ምሥራቅ ወለጋ፣ ኪራሙ ወረዳ የመንግሥት ሠራተኞች መገደልና ተጨማሪ ሥጋት
ማክሰኞ፣ መስከረም 7 2017
በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ወለጋ ዞን ኪረሙ ወረዳ ታጣቂዎች በከፈቱት ተኩስ ሁለት የመንግስት ሰራተኞች ተገደሉ፡፡አንድ ቆሰለ። ሠራተኞቹ የተገደሉት በሞተር ሳይክል በመጓዝ ላይ እያሉ ድንገት በጥይት ተደብድበዉ ነው ተብሏል፡፡ሠራተኞቹ በቅርቡ ኦሮሚያ ክልል ከፊል የወረዳ ሰራተኞችና አመራሮች ወደ ቀበሌ እንዲመደቡ በዘረጋው አዲስ መዋቅር መሰረት ባለፈዉ ቅዳሜ ከወረዳው ከተማ ኪረሙ ወደተመደቡበት ቀበሌ በመጓዝ ላይ ነበሩ። የሠራተኞቹ መገደል ወትሮም ሰላም በራቀዉ በምሥራቅ ወለጋ ተጨማሪ ሥጋት አስከትሏል።
የሰራተኞቹ ግድያ እና ያጠላው ስጋት
ሶስቱን የመንግስት ሰራተኞች በስም ጠቅሰው አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡ የአይን እማኝ ሰራተኞቹ የተገደሉት ወደ ተመደቡበት ቀበሌ በሞተር በመጓዝ ላይ ሳሉ ነው ብለዋል፡፡ ለደህንነታቸው ስባል ስሜ ይቆይ ያሉት አስተያየት ሰጪው ሁለቱ በደረሰባቸው ጥቃት ህይወታቸው ስያልፍ አንዱ በህክምና ላይ ናቸውም ብለዋል፡፡ “ጥቃቱ የተወሰደው ከወረዳ ወደ ቀበሌ ስወርዱ በነበሩ አመራሮች ላይ ነው” ያሉት አስተያየት ሰጪው የጥቃቱ ሰለባ የሆኑት አመራሮቹም “ዓላምረው ረታ፣ አክሊሉ ፍቃዱ እና መርጋ ዓለሙ” ናቸው ብለዋል፡፡ አስተያየት ሰጪው ጥቃቱ የደረሰባቸው ሰራተኞቹ ሁለቱ ስሞቱ አንዱ ክፉኛ ቆስለው በህክምና እየተረዱ መሆኑን አስረድተዋልም፡፡ ሰራተኞቹ ከኪረሙ ወረዳ ከተማ ተነስተው 15 ኪ.ሜ ግድም ርቀት ላይ ወረምትገኘው ስሬዶሮ ወደምትባል አነስተኛ ከተማ በመጓዝ ላይ ነበሩ የሚሉት አስተያየት ሰጪው መዳረሻቸው ጋ ሳይደርሱ በአከባቢው በሚንቀሳቀሱ “ፋኖ” ያሏቸው ታጠቂዎች ጥቃቱ እንደተፈጸመባቸው አመልክተዋል፡፡
አስተያየት ሰጪው አክለውም፤ “በአንድ ሞተር በመጓዝ ላይ ከነበሩት ሶስቱ የመንግስት ሰራተኞች ሁለቱ መሳሪያ ታጥቀው የነበረ ቢሆንም ጥቃቱን የፈጸሙ ታጣቂዎች ጥቃቱን ካደረሱ በኋላ መሳሪያዎቹን አስፈትተው ይዘው መሄዳቸውንም” አክለው ገልጸዋል፡፡
ኪረሙ እና አጎራባች ወረዳዎች ለዳግም አለመረጋጋት እየተዳረጉ ይሆን?
ላለፈው አንድ ዓመት የተረጋጋ መስሎ ከገጠርወደ ከተማ የተሰደዱ አርሶአደር ተፈናቃዮችንም ወደ ቀዬያቸው መመለስ በተጀመረበት ኪረሙ ወረዳ አሁን አሁን ግጭቶች የማገርሸት አዝማሚያ እያሳዩ ነው የሚሉት አስተያየት ሰጪው የአከባቢው ነዋሪ፤ ሰራተኞቹ ይጓዙበት በነበረው ስሬዶሮ በምትባል አነስተኛ ከተማ በቅርቡም ሰዎች መገደላቸውን አንስተዋል፡፡ “ከሁለት ሳምንት በፊትም በዚያው ስሬዶሮ ከተማ ውስጥ በላቸው ዳኙ እና መርጋ አመንቴ እና ረጋሳ ጎዶ የሚባሉ ግለሰቦች ተገድለዋል” ብለዋል፡፡ ተመሳሳይ ጥቃቶች ባለፉት ሁለት ሳምንታት መደረጉን ያነሱት አስተያየት ሰጪው በኪረሙ ወረዳ ታጣቂዎቹ በስፋት ይንቀሳቀሱበታል ካሉት ሀሮ አከባቢ በመነሳት በአገምሳ እና አከባቢው ሰዎች ላይ ጥቃት የማድረስ እና ከብቶችን የመዝረፍ ድርጊቶች ተፈጽሟል ነው ያሉት፡፡
መረጋጋት ታይቶበት በነበረው የኪረሙ ወረዳ ተፈናቃዮች በስፋት ወደ ቀዬያቸው መመለሳቸው ተነግሮ የነበረ ብሆንም አሁን አሁን መልሶ እየገረሸ ባለው የጸጽታ ሁኔታ የነዋሪዎች ደህንነት ስጋት ላይ ወድቋልም ነው የተባለው፡፡ “ብያንስ ወደ አባይ ባይወርድም ላይ ላዩ ታርሶ ነበር፡፡ አሁን ግን አዲስ ጥቃት ነው እየተጀመረ ያለውና ተከታትሎ እርምጃ የመውሰድ ተግባርም ብዙ አይታይም” ያሉት አስተያየት ሰጪው በከተማም ብሆን ነዋሪዎች ከደህንነት ስጋት ነጻ አልሆኑም ሲሉ አመልክተዋል፡፡
ዶይቼ ቬለ ስለአከባቢው አሁናዊ የጸጥታ ይዞታ እና ስለተፈጸመው ጥቃት ከወረዳው አስተዳዳሪ አቶ ብርሃኑ ፍቃዱ ለመጠየቅ ጥረት ብያደርግም ስብሰባ ላይ መሆናቸውን ገልጸው ከሰዓታት ቆይታ በኋላም ብደወልላቸው ስልካቸው አይነሳም፡፡ እንዲሁም ከወረዳው ጸጥታ መምሪያ ኃላፊ እና ከምስራቅ ወለጋ ምክትል ዋና አስተዳዳሪም መረጃውን ለማግኘት የተደረገው ጥረት አልሰመረም፡፡
የኦሮሚያ ክልል አዲስ የቀበሌ ደረጃ መዋቅር ለምን?
“መተዳደርም፤ ማስተዳደርም ቀበሌ ነው” በሚል መርህ በኦሮሚያ ክልል ወደ ቀበሌ ደረጃ የወረደው የመንግስት መዋቅር፤ ትልቅ ስርዓታዊ ለውጥ የሚያመጣ ብባልለትም አተገባበሩ ላይ ጥያቄ ያነሱ በርካታ ሰራተኞች ናቸው፡፡ አደረጃጀቱን ተከትሎ እየተፈጸሙ ባሉ የሲቪል ሰርቫንቱ አመዳደብ ላይ በቅርቡ ከሰሜን ሸዋ ዞን አስተያየታቸውን የሰጡን ሰራተኛ በተለይም ከደህንነት ጋር በተያየዘ ሃሳባቸውን አጋርተውን ነበር፡፡ አስተያየት ሰጪው አዲሱ የቀበሌ መዋቅር አለው የተባለውን እምቅ አቅም አይክዱትም፡፡ “ማንም ተቀብሎ ልሰራበት የሚገባው መመሪያ እንደሆነም ነው የማምነው” ይላሉ፡፡ ነገር ግን ቅሬታው ያለው ከወዲህ ነው ይላሉ አሰርተያየት ሰጪው የመንግስት ሰራተኛ፤ የጸጥታው ሁኔታ በብዙ ቀበሌ ከባድ ነው፡፡ እኔ አሁን እስካሁን ከየትኛውም ፖለቲካ ገለልተኛ ነኝ፡፡ በሙያተኝነት ነው ሳገለግል የቆየሁት፡፡ የአመራር ክህሎትም የለኝም፡፡ የውትድርና ስልጠናም አልተሰጠኝም፡፡ እንዴት ነው አስቸጋሪ የጸጥታ ሁኔታ ባለበት ላይ የአንድ ቀበሌ አስተተዳዳሪ ሁን የሚል ግዴታ የሚሰጠኝ” ሲሉ ጥያቄ አነሱ፡፡
ከአዲሱ የቀበሌ መዋቅር አወቃቀር ጋር ተያይዞ ሰራተኞቹ እንደ ስጋት ያነሱት ሃሳቦች ላይ ለክልሉ ፐብሊክ ሰርቪስ ቢሮ ኃላፊ እና ምክትላቸው ብንደውልም ጥረታችን አልሰመረም፡፡
የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት የወረዳዎች እና ቀበሌዎች ሪፎርም በሚል ያዘጋጀው ሰነድ በሶስተኛ አንቀጹ ላይ የዚህ መዋቅር ዓላማ በቀበሌ ደረጃ ጠንካራ መንግስት በማዋቀር የህብረተሰቡን የመልማት፣ የሰላምና ጸጥታ ብሎም የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ምላሽ መስጠት ነው ይላል፡፡ “ህገመንግስትን መሰረት ያደረገ ነው” የተባለው አደረጃጀቱ ሶስቱ የመንግስት መዋቅሮችም እንደሚኖሩትና የቀበሌ አስተዳዳሪን ጨምሮ ብያንስ ሰባት የአመራር እርከኖች ያሉት እንደሆነ ነው የተገለጸው፡፡
ስዩም ጌቱ
ፀሐይ ጫኔ