1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የመስከረም 27 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ መስከረም 27 2017

በሊዝበን የግማሽ ማራቶን ብርቱ ፉክክር ኢትዮጵያዊው አትሌት ሞስነት ገረመው ለድል በቅቷል ። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ሊቨርፑል መሪነቱን እንዳስጠበቀ ነው ። ማንቸስተር ሲቲ እና አርሰናልም እግር በእግር እየተከተሉ ነው ። በጀርመን ቡንደስሊጋ መሪው ባየር ሙይንሽን በሁለት ነጥብ ከሚበልጠው አይንትራኅት ፍራንክፉርት ጋር ነጥብ ለመጋራት ተገድዷል ።

https://p.dw.com/p/4lVTM
Euro 2024 | Türkei - Niederlande
ምስል John MacDougall/AFP/Getty Images

ሣምታዊ የስፖርት ዘገባ

በሊዝበን የግማሽ ማራቶን ብርቱ ፉክክር  ኢትዮጵያዊው አትሌት ሞስነት ገረመው ለድል በቅቷል ። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ሊቨርፑል መሪነቱን እንዳስጠበቀ ነው ። ማንቸስተር ሲቲ እና አርሰናልም እግር በእግር ይከተላሉ ። በጀርመን ቡንደስሊጋ መሪው ባየር ሙይንሽን በሁለት ነጥብ ከሚበልጠው አይንትራኅት ፍራንክፉርት ጋር ነጥብ ለመጋራት ተገድዷል ።  ለአይንትራኅት ፍራንክፉርት ዖማር ማርሙሽ ድንቅ ብቃቱን ዐሳይቷል ።  ሮበርት ሌቫንዶቭስኪ በስፔን ላሊጋ ሔትትሪክ ሠርቶ ባርሴሎናን ለድል አብቅቷል ። በዩናይትድ ስቴትስ ዝነኛው የቅርጫት ኳስ ግጥሚያ አባት እና ልጅ አንድ ላይ በመሰለፍ ታሪክ አስመዝግበዋል። 

አትሌቲክስ

ፖርቹጋል ውስጥ ትናንት በተከናወነው የሊዝበን የግማሽ ማራቶን ብርቱ ፉክክር ኢትዮጵያዊው አትሌት ሞስነት ገረመው ኬንያውያን እና የዩጋንዳ ሯጮችን አስከትሎ በአሸናፊነት አጠናቋል ። አትሌት ሞስነት ገረመው ውድድሩን በአንደኛነት ያጠናቀቀው 1:03.09 በሆነ ጊዜሮጦ በመግባት ነው ። በዚህ ውድድር፦ የኬንያው አትሌት ፔተር ክዋሊ ሰባት ሰከንድ ከሞስነት በመዘግየት ሁለተኛ ወጥቷል ። ሦስተኛ ደረጃ ያገኘው የዩጋንዳው ሯጭ ቪክቶር ክዌምቦይ በሞስነት በ14 ሰከንዶች ተቀድሟል ።  የመስከረም 20 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ኬንያውያት አሸናፊ በሆኑበት በሴቶች ተመሳሳይ ርቀት ፉክክር ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ዓለም ንጉሥ የሦስተኛ ደረጃ ይዛ አጠናቃለች ። ኬንያዊቷ ሯጭ ፌይዝ ቼፕቺር ኪፕሮች ርቀቱን በ01:10:33 በማጠናቀቅ አንደኛ ወጥታለች ። ሌላኛዋ ፌይዝ ቼፕኮዬች በአራት ሰከንዶች ተቀድማ ሁለተኛ ደረጃ አግኝታለች ። ዓለም ያጠናቀቀችው 01:10:46 በመሮጥ ነው ።

የሩጫ ፉክክር
በርቹጋል የሊዝበን የግማሽ ማራቶን ብርቱ ፉክክር ኢትዮጵያዊው አትሌት ሞስነት ገረመው ኬንያውያን እና የዩጋንዳ ሯጮችን አስከትሎ በአሸናፊነት አጠናቋል ምስል Pavel/Pond5 Images/IMAGO

እግር ኳስ

ዕድሜያቸው ከ20 ዓመት በታች ተጨዋቾች በሚፎካከሩበት የሴካፋ እግር ኳስ ግጥሚያ፦ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዛሬ ከዩጋንዳ ጋር አቻው ጋር ተጋጥሞ 3 ለ0 ተሸንፏል ። ሦስተኛው ግብ የተቆጠረው ቡድኑ ዛሬ በአዛም ኮምፕሌክስ ስታዲየም ውስጥ ያደረገው የመጀመርያ የምድብ ጨዋታውን ነው ።  

 የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በበኩሉ ለ2025 የአፍሪቃ ዋንጫ ማጣርያ ከጊኒ ጋር ለሚያደርጋቸው ጨዋታዎች ዝግጅቱን ከወዲሁ መጀመሩ ታውቋል ። ብሔራዊ ቡድኑ እሁድ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሜዳ የሁለተኛ ቀን ልምምዱን አከናውኗል ። በትናንት ልምምድ ላይም ከአሜሪካ ቡድኑን ከሚቀላቀለው ሱራፌል ዳኛቸው በስተቀር 22 ተጫዋቾች መገኘታቸውን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዐሳውቋል ። ከጊኒ ጋር ሁለት የማጣርያ ጨዋታዎች ጥቅምት 2 እና 5 ኮትዲቯር አቢጃን ውስጥ እንደሚከናወኑም ታውቋል ።  የብሔራዊ ቡድኑ አቋም እና አሰልጣኙ ከቡድኑ ጋር ስላላቸው የወደፊት ቆይታ ቃለ መጠይቅ አድርገናል ። የመስከረም 13 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

የስፖርት ጋዜጠኛ ዖምና ታደለ፦ ከአፍሪቃ ዋንጫ በፊት ያለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ሁኔታ ጥሩ አይመስልም ብሏል ። በምድቡ አንድም ግብ ማስቆጠር ተስኖት አንድ ነጥብ ብቻ ይዞ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ለሚገኘው ብሔራዊ ቡድን የውድድር ጉዞው አስቸጋሪ መሆኑንም ገልጧል ። ቀሪ የማጣሪያ ጨዋታዎቹ የብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ እጣ ፈንታንም የሚወስኑ መሆናቸውን ጠቁሟል ።

የስፖርት ጋዜጠኛ ዖምና ታደለ
የስፖርት ጋዜጠኛ ዖምና ታደለ፦ የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ሁኔታ ጥሩ አይመስልም ብሏልምስል privat

ፕሬሚየር ሊግ

ሊቨርፑል በአዲስ አሰልጣኙ አርኔ ስሎት ዘመን የሚያቆመው አልተገኘም ። በዘንድሮ የፕሬሚየር ሊግ ሰባተኛ ውድድሩ ክሪስታል ፓላስን 1 ለ0 በማሸነፍ ነጥቡን 18 ማድረስ ችሏል ። የደረጃ ሰንጠረዡ ላይም በመሪነት እንደተቆናጠጠ ነው ። ጨዋታው በተጀመረ ዘጠነኛው ደቂቃ ላይ በዲዬጎ ጆታ ግብ መምራት የቻለው ሊቨርፑል ተጨማሪ ግብ ማስቆጠር ተስኖት ግን ነጥብ ላለመጣልም ሥጋት ውስጥ ገብቶ ነበር ። በተለይ የክሪስታል ፓላሱ አጥቂ ጆን ፊሊፕ ማቴታ አቻ ሊሆን የሚችል የግብ ዕድል አግኝቶ በሊቨርፑል ጠንካራ የተከላካዮች ብቃት መክሸፉ ለደጋፊዎቹ አስደንጋጭ ነበር ።

ከአሰልጣኝ ዬርገን ክሎፕ ዘመን በኋላ ሊቨርፑል የሻምፒዮንስ ሊግ ግጥሚያን ጨምሮ ባደረጋቸው ዐሥር ግጥሚያዎች ዘጠኙን በድል አጠናቅቋል ። በሻምፒዮንስ ሊግም  የጣሊያኑ ኤሲ ሚላንን 3 ለ1 እንዲሁም ቦሎኛን 2 ለ0 ማሸነፍ ችሏል ። ሊቨርፑል እስካሁን ሽንፈት የደረሰበት በኖቲንግሀም ፎረስት የ1 ለ0 ብቻ ነው ።

ያለፈው የጨዋታ ዘመን የዋንጫ ባለድል ማንቸስተር ሲቲ እና ተፎካካሪው አርሰናል ሊቨርፑልን በ17 ነጥብ እግር በእግር እየተከተሉ ነው ። ሁለቱም ተመሳሳይ 17 ነጥብ እና ዘጠኝ የግብ ክፍያ አላቸው ።  ማንቸስተር ሲቲ 17 አርሰናል 15 ግቦችን አስቆጥረው ስምንት እና ስድስት ተቆጥሮባቸዋል ።

በፔፕ ጓርሲዮላ የሚሰለጥነው ማንቸስተር ሲቲ ፉልሀምን 3 ለ2 አሸንፏል ። የፉልሀም ተጨዋቾች እስከ መጨረሻው ድረስ ብርቱ ፉክክር ዐሳይተዋል ። በደረጃ ሰንጠረዡ ሁለተኛ ላይ የሚገኘው ማንቸስተር ሲቲ ደጋፊዎች የአሰልጣኙ ውል ከወዲሁ እንዲራዘም በነጭ ቀለም በስፓኒሽኛ በተጻፈ ጽሑፍ በጨዋታው ወቅት ጠይቀዋል ። ፦ «ፔፕ ጓርሲዮላ እንድትቆይ እንፈልጋለን!» ሲሉም ተማጽነዋል ።

የማንቸስተር ሲቲ  አሰልጣኝ ፔፕ ጓርሲዮላ
የማንቸስተር ሲቲ አሰልጣኝ ፔፕ ጓርሲዮላ በፕሬሚየር ሊግ ኮከብ ግብ አግቢው ለሆነው ኧርሊንግ ዖላንድን መመሪያ ሲሰጡምስል SCOTT HEPPELL/REUTERS

አርሰናል ከታችኛው ዲቪዚዮን ዳግም ብቅ ያለው ሳውዝሐምፕተንን 3 ለ1 ድል አድርጓል ። አርሰናል ለድል የበቃው 1 ለ0 ከመመራት ተነስቶ ነው ። አቻ የምታደርገውን ግብ  የጀርመን ብሔራዊ  ቡድን ተሰላፊው ካይ ሐቫርትስ 58ኛ ደቂቃ ላይ አስቆጥሯል ። የዕለቱ ምርጥ ተጨዋች የነበረው ቡካዮ ሳካ የመጀመሪያዋን እና ጋብሪዬል ማርቲኔሊ 68ኛ ደቂቃ ላይ ያስቆጠሩትን ግቦች አመቻችቷል ።  መደበኛ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ሊጠናቀቅ ሁለት ደቂቃ ሲቀረውም ሦስተኛውን ግብ ራሱ ከመረብ አሳርፏል ።

በሌሎች ግጥሚያዎች፦ ትናንት እስከ መጀመሪያው ረፍት ድረስ ብራይተንን 2 ለ0 ሲመራ የነበረው ቶትንሀም የማታ ማታ መሪነቱን ከእጁ አሳልፎ የ3 ለ2 ሽንፈት አስተናግዷል ። በ14 ነጥብ አራተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ቸልሲ በቀይ ካርድ አንድ ተጨዋቹን ካጣው ኖቲንግሀም ፎረስት ጋር አንድ እኩል ተለያይቶ ነጥብ ተጋርቷል ። ማንቸስተር ዩናይትድ ትናንት ከአስቶን ቪላ ጋር ያለምንም ግብ ተለያይቷል ። በ8 ነጥብ ብቻ ተወስኖ 14ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል ። ክሪስታል ፓላስ፤ ሳውዝሐምፕተን እና ዉልቭስ ከ18ኛ እስከ 20ኛ ወራጅ ቀጣና ውስጥ ይገኛሉ። የማንቸስተር ሲቲው ግብ አዳኝ ኧርሊንግ ዖላንድ 10 ግቦችን ከመረብ በማሳረፍ የፕሬሚየር ሊጉ ኮከብ ግብ አግቢነቱን ይመራል ። የብሬንትፎርድ ብርያን ምቤሙ እና የቸልሲው ኮል ፓልመር በስድስት ግቦችቦች ይከተላሉ ። የሊቨርፑሉ ሉዊስ ዲያዝ በአምስት ግቦች ይከተላል ።

ቡንደስሊጋ

የአይንትራኅት ፍራንክፉርቱ ዖማር ማርሙሽ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ባዬርን ሙይንሽንን ጉድ አድርጓል ። ትናንት በነበረው የቡንደስሊጋ ግጥሚያ 3 ለ2 ሊሸነፍ የነበረው አይንትራኅት ፍራንክፉርት በዖማር ማርሙሽ 90 ደቂቃ ተገባዶ በጭማሪው 4ኛ ላይ በተቆጠረው ግብ አቻ ወጥቷል ። የጨዋታው ኮከብ የነበረው ዖማር ማርሙሽ እስካሁን በቡንደስሊጋው ባደረጋቸው ስድስት ጨዋታዎች የትናንትና ሁለት ግቦችን ጨምሮ ስምንት ግቦችን አስቆጥሯል ፥ በዚያም የቡንደስሊጋው ኮከብ ግብ አግቢ ነው ። አራት አመቻችቷል ።  በባከነ ደቂቃ የማሸነፍ ዕድላቸውን የተነጠቁት የባዬርን ሙይንሽን አሰልጣኝ ቪንሰንት ኮምፓኒ፦ ተረጋግተን እንቀጥላለን ብለዋል በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ።

የባዬርን ሙይንሽን አሰልጣኝ ቪንሰንት ኮምፓኒ
የባዬርን ሙይንሽን አሰልጣኝ ቪንሰንት ኮምፓኒምስል Uwe Anspach/dpa/dpa

ላይፕትሲሽ ትናንት ሆፈንሀይምን 1 ለ0 አሸንፎ ነጥቡን 14 አድርሷል ። አይንትራት ፍራንክፉርት በ13፤ ፍራይቡርግ በ12 ነጥብ ሦስተኛ እና አራተኛ ደረጃ ላይ ናቸው ። ሆፈንሀይም፤ ሆልሽታይን ኪል እና ቦሁም ከ16ኛ እስከ 18ኛ ወራጅ ቀጣና ላይ ተደርድረዋል ።  ጀርመን በኔሽን ሊግ ከቦስኒያ እና ሔርዜጎቪና ጋር የፊታችን ዐርብ ለሚኖረው ጨዋታ የቡንደስሊጋ ግጥሚያዎች ለጊዜው ገታ ይደረጋሉ ። ከሐሙስ እስከ ቅዳሜ ድረስ 26 የኔሽን ሊግ ግጥሚያዎች ይኖራሉ ። የጳጉሜ 4 ቀን፣ 2016 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

በስፔን ላሊጋ ሮበርት ሌቫንዶቭስኪ አላቬስ ላይ ትናንት ሔትትሪክ በመሥራት ባስቆጠራቸው ሦስት ግቦች መሪው ባራሳ በ24 ነጥብ እንዲገሰግስ አአስችሎታል ። ሪያል ማድሪድ በ21 አትሌቲኮ ማድሪድ በ17 ሁለኛተኛ እና ሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ ። ሁለቱ ትናንት ተጋጥመው አንድ እኩል ነው የተለያዩት ። በነገራችን ላይ የሪያል ማድሪድ ዐይኖች የሊቨርፑሉ ትሬንት አሌክሳንደር አርኖልድ ላይ ማረፋቸው ተዘግቧል ። ምናልባትም ትሬንትን ጥር ወር ላይ ሪያል ማድሪድ ሊያስፈርመው ይችላል ተብሏል ።

ቅርጫት ኳስ

 የብሔራዊ ቅርጫት ኳስ ማኅበር (NBA) ግጥሚያ ዝነኛው ሌብሮን ጄምስ
የብሔራዊ ቅርጫት ኳስ ማኅበር (NBA) ግጥሚያ ዝነኛው ሌብሮን ጄምስ (ኳስ የያዘው) ከደቡብ ሱዳን ጋር የተጫወቱ ጊዜ ። ፎቶ፦ ከማኅደርምስል Gregory Shamus/Getty Images

በዩናይትድ ስቴትስ የብሔራዊ ቅርጫት ኳስ ማኅበር (NBA) ግጥሚያ ዝነኛው ሌብሮን ጄምስ እና ልጁ ብሮኒ ጄምስ በተመሳሳይ ቡድን ውስጥ ተሰልፈው በመጫወት ታሪክ አስመዘገቡ ። አባት እና ልጅ ቡድናቸው ሎስአንጀለስ ሌከርስ ከፎኒክስ ሰንስ ጋር ሲጋጠም የ20 ዓመቱ ብሮኒ በሁለተኛው ሩብ ግጥሚያ ላይ ከአባቱ ጋር ለመሰለፍ ችሏል ። የ39 ዓመቱ አባት ሌብሮን ጄምስ «ዎው፤ ያ ፍጹም እውን የማይመስል ነው» ሲል ኤክስ የማኅበራዊ መገናኛ አውታር ላይ ጽፏል ። ልጅ ብሮኒ ጄምስ ለሎስአንጀለስ ሌከርስ የቅርጫት ኳስ ቡድን ለሁለት ዓመት መፈረሙ ታውቋል ። አባቱ ሌብሮን ጄምስ በቅርጫት ኳስ ታሪክ የምንጊዜም ምርጥ ነጥብ አስቆጣሪ በመሆን ስሙን ከፍ ተደርጎ ይጠራል ።  በብሔራዊ ቅርጫት ኳስ ማኅበርም የአራት ጊዜያት አሸናፊ በመሆን ይታወቃል ።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ኂሩት መለሠ