1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

«በጎፋው የመሬት መንሸራተት አደጋ ከ2 ሺህ በላይ ሰዎች የአስቸኳይ ግዜ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል።»

ረቡዕ፣ ሐምሌ 17 2016

በመሬት መንሸራተት አደጋው ህይወታቸው ያለፈ ቀሪ ሰዎችን የመፈለጉ ሂደት አሁንም መቀጠሉን የገዜ ጎፋ ወረዳው ባለሥልጣናት አስታውቀዋል ፡፡ በአሁኑ ወቅትም ከ40 በላይ የሚሆኑ ሰዎች ከአፈር በታች ይገኛሉ የሚል ጥርጣሬ መኖሩን የወረዳ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ማስረሻ ማንአየ ለዶቼ ቬለ ገልጸዋል ፡፡

https://p.dw.com/p/4igkV
የጎፋ ወረዳ ነዋሪዎች በአስከሬን ፍለጋ ላይ
የጎፋ ወረዳ ነዋሪዎች በአስከሬን ፍለጋ ላይ ምስል Gofa Zone Government Communication Affairs Department

«በጎፋው የመሬት መንሸራተት አደጋ ከ2 ሺህ በላይ ሰዎች የአስቸኳይ ግዜ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል።»

ጎፋ ከአደጋው ማግሥት  

አቶ ዘለቀ ዶሳ በጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ ከትናንት በስቲያ ሰኞ በደረሰው የመሬት መንሸራተት አደጋ አምስት የባለቤታቸው ቤተሰብ አባላትን መቅበራቸውን ይናገራሉ ፡፡  በቀበሌው የደረሰው አደጋ ቁጥሩ ቢለያይም እያንዳንዱን ቤት ለከፋ ሀዘን መዳረጉን ነው ተጎጂው ለዶቹ ቬለ የተናገሩት ፡፡አደጋው አስከፊና  በቃላት ለመግለጽ እንደሚከብድ የተናገሩት አቶ ዘለቀ “ የቤተሰብ አባሎቻቸውን ከአፈር ናዳ ሥር ለማግኘት ያለውን ፈተና ከባድና የሚጨንቅ ነው ፡፡ ከተጫነው ናዳ ሥር የወጡ ሟቾች በጭቃ የተለወሱ ናቸው ፡፡ ሰዎች የቤተሰብ አባሎቻቸውን የሚለዩት የአስክሬኖችን ፊት በማጠብ ነው ፡፡ 16 የቤተሰብ አባላቱን ያጣ ፣ ስምንት ልጆቿን ያጣች እናት አለች ፣ ቤተሰቦቹ አልቀውበት ብቻው የቀረ ህጻን አለ ፡፡ ሁኔታ ዘግናኝና አስጨናቂ ነው “ ብለዋል ፡፡የጎፋው ዘግናኝ የተፈጥሮ አደጋ

አስቸኳይ ድጋፍ

በመሬት መንሸራተት አደጋው ህይወታቸው ያለፈ ቀሪ ሰዎችን  የመፈለጉ  ሂደት አሁንም መቀጠሉን የገዜ ጎፋ ወረዳው ባለሥልጣናት አስታውቀዋል ፡፡ በአሁኑ ወቅትም ከ40 በላይ የሚሆኑ ሰዎች ከአፈር በታች ይገኛሉ የሚል ጥርጣሬ መኖሩን የወረዳ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር  ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ማስረሻ ማንአየ ለዶቼ ቬለ ገልጸዋል ፡፡
በአደጋው በከፊልና በሙሉ የቤተሰብ አባሎቻቸውን ያጡ ተጎጂዎችን የመለየትና የመመዝገብ ሥራ በመከናወን ላይ እንደሚገኝ  አቶ ማስረሻ ጠቅሰዋል ፡፡ እስከአሁን ባለው መረጃ ከአደጋው ጋር በተያያዘ ከሁለት ሺህ ሦስት መቶ በላይ ሰዎች አስቸኳይ ድጋፍ እንደሚያሥፈልጋቸው መረጋገጡን ሃላፊው ተናግረዋል ፡፡

የጎፋ ወረዳ ነዋሪዎች በመሪት መንሸራተት  የተቀበሩ ቤተሰቦቻቸውን አስከሬን እየፈለጉ
የጎፋ ወረዳ ነዋሪዎች በመሪት መንሸራተት የተቀበሩ ቤተሰቦቻቸውን አስከሬን እየፈለጉምስል Gofa Zone Government Communication Affairs Department

ወደ ሥራ የገባው ግብረኃይል

እስከአሁን ባለዉ ሂደት የተለያዩ ኮሚቴዎች ተደራጅተዉ የነፍስ አድን እና የዕለት ደራሽ ዕርዳታ የማቅረብ ሥራ በመከናወን ላይ እንደሚገኝ የክልሉ መንግሥት አስታውቋል፡፡ ድጋፉን በተቀናጀ መልኩ ለመፈጸም የተቀናጀ መዋቅር መደራጀቱን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የመንግሥት ተጠሪ አቶ አለማየሁ ባውዴ ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ ጠቅሰዋል በጎፋ ዞን በደረሰ የመሬት መንሸራተት ሕይወታቸውን ያጡ ሰዎች ቁጥር ወደ 55 ማሻቀቡን ባለሥልጣናት ተናገሩ፡፡
አደጋው እጅግ ልብ ሰባሪ የሚያደርገው የተጎዱ ወገኖችን ለማትረፍ ወደ ሥፍራው የሄዱ ሰዎች በሁለተኛው ናዳ ህይወታቸው መጥፋቱ መሆኑን የጠቀሱት አቶ አለማየሁ “ አሁን ድጋፍ የሚፈልጉ ወገኖቻችንን መደገፍ ጀምረናል ፡፡ ከዛሬው ጠዋት ጀምሮ የምግብ አቅርቦት እየተከናወነ ይገኛል ፡፡ በቀጣይ ተጎጂዎችን በማረፊያ ቦታ በማቆየት የተቀናጀ ድጋፍ የሚደረግ ይሆናል ፡፡ ለዚህም ከፌዴራል መንግሥት ጋር በመቀናጀት እየተሠራ ይገኛል “ብለዋል ፡፡
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በአደጋው የተጎዱ ዜጎችን ለመደገፍ በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጽህፈት ቤት የሚመራ ግብረሀይል ትናንት መቋቋሙ የሚታወቅ ነው ፡፡ በአሁኑወቅት የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችና ተቋማት በገንዘብ እና በአይነት ድጋፍ  እያደረጉ ይገኛሉ ፡፡

ሸዋንግዛው ወጋየሁ
ኂሩት መለሰ
እሸቴ በቀለ