1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የትግራይ ጦርነት ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸዉ መመለስ ጀመሩ

ሰኞ፣ ሰኔ 24 2016

በተለያዩ የትግራይ ከተሞች በሚገኙ ግዚያዊ መጠልያዎች አድርገው ከነበሩ ተፈናቃዮች መካከል የተወሰኑት፥ ካለፈው ቅዳሜ ጀምሮ ወደቀዬአቸው መመለስ ጀምረዋል። ተፈናቃዮች ወደቀዬአቸው መመለስ መጀመራቸው በበርካቶች ዘንድ ተስፋ የፈጠረ ቢሆንም፥ የፀጥታና ድህነት ስጋቶች ትኩረት እንዲሰጣቸው ተመላሾቹ ይጠይቃሉ።

https://p.dw.com/p/4hkGI
የትግራይ ጦርነት ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸዉ መመለስ ጀመሩ
የትግራይ ጦርነት ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸዉ መመለስ ጀመሩምስል Million Haileselasie/DW

የትግራይ ክልልና ኢሰመኮን ያወዛገበው ዓመታዊ ዘገባ

የትግራይ ጦርነት ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸዉ መመለስ ጀመሩ

በጦርነቱ ምክንያት ተፈናቅለው በመጠልያዎች የነበሩ የፀለምቲ አካባቢ ነዋሪዎች ወደቀዬአቸው እየተመለሱ መሆኑ ተገለፀ። ተፈናቃዮች ወደቀዬአቸው መመለስ መጀመራቸው በበርካቶች ዘንድ ተስፋ የፈጠረ ቢሆንም፥ የፀጥታ እና ድህነት ስጋቶች ትኩረት እንዲሰጣቸው ተመላሾቹ ይጠይቃሉ።

ከጦርነቱ ጅማሮ በኃላ ከቀዬአቸው የተፈናቀሉ እና ኑሮአቸው ለዓመታት በተለያዩ የትግራይ ከተሞች በሚገኙ ግዚያዊ መጠልያዎች አድርገው ከቆዩት መካከል የተወሰኑት፥ ካለፈው ቅዳሜ ጀምሮ ወደቀዬአቸው መመለስ ጀምረዋል። የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት እና የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ካደረጉት ውይይት በኃላ ከቅዳሜ ጀምሮ መመለስ የጀመሩ ተፈናቃዮች፥ በአማራ ክልል በኩል የይገባኛል ጥያቄ ከሚነሳበት የትግራይ ሰሜን ምዕራብ ዞን ፀገዴ ወረዳ ከጦርነቱ ጅማሮ በኃላ የተፈናቀሉት ናቸው። ከተመላሾቹ እንደተረዳነው በአካባቢው በአማራ ክልል በኩል ተቋቁሞ የነበረው አስተዳደር መፍረሱ የገለፁልን ሲሆን ሙሉ በሙሉ ባይባልም የነበረው ታጣቂም ከአካባቢው መውጣቱ፣ መከላከያ በዋነኝነት የፀጥታ ስራ እየከወነ መሆኑ ገልፀዋል። ባለው ቅዳሜ ከእንዳባጉና የተፈናቃዮች መጠልያ ተነስተው ወደ ቀዬአቸው ፀለምቲ ወረዳ ማይዓይኒ የተባለ አካባቢ የተመለሱት ያነጋገርናቸው አቶ መልካሙ ዘውደ ከዓመታት አስከፊ መፈናቀል በኃላ የመመለስ ዕድል ማግኘታቸው ደስታ ፈጥሮባቸውል።

አቶ መልካሙ "ከተመለስን 48 ሰዓታት አድርገናል። ሁኔታዎች እያየን ነው። ወደቤታችን መመለሳችን ደስታ ፈጥሮብናል። በመጠልያ ለዓመታት መጥፎ ሁኔታ ላይ ነበር የነበርነው። አሁንም ቢሆን ተመለስን እንጂ በእጃጅን የያዝነው ነገር የለም፥ መፈናቀሉ ከባድ የኢኮኖሚ ቀውስ ነው የፈጠረብን" ብለዋል። ሌላው ያነጋገርናና ወደቀዬአቸው ፀለምቲ ወረዳ የተመለሱ ላለፉት ሶስት ዓመታት በሽረ መጠልያ የቆዩት አቶ ሙላው አለማየሁ በበኩላቸው ባለፈው ቅዳሜ በመከላከያ ታጅበው ወደቤታቸው መግባቻቸው አንስተዋል።

እንዳነጋገራቸው ተመላሽ ምስክርነት ቤታቸው ሙሉ በሙሉ ተዘርፎ፣ ጣርያው ጭምር ተነቅሎ የቆያቸው ሲሆን፥ በዚህ ሁኔታም ቢሆን መመለሳቸው መልካም መሆኑ፣ በቀጣይ አስተማማኝ የፀጥታ ሁኔታ ይኖራል ብለው እንደሚገምቱ፣ ሕጋዊ ሲቪል አስተዳደር ስራ ሊጀምርም እንደሚጠብቁ  ይገልፃል። የፀጥታ ሁኔታ አስተማማኝነት ለመገምገም ቤተሰቦቻቸው እስካሁን ወደቀድሞ ቀዬአቸው እንዳላስመጡ ተመላሾቹ ጨምረው ገልፀውልናል።

የትግራይ ጦርነት ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸዉ መመለስ ጀመሩ
የትግራይ ጦርነት ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸዉ መመለስ ጀመሩምስል Million Haileselassie/DW

ሌላው ተመላሽ መምህር መልካሙ፣ የፀጥታ ሁኔታ እንዲሻሻል መሰራት አለበት የሚሉ ሲሆን፥ ከዚህ ቀደም ያፈናቀሉ እና የተለያየ በደል ሲፈፅሙ የነበሩ አካላት አሁንም በአካባቢው መኖራቸው በስጋትነት ያነሳሉ። "አስተዳደሩ ፈርሷል ነው የሚባለው። ግን ደግሞ ሰዎቹ አሉ። እንድንፈናቀል ያደረጉ፣ የተለያየ በደል ያደረሱ ሰዎች ትላንት በአካል አይተናቸዋል። በአጠቃላይ ሁሉ ነገር ሰላም ነው፣ ስጋት የለም ማለት አይቻልም። ግን በተቻለ መጠን ደህና የተረጋጋ ይሆናል ብለን ተስፋ ማድረጋችን አልቀረም" ብለዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ከትግራይ ምዕራባዊ ዞን የተፈናቀሉ ዜጎች አሁንም ወደቀዬአቸው ሊመለሱ ይጠብቃሉ። የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት አቶ ጌታቸው ረዳ ትላንት በማሕበራዊ የትስስር ገፃቸው ባስተላለፉት መልእክት በሰላማዊ መንገድ ሁሉም ለህልውናችን የሚያስፈልጉ ተግባራት እንከውናለን ብለዋል።

ሚሊዮን ኃይለሥላሴ

አዜብ ታደሰ

ዮኃንስ ገብረግዚአብሔር