1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የመስከረም 13 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ መስከረም 13 2017

በሳምንቱ መጨረሻ እጅግ ተጠባቂ በነበረው የማንቸስተር ሲቲ እና አርሰናል ፍልሚያ ሲቲ በሜዳው ጉድ ከመሆን የማታ ማታ ተርፏል ። አርሰናል ሙሉ ግማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜውን አንድ ተጨዋች ጎድሎበትም አይበገሬነቱን ዐሳይቷል ። ቸልሲ እና በሻምፒዮንስ ሊጉም ድል የቀናው ሊቨርፑል በተመሳሳይ የግብ ልዩነት ተጋጣሚዎቻቸውን አሰናብተዋል ።

https://p.dw.com/p/4kyxg
ማንቸስተር ሲቲ እና አርሰናል
ማንቸስተር ሲቲ እና አርሰናል ዘንድሮም በብዙዎች ዘንድ ለዋንጫ ከሚጠበቁ ጥቂት ቡድኖች ቀዳሚዎቹ ናቸውምስል Dave Thompson/AP Photo/picture alliance

ሳምንታዊ የስፖርት ዘገባ

በሳምንቱ መጨረሻ እጅግ ተጠባቂ በነበረው የማንቸስተር ሲቲ እና አርሰናል ፍልሚያ ሲቲ በሜዳው ጉድ ከመሆን የማታ ማታ ተርፏል ። አርሰናል ሙሉ ግማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜውን አንድ ተጨዋች ጎድሎበትም አይበገሬነቱን ዐሳይቷል ። ቸልሲ እና በሻምፒዮንስ ሊጉም ድል የቀናው ሊቨርፑል በተመሳሳይ የግብ ልዩነት ተጋጣሚዎቻቸውን አሰናብተዋል ። ማንቸስተር ዩናይትድ ግብ ማግባት ተስኖት ነጥብ ተጋርቷል ። ዕድሜያቸው ከ20 ዓመት በታች  የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን  ለታንዛኒያው የሴካፋ ፉክክር ዝግጅቱን በማካናወን ላይ ነው ። የሙቀት ጉዳይ በፎርሙላ አንድ አሽከርካሪዎች ዘንድ ዋነኛ መነጋገሪያ ሁኗል ።

እግር ኳስ

እጅግ አጓጊ ወደነበረው የእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ የሳምንቱ መጨረሻ ውድድር ከመሻገራችን አስቀድመን ታንዛኒያ ስለምታዘጋጀው የሴካፋ ውድድር አጠር ያለ ዘገባ ይኖረናል ። ዕድሜያቸው ከ20 ዓመት በታች  የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ታንዛኒያ በምታስተናግደው የዘንድሮ የሴካፋ ዞን የፍሪቃ ዋንጫ ዝግጅቱን በማካናወን ላይ ነው ።  ቡድኑ ለአፍሪቃ ዋንጫ ማጣርያ በሚኖረው ዝግጅት ትናንት በአዲስ አበባ አበበ ቢቂላ ስታድየም የአምስተኛ ቀን ልምምድ ካደረገ በኋላ ቀደም ብሎ ከተቀነሱ ተጫዋቾች በተጨማሪ ሦስት ግብ ጠባቂዎች መቀነሳቸው ተገልጧል ።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ቡድን  በምድብ «ለ»  ከኡጋንዳ፤ ቡብ ሱዳን እና ቡሩንዲ ጋር ተደልድላለች ። በምድ «ሀ» ደግሞ፦ አስተናጋጇ ታንዛኒያ፤ ሱዳን፤ ርዋንዳ እና ኬንያ ተደልድለዋል ። ውድድሮቹ ከእሁድ መስከረም 26 ቀን፤ 2017 ዓ.ም እስከ ጥቅምት 10 ቀን፤ 2017 ዓ.ም ድረስ ለሁለት ሳምንታት ታንዛኒያ ውስጥ ይከናወናሉ ። 

የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን መቼ ይሆን በሜዳው የሚጫወተው?
የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን መቼ ይሆን በሜዳው የሚጫወተው?ምስል Omna Tadele/ DW

ፕሬሚየር ሊግ

በሳምንቱ መጨረሻ ከተከናወኑ የእግር ኳስ ግጥሚያዎች መካከል ማንቸስተር ሲቲ አርሰናልን ያስተናገደበት እጅግ አጓጊ ነበር ። የማታ ማታ በጆን ስቶንስ ግብ ሁለት እኩል ወጣ እንጂ ማንቸስተር ሲቲ ብርቱ ሽንፈት ገጥሞት ነበር ።  በሜዳው ኢትሐድ፤ በደጋፊዎቹ ፊት የተጫወተው ማንቸስተር ሲቲ አንድ ተጨዋቹ በቀይ ካርድ ከሜዳ በተሰናበተበት አርሰናል መቼም የማይረሳ ሽንፈት ገጥሞት ነበር ። የማንቸስተር ሲቲ ተከላካይ ማኑዌል አካንጂ በመልሱ ጨዋታ ኤሚሬትስ ስታዲየም ውስጥ አርሰናልን በደጋፊው  ፊት ድል እናደርጋለን ሲል ዝቷል ።

አርሰናል የመጀመሪያው መደበኛ ጨዋታ አጋማሽ ተጠናቆ በ8ኛው ደቂቃ ሌአንድሮ ትሮሳርድ በሁለት ቢጫ በቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቶበታል ። ቀሪውን አጋማሽም በ10 ተጨዋቾች በአብዛኛው በመከላል ለማጠናቀቅ ተገድዷል ። ተጋጣሚውንም አስጨንቆ ሦስት ነጥብ ይዞ ለመውጣት ጫፍ ደርሶ ነበር ። የማታ ማታ ግን ማንቸስተር ሲቲ የአርሰናልን የብረት አጥር የመከላከል ስልት በጆን ስቶንስ ሰብሮ አቻ የምታደርገውን ግብ በማስቆጠር ጨዋታው ወዲያው ተጠናቋል ። የማንቸስተር ሲቲ ላለመሸነፍ ፤ የአርሰናል ድል አድርጎ ወደ ሜዳው ለመመለስ እስከ መጨረሻዋ ደቂቃ ድረስ ያደረጉት ግብግብ እጅግ አዝናኝ ነበር ።  የጳጉሜ 4 ቀን፣ 2016 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

በማንቸስተር ሲቲ የቀኝ የኋላ ተከላካይ መስመር ካይ ዎከር እንደ ግድግዳ ሆኖ የአርሰናል አጥቂዎችን መፈናፈኛ አሳጥቶ ነበር ። ነጥብ ይዘን እንመለሳለን ብሎ ወደ  ኢትሀድ ስታዲየም ላቀናው አርሰናል አንድ ተጨዋች ተሰናብቶበትም ያስመዘገበው ውጤት እጅግ የሚደነቅ ነው ። ማንቸስተር ሲቲም በጨዋታው የባከነ ጊዜ መጠናቀቂያ  ላይ ያስቆጠረው በሜዳው ተሸንፎ ጉድ ከመሆን የተረፈበት  ነው ።

የሻምፒዮንስ ሊጉ ዋንጫ
በሻምፒዮንስ ሊጉም ድል ቀንቶት ኤሲ ሚላንን በሜዳው ሳን ሳሪኖ 3 ለ1 የረታው ሊቨርፑል በፕሬሚየር ሊጉም ተጨማሪ 3 ግብ አስቆጥሮ አሸንፏል ። ምስል Gregorio Borgia/AP/picture-alliance

ለጊዜውም ቢሆን የደረጃ ሰንጠረዡን በ12 ነጥብ በበላይነት የመራው ሊቨርፑልም  ቦታውን በ1 ነጥብ ለበለጠው ማንቸስተር ሲቲ አስረክቧል ። አርሰናል በ11 ነጥብ ከአስቶን ቪላ ቀጥሎ አራተኛ ደረጃ ላይ ሰፍሯል ። አስቶን ቪላ እንደ ሊቨርፑል 12 ነጥብ ይዞ በግብ ልዩነት ሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል ። አስቶን ቪላ ዎልቭስን ቅዳሜ ዕለት 3 ለ1 ድል አድርጓል ። ሊቨርፑልም ዳርዊን ኑኔዝ የመጀመሪያ ግቡን አስቆጥሮ ባለቀሰበት የቅዳሜ ግጥሚያ በርመስን 3 ለ0 ሸኝቷል ። ቸልሲ በ10 ነጥብ በደረጃ ሰንጠረዡ አምስተኛ ነው ። ቅዳሜ ዕለት ከክሪስታል ፓላስ ጋር ያለምንም ግብ የተለያየው ማንቸስተር ዩናይትድ ሰባት ነጥብ ሰብስቦ 11ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል ። ሳውዝሐምፕተን፤ ኤቨርተን እና ዎልቭስ በአንድ ነጥብ ከ18ኛ እስከ 20ኛ ደረጃ ወራጅ ቀጣና ውስጥ ሰፍረዋል ። 

ቡንደስ ሊጋ

በጀርመን ቡንደስሊጋ የሳምንቱ መጨረሻ ፉክክር፦ መሪው ባዬር ሙይንሽን ቬርደር ብሬመን ሜዳ ተጉዞ 5 ለ0 ኩም አድርጎታል ።  በ12 ነጥቡም የደረጃ ሰንጠረዡ መሪነቱን አስጠብቋል ። ሽቱትጋርት በሜዳው ትናንት ዶርትሙንድን አስተናግዶ 5 ለ1 ሸኝቶታል ።   ዶርትሙንድ በደረጃ ሰንጠረዡ እንደሰበሰበው ነጥቡ 7ኛ ነው ። 

ቮልፍስቡርግን ትናንት 4 ለ3 ያሸነፈው ባዬርን ሌቨርኩሰን  በ9 ነጥብ በደረጃ ሰንጠረዡ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል ። ፍራይቡርግ እና አይንትራኅት ፍራንክፉርትም ተመሳሳይ 9  ነጥብ ይዘው በግብ ልዩነት ሦስተኛ እና አራተ ናቸው ።

ባዬር ሙይንሽን
በጀርመን ቡንደስሊጋ መሪው ባዬር ሙይንሽን ምስል Gregor Fischer/dpa/picture alliance

ከሳንክት ፖውሊ ጋር ትናንት ያለምንም ግብ የተለያየው ላይፕትሲሽ እንዲሁም ቅዳሜ ዕለት ሆፈንሀይምን 2 ለ1 የረታው ዑኒዮን ቤርሊን ተመሳሳይ 8 ነጥብ አላቸው ። በግብ ክፍያ ልዩነት ብቻ 5ኛ እና 6ኛ ደረጃ ላይ ሰፍረዋል ። ቦሁም ፤ሳንክት ፓውሊ እና ሆልሽታይን ኪዪል ከ16ኛ እስከ 18ኛ ወራጅ ቀጣና ላይ ይገኛሉ ። የነሐሴ 27 ቀን፣ 2016 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ፎርሙላ አንድ

ሲንጋፖር ውስጥ ትናንት በተከናወነው የፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም ሁለቱ የማርሴዲስ አሽከርካሪዎች ሙቀት ያሰረሰባቸው ተጽእኖ ከፍተኛ መሆኑ ተገለጠ ። በትናንትናው ሽቅድምድም፦ ጆርጅ ሩሴልም ሆነ ሌላኛው የመርሴዲስ አሽከርካሪ ሌዊስ ሐሚልተን አራተኛ እና ስድስተኛ ደረጃ አግኝተው አጠናቀዋል ። ከውድድሩ በኋላ ግን ሙቀቱ በፈጠረባቸው ራስ ምታት የተነሳ ግዴታ በነበረው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ መሳተፍ ተስኗቸዋል ። የመርሴዲስ ተፎካካሪዎች አሰልጣኝ ቶቶ ቩልፍ  ከውድድሩ በኋላ ወዲያውኑ መታመማቸው ተዘግቧል ።

የመርሴዲስ አሽከርካሪው ሌዊስ ሐሚልተን
ቀዝቀቃዛ በሚባለው የዓመቱ ወቅት እንኳን ሙቀት ለፎርሙላ አንድ አሽከርካሪዎች ብርቱ ተጽእኖ አለውምስል Gongora/NurPhoto/picture alliance

አሽከርካሪዎች ላይ የሚከሰተው የሙቀት ሁኔታ አሳሳቢነቱ አነጋግሯል ። በሲንጋፖር ሽቅድምድም  የማክላረኑ አሽከርካሪ ላንዶ ኖሪስ አሸናፊ ሁኗል ። ላንዶ ራሱ አሸንፎ ከተሽከርካሪው ሲወጣ ሙቀቱ አጥወልውሎት እንደነበር ተናግሯል ።  በትናንቱ የፎርሙላ አንድ ሽቅድምድም ሌላኛው የማክላረን አሽከርካሪ ዖስካር ፒያስትሪ ሦስተኛ ደረጃ አግኝቶ አጠናቋል ። ሌዊስ ሐሚልተንን በመቅደም ደግሞ ሻርል ሌክሌርክ አምስተኛ ወጥቷል ።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ታምራት ዺንሳ