1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቀጠለው በመሬት መንሸራተት የጠፉ ሰዎችን የመፈለግ ሂደት

ዓርብ፣ ሐምሌ 19 2016

በጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ በመሬት መንሸራተት የጠፉ ሰዎችን የመፈለጉ ሂደት ዛሬ ለአምስተኛ ቀን ሲካሄድ ውሏል ፡፡፡ የቤተሰብ አባላቸውን አስክሬን አግኝተው መቅበራቸውን ለዶቼ ቬለ የተናገሩ አንድ የኬንቾ ሻቻ መንደር ነዋሪ ሌሎች ግን አሁንም ፍለጋ ላይ ናቸው ብለዋል ።

https://p.dw.com/p/4in83
Äthiopien Rettungseinsatz und humanitäre Hilfe in der Gofa-Zone
ምስል Gofa Zone Government Communication Affairs Department

የቀጠለው በመሬት መንሸራተት ሟቾችን የመፈለግ ስራ

በጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ በመሬት መንሸራተት የጠፉ ሰዎችን የመፈለጉ ሂደት ዛሬ ለአምስተኛ ቀን ሲካሄድ ውሏል ፡፡፡  የቤተሰብ አባላቸውን አስክሬን አግኝተው መቅበራቸውን ለዶቼ ቬለ የተናገሩ አንድ የኬንቾ ሻቻ መንደር ነዋሪ  ሌሎች ግን አሁንም ፍለጋ ላይ ናቸው ብለዋል  ፡፡

የአየሩ ሁኔታና የመንገድ አለመኖር የቀሪ ሰዎችን ፍለጋ አስቸጋሪ እንዳደረገው  በጎፋ ዞን የገዜ ጎፋ ወረዳ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ጽህፈት ቤት አስታውቋል ፡፡ አሁን ላይ የተጎጂ ቤተሰቦችን የመጽናናትና የአስቸኳይ ድጋፍ አቅርቦት ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ እንደሚገኝ የጽህፈት ቤት ሃላፊው አቶ የዓለም መሪነህ አስፋው ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል ፡፡

  የጎፋው ዘግናኝ የተፈጥሮ አደጋ

 

የጎፋ አደጋ እና የቀጠለው የተጎጂዎች ፍለጋ

በጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ ባለፈው ሰኞ የደረሰው የመሬት መንሸራተት አደጋ በናዳው ተቀብረው የሚገኙ ቀሪ ሰዎችን  የማፈላለጉ ሥራ ዛሬም ለአምስተኛ ቀን እንደቀጠለ ይገኛል ፡፡   የቤተሰብ አባላቸውን አስክሬን አግኝተው መቅበራቸውን ለዶቼ ቬለ የተናገሩ የኬንቾ ሻቻ መንደር ነዋሪ በዛብህ በላይነህ ሌሎች ግን አሁንም ፍለጋ ላይ ናቸው ብለዋል  ፡፡

ከዚህ በኋላ ሰዎችን በህይወት የማግኘት ተስፋ አለመኖሩን የጠቀሱት በዛብህ “ ነገር ግን ሰዎች አሁንም አይናቸውን በአደጋው ሥፍራ አድርገው እየጠበቁ ይገኛሉ ፡፡ ትናንት የተወሰነ ቤተሰቦች አስክሬን አግኝተዋል በመቅበራቸው ራሳቸውን እንደ ዕድለኛ ሲቆጥሩ ነበር ፡፡ አሁንም የቤተሰብ አባላቸውን ያላገኙ ተደራቢ  ሀዘን እንደሆነባቸው ይገኛሉ ፡፡ ከዛሬ ነገ እናገኛለን በሚል ተስፋ እየጠበቁ ይገኛሉ “ ብለዋል ፡፡

ለጎፋ የአደጋ ሰለባ ቤተሰቦች የሚደረገው የርዳታ ሁኔታ

የድህፈት ቤቱ ሥጋትና የተጎጂዎች ድጋፍ

በሠኞው አደጋ የሞቱ ሰዎች ቁጥር እስከአሁን 226 ሥለመሆኑ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ባለሥልጣናት እየገለጹ ይገኛሉ ፡፡የተባበሩት መንግሥት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ግን የሟቾቹ ቁጥር እስከ 500 ሊደርስ ይችላል ሲል ትናንት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል ፡፡

የጎፋ የተፈጥሮ አደጋ ተጎጂዎች
በሠኞው አደጋ የሞቱ ሰዎች ቁጥር እስከአሁን 226 ሥለመሆኑ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ባለሥልጣናት እየገለጹ ይገኛሉ ፡ምስል MICHELE SPATARI/AFP/ Getty Image

 

በአካባባው የዝናቡ ሁኔታ በመቀጠሉና ተሽከርካሪ መንገድ አለመኖር የቀሪ ሰዎችን ፍለጋ አስቸጋሪ እንዳደረገው በጎፋ ዞን የገዜ ጎፋ ወረዳ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ጽህፈት ቤት አስታውቋል ፡፡ አሁን ላይ የተጎጂ ቤተሰቦችን የማጽናናትና የአስቸኳይ ድጋፍ አቅርቦት ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ እንደሚገኝ የጽህፈት ቤቱ ሃላፊ አቶ የዓለም መሪነህ አስፋው ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል ፡፡

«በጎፋ ወረዳው የመሬት መንሸራተት አደጋ ከ2 ሺህ በላይ ሰዎች የአስቸኳይ ግዜ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል።»

ተጨማሪ አደጋን የመከላከል ሥራ

በቀበሌው ተጨማሪ አደጋ እንዳይከሰት የጥንቃቄ ሥራ በመከናወን ላይ እንደሚገኝ በጎፋ ዞን የገዜ ጎፋ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ጽህፈት ቤት አስታውቋል ፡፡ በአሁኑወቅት የመሬት ባለሙያዎች በሥፍራው ተገኝተው የመሬቱን አቀማመጥና የአፈሩን ሁኔታ መመርመራቸውን የጠቀሱት አቶ የዓለም መሪነህ “ ባለሙያዎቹ ባቀረቡት ምክረ ሀሳብ መሠረት ቀሪ ነዋሪዎችን የማንሳት ሥራ ተጀምሯል ፡፡ በአጠቃላይ 508 አባወራዎች ወደ ተለዋጭ ጊዜያዊ መጠለያ ይዛወራሉ ፡፡ በቀበሌው በባለሙያዎች በተመረጠ ሜዳማ ሥፍራ ላይ ጊዜያዊ የድንኳን መጠለያዎች  ተዘጋጅተዋል  “ ብለዋል ፡፡

የጎፋ የተፈጥሮ አደጋ ተጎጂዎች
በቀበሌው ተጨማሪ አደጋ እንዳይከሰት የጥንቃቄ ሥራ በመከናወን ላይ እንደሚገኝ በጎፋ ዞን የገዜ ጎፋ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ጽህፈት ቤት አስታውቋል ፡፡ምስል MICHELE SPATARI/AFP

የጎፋ ነዋሪዎች የምግብ ርዳታ ጥያቄ

ቀጣይ ድጋፍ

በአሁኑወቅት የክልልና የፌዴራል ከፍተኛ መንግሥት የሥራ ሃላፊዎች የአደጋው ተጎጂ ቤተሰቦችን እያፅናኑ ፤ የተለያዩ ድጋፎችንም እያደረጉ ይገኛሉ ፡፡  የጎፋ አካባቢ ተወላጅና በአደጋው የቅርብ ዘመዶቻቸውን እንዳጡ የጠቀሱት በኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ዋና ተጠሪ ዶክተር ተስፋዬ ቤልጂጌ “ አደጋው በሁሉም ቤተሰብ ውስጥ የገባ አሳዛኝ ክስተት ነው ፡፡ እኔ ሦስት የአባቴ አጎት ልጆች እዚህ ሥፍራ ተውጠው ቀርተዋል ፡፡ አሁን መንግስት በሦስት መንገድ እየሠራ ይገኛል ፡፡ ከፌዴራል ፣ ከክልል እና ከዞን አስተዳደር ጋር ተቀናጅተው ለተጎጂዎች ፈጣን ድጋፍ እያደረጉ ይገኛሉ “ ብለዋል ፡፡

ሸዋንግዛው ወጋየሁ

እሸቴ በቀለ

ፀሀይ ጫኔ