ቡርኪናፋሶ ኢትዮጵያን በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ አሸነፈች
ማክሰኞ፣ ኅዳር 11 2016የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን በዓለም ዋንጫማጣርያ 2ኛ የምድብ ጨዋታ ከቡርኪና ፋሶ ጋ በሞሮኮ የኤል አብዲ ስታዲየም ዛሬ ባደረገው ግጥሚያ 3 ለ0 ተሸነፈ ።
ለቡርኪናፋሶ የመጀመሪያዋን ግብ በ69ኛው ደቂቃ ላይ ያስቆጠረው ብላቲ ቱሬ ነው ። ሚሊዮን ሰለሞን በሠራው ጥፋት የተገኘውን የፍጹም ቅጣት ምት ደግሞ 78ኛው ደቂቃ ላይ በርትራንድ ትራዎሬ ከመረብ በማሳረፍ ሁለተኛ ግቡን አስቆጥሯል ። 90ኛ ደቂቃ ላይ ግብ ጠባቂው ሰዒድ ሐብታሙ ወደ ፊት በመውጣት በሠራው ስህተት ዳንጎ ኡዋታራ በቀላሉ ሦስተኛውን ግብ አስቆጥሯል ።
የኢትዮጵያብሔራዊ ቡድን ባለፈው ሳምንት ረቡዕ በዓለም ዋንጫ ማጣርያ ከሴራሊዮን ጋር ተጫውቶ ያለ ጎል አቻ መለያየቱ ይታወሳል ። ምድቡን ግብጽ በ6 ነጥብ ትመራለች ። ቡርኪናፋሶ እና ጊኒ ቢሳዎ በአራት ነጥብ ግን በግብ ክፍያ ልዩነት 2ኛ እና 3ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ ።
ሴራሊዮን እና ኢትዮጵያአንድ ነጥብ ሲኖራቸው በግብ እዳ ልዩነት ሴራሊዮን 4ኛ ደረጃ ላይ ሰፍሯል። ኢትዮጵያ ምንም ነጥብ የሌላት ጅቡቲን በአንድ ነጥብ በልጣ አምስተኛ ደረጃ ላይ ነች ። የዛሬው ድል ለቡርኪናፋሶ የመጀመሪያው ሆኖ ተመዝግቧል ።
የጥቅምት 27 ቀን፣ 2016 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድንን ለማሰልጠን በቅርቡ ለፈረሙት አሰልጣኝ ገብረ መድኅን ኃይሌ የመጀሪያ ጨዋታቸው ነጥብ በመጋራት፤ ሁለተኛው ደግሞ ዛሬ በሰፋ ግብ ልዩነት ሽንፈት ተጠናቋል ። ብሔራዊ ቡድናችን በሰው ሀገር ሩቅ ተጉዞ ለመጫወት የተገደደው የፊፋን መስፈርት የሚያሟላ ስታዲየም ኢትዮጵያ ማዘጋጀት ስላልቻለች ነው ። ያም በመሆኑ የዛሬውን ጨምሮ ዋጋ እየከፈለ ነው ። ሊታሰብበት ይገባል ።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር