጋ ስጋት ስራ አመራር) ቢሮ በኦሮሚያ ውስጥም ያሉ በአማራ ክልልም ያሉ ተፈናቃዮች እርፈዳታ አልተቋረጠም ይላል፡፡ የቢሮው ኃላፊ አቶ ሞገስ ኢዳኤ ለዶይቼ ቬለ እንደተናገሩት “አሁን የተመላሾች ቁጥር እየጨመረ ነው፡፡ አሁን ከሰኔ ወዲህ ዳታ አልሰበሰብንም እንጂ በዚያን ጊዜ እንኳ ከ12 ሺህ በላይ ተፈናቃዮች ተመልሰዋል፡፡ ሰላም ሲሻሻል በራሳቸው የተመለሱም አሉ፡፡ እርዳታ ግን በዚህም ሆነ በዚያ አልተቋረጠም” ብለዋል፡፡
ያም ሆኖ ቁጥራቸው እጅግ ከፍተኛ የሆነ ተፈናቃዮችን ወደ ቀዬያቸው የመመለስ እና የማቋቋም ስራ ገና ይቀራል ነው ያሉት፡፡ አሁን ላይ ክረምቱ እንደወጣም ተፈናቃዮችን ወደ ቀዬያቸውና ነባሩ ኑሮያቸው የመመለሱ ተግባር ይቀጥላል ሲሉም ቀጣዩን እቅድ ገልጸዋል፡፡ ተፈናቃዮቹ ግን በዚህ ላይ ስጋት አላቸው፤ “እኛ እኮ ወደ ቀዬያችን መመለሱን አንጠላም፤ በዋናነት የምንፈልገውም እሱን ነው፡፡ ግን ከዚህ በፊት የነበረው ግጭት አለመረጋጋቱ ቀንሷል የሚባለው እንደየቦታው ሁኔታ ነው፡፡ አንዳንድ ቦታ ላይ አሁንም ስጋቱ መኖሩ ነው ያሰጋን” ብለዋል፡፡
የኦሮሚያ ክልል ቡሳ ጎኖፋ ቢሮ ኃላፊው አቶ ሞገስ ግን በዚህ አይስማሙም፤ “ተፈናቃዮች ወደ ቀዬያቸው እንዳይመለሱ የፖለቲካ ጫና የሚያደርጉ አሉ፡፡ ተፈናቃዮች የተፈናቀሉበት ኦሮሚያ ክልል አሁን ላይ ወደ ሰላም እየተመለሰ ነው፡፡ አሁን በዛ ላይ ነው የምንሰራው” ብለዋል፡፡
ሥዩም ጌቱ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር