1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የትግራይ ጦርነት ተፈናቃዮች መንግሥት ወደ ቀያቸዉ እንዲመልሳቸዉ ጠየቁ

ሰኞ፣ ሰኔ 17 2016

በትግራይ የጦርነት ተፈናቃዮች በመቐለ፣ ሽረ፣ አክሱም እና ዓዲግራትን ጨምሮ በሌሎች ከተሞች ባደረጉት ሰልፍ መንግስት ወደቀያቸው እንዲመልሳቸው ጠየቁ። ሰልፈኞቹ በተገባላቸው ቃል መሰረት እስከ ሰኔ 30 ድረስ እንዲመለሱ ጠይቀዋል። የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ተፈናቃዮችን ለመመለስ ከፌደራል መንግስቱ ጋር በመግባባት እየተሰራ መሆኑን ገልጿል።

https://p.dw.com/p/4hRS3
የትግራይ ጦርነት ተፈናቃዮች ወደ ቦታችን እንመለስ ጥሪ
የትግራይ ጦርነት ተፈናቃዮች ወደ ቦታችን እንመለስ ጥሪ ምስል Million Hailesilassie/DW

የትግራይ ጦርነት ተፈናቃዮች መንግሥት ወደ ቀያቸዉ እንዲመልሳቸዉ ጠየቁ 

በትግራይ የሚገኙ የጦርነቱ ተፈናቃዮች ትላንት በመቐለ፣ ሽረ፣ አክሱም እና ዓዲግራትን ጨምሮ በሌሎች ከተሞች ባደረጉት ሰልፍ መንግስት ወደቀያቸው እንዲመልሳቸው ጠየቁ። ሰልፈኞቹ በተገባላቸው ቃል መሰረት እስከ ሰኔ 30 ድረስ ወደ ቀያቸው እንዲመልሳቸው ጥሪ አቅርበዋል። የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት ጌታቸው ረዳ ተፈናቃዮች ለመመለስ ከፌደራል መንግስቱ ጋር በመግባባት እየተሰራ መሆኑና በአጭር ግዜ ውስጥ ተፈናቃዮቹ እንደሚመለሱ ተናግረዋል።

ከጦርነቱ ጅማሮ በኃላ ከምዕራብ ትግራይ ዞን የተለያዩ አካባቢዎች፣ ከሰሜን ምዕራብ ዞን፣ ከኤርትራ ጋር ከሚዋሰኑ ዛላንበሳ እና ኢሮብ እንዲሁም ሌሎች አካባቢዎች የተፈናቀሉ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ትላንት በተለያዩ የትግራይ ከተሞች መንግስት ወደቀዬአቸው እንዲመልሳቸው የሚጠይቅ ሰልፍ አካሂደዋል። መቐለ፣ ሽረ፣ ሸራሮ፣ አክሱም፣ ዓዲግራት እና ዓብይ ዓዲ ትላንት የተፈናቃዮች ሰልፍ ከተካሄደባቸው ከተሞች መካከል ናቸው። ሰልፈኞች በዋነኝነት መንግስት ድህንነታቸው በተጠበቀ መንገድ ወደቀዬአቸው እንዲመልሳቸው የጠየቁ ሲሆን፣ እንደሚመለሱ የተገባላቸው ቃል ተከብሮ እንዲሁም የፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት ተፈፃሚ ተደርጎ ችግራቸው እልባት እንዲያገኝ መልእክት አስተላልፈዋል። በመቐለ በተካሄደው ሰልፍ ያነጋገርናቸው በጦርነቱ ጀማሮ 2013 ዓመተምህረት ከማይካድራ ተፈናቅለው አሁን ላይ በመቐለ በሚገኝ መጠልያ እየኖሩ ያሉት ተፈናቃይ አቶ ሕሉፍ በርሃ "ጥያቄአችን ወደቤታችን መንግስት እንዲመልሰን ነው። ወደቀዬአችን መልሱን ሰርተን እንበላለን" ሲሉ ተናግረዋል።

የትግራይ ጦርነት ተፈናቃዮች ወደ ቦታችን እንመለስ ጥሪ
የትግራይ ጦርነት ተፈናቃዮች ወደ ቦታችን እንመለስ ጥሪ ምስል Million Hailesilassie/DW

ሌላዋ የሰልፉ ተሳታፊ እና ከሑመራ ከነህፃናት ልጆችዋ ጋር ተፈናቅላ በሰብዓ ካሬ መጠልያ ያለችው እናት አበባ ተክለሃይማኖት በበኩልዋ አራተኛ ክረምት በተፈናቃይ መጠልያ ከመኖር መንግስት እንዲታደጋቸው ትጠይቃለች።

በሌሎች የትግራይ ከተሞችም እንዲሁ ትመለሳላችሁ ተብሎ በተነገራቸው የግዜ ሰሌዳ መሰረት ሁሉም ተፈናቃይ ወደቀዬው እንዲመለስ ሰልፈኞቹ ጠይቀዋል። ተፈናቃዮቹ በሰልፍ ላቀረቡት ጥያቄ ምላሽ የሰጡት የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት ጌታቸው ረዳ ተፈናቃዮቹ ለመመለስ ከፌደራል መንግስቱ ጋር መግባት መደረሱ፣ በአማራ ክልል በኩል የነበረ ማስተጓገልም እየተቀረፈ መሆኑ ተናግረዋል።

አቶ ጌታቸው ረዳ "በሌሎች አካባቢዎች ተፈናቃዮች የመመለስ ስራ ፈጥነን እንጀምራለን።የምዕራብ ትግራይ ተፈናቃዮችም ቢሆን በሁለቱ አካባቢዎች ያየናቸው ሁኔታዎች ግምት ውስጥ አስገብተን፣ በአጭር ግዜ ተፈናቃዮች መመለስ እንጀምራለን። ዋናው ነገር በፌደራል መንግስት በኩል በአካባቢው ቤታቸው ንብረታቸው የተነጠቁ ሰዎች የመለየት፣ ከምንም በላይ ደግሞ እዛ ካለው ህዝብ ጋር ወደ ጠብ ለማስገባት ያለመ የጠላት አሻጥር ስላለ፥ ዘላቂነት ባለው መንገድ ይህ ለመፍታት የሚያስችል ግንኙነት እና መግባባት ከፌደራል መንግስት ጋር አለን። በአማራ ክልል መንግስት በኩልም ቢሆን የተወሰነ እግር መጉተት የነበረ ቢሆንም አሁን ላይ የህዝብ ችግር ከመፍታት አልፎ በሐይል የሚቀየር፣ በሐይል የሚነጠቅ መሬት እንደሌለ፣ ይህ ይዞም ለረዥም ግዜ የመቆየት እንደማይቻል የመረዳት ዝንባሌ አለ። ስለዚ ይህ እንዲያዘልቅላቸው በተቻለን መንገድ እናግዛለን" ብለዋል።

የትግራይ ጦርነት ተፈናቃዮች ወደ ቦታችን እንመለስ ጥሪ
የትግራይ ጦርነት ተፈናቃዮች ወደ ቦታችን እንመለስ ጥሪ ምስል Million Hailesilassie/DW

የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር የራያ እና ፀለምቲ ተፈናቃዮች እስካለፈው ግንቦት 30 ድረስ፣ የምዕራብ ትግራይ ተፈናቃዮች እስከ መጪው ሰኔ 30 ድረስ ለመመለስ እየሰራ መሆኑ ገልፆ የነበረ ቢሆንም እስካሁን ተጨባጭ እንቅስቃሴ አለመታየቱ በማንሳት ተፈናቃዮች ይተቻሉ።

 

ሚሊዮን ኃይለሥላሴ 

አዜብ ታደሰ 

ነጋሽ መሐመድ