1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ትምህርትዓለም አቀፍ

ዓለም አቀፍ የትምህርት ቀን

ልደት አበበ
ዓርብ፣ ጥር 17 2016

የተመድ ዕሮብ ታስቦ የዋለውን ዓለም አቀፍ የትምህርት ቀን በማስታወስ ባወጣው መግለጫ አፍጋኒስታን ውስጥ ሴቶችን ከትምህርት ገበታ ማግለል ሁሉንም የሀገሪቱን ዜጋ እንደሚጎዳ አስታውቋል። ኢትዮጵያ የአፍጋኒስታን አይነት ችግር ባይኖራትም በሀገሪቱ በነበረና ባለ ጦርነት የተነሳ አሁንም በብዙ ሺ የሚቆጠሩ ተማሪዎች ትምህርታቸውን መከታተል አልቻሉም።

https://p.dw.com/p/4bhSG
ወደ ትምህርት የተመለሱት የትግራይ ወጣቶች
ወደ ትምህርት የተመለሱት የትግራይ ወጣቶች ምስል picture alliance / ZUMAPRESS.com

ዓለም አቀፍ የትምህርት ቀን

እጎአ በ2018 ዓም ነበር የተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባኤ የጎርጎሮሲያውያኑን ጥር 24 ቀን "ዓለም አቀፍ የትምህርት ቀን" ብሎ የሰየመው።ይህም ዕለት የትምህርት ጠቃሚ ሚና የሚታወስበት ዕለት ነው። እንደ ተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከሆነ በዓለም ላይ  ከ258 ሚሊዮን በላይ ህጻናት እና አዳጊ ወጣቶች ከትምህርት ገበታ ውጪ ናቸው። 617 ሚሊዮን ህጻናት ማንበብ አይችሉም ወይም መሠረታዊ የሂሳብ ክህሎት አላዳበሩም። ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገራት ከሚገኙ  ልጃገረዶች ከ40 በመቶ ያነሱ ብቻ ናቸው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን የሚያጠናቅቁት። በተለይ እየተደጋገሙ በመጡ የተፈጥሮ አደጋዎች፣ የምግብ እጥረት ወይም ግጭቶች ምክንያት ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው እየተፈናቀሉ እንደሚገኙ ድርጅቱ አስታዉቃል።

 ሌላው ደግሞ አፍጋኒስታን ውስጥ ሴቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ ከህዝብ አይን እየጠፉበት ያለው ሁኔታ ነው። ይህም ታሊባን ሥልጣን ከተቆጣጠረበት ጊዜ ወዲህ በሀገሪቱ ሴቶች መማር የሚፈቀድላቸው እስከ ስድስተኛ ክፍል ድረስ ብቻ በመሆኑ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ የሴቶች የትምህርት ተሳትፎ ከፍተኛ እንደሆነ ነው ያነጋገርናቸው መምህራን የገለፁልን። ስማቸውን መግለፅ ያልፈለጉ አንድ በሶማሌ ክልል ለአራት አመታት በመምህርነት የሰሩ እና በአሁኑ ሰዓት በድሬደዋ እያስተማሩ እንደሆነ የገለፁልን መምህር  እንደነገሩን የሴት ተማሪዎች ተሳትፎ ከወንዶችም የጎላ የሚባል ነው።  « በቁጥር አንፃር ሴቶቹ የሚበልጡበት ሁኔታ ነው። ጥራት ላይ ነው እንጂ ተሳትፎ ላይ ችግር የለም።» ይላሉ። በድሬደዋ ከተማም የገጠማቸው ተመሳሳይ ነገር ነው።

አፍጋኒስታን ውስጥ ህፃናት እና መምሕርት
አፍጋኒስታን ውስጥ በሀገሪቱ ሴቶች መማር የሚፈቀድላቸው እስከ ስድስተኛ ክፍል ድረስ ብቻ ነውምስል Ebrahim Noroozi/AP Photo/picture alliance

በወልቂጤ ዩንቨርስቲ መምህርና የትምህርት ክፍል ኃላፊ የሆኑት መለሠ ሞሬታም ቢሆኑ የሴቶች ተሳትፎ ጥሩ የሚባል እንደሆነ ይናገራሉ። ቢሆንም ግን ይበልጥ ሊሰራበት እንደሚገባ ያሳስባሉ። « ሴቶች በፊት ላይ ማበረታቻ ይሰጣቸው ነበር። አሁን ላይ ሴቶች ናቸው ጎበዝ ተማሪዎች። ግን በተለይ ደግሞ ድጋፍ ቢደረግ የተሻለ ነገር ይመጣል።»

ትምህርት የተቋረጠበት የአማራ ክልል

ጌራ ወርቅ ሁለት የ9ኛ ክፍል ተማሪ የሆኑ ልጆች አሏቸው። የሚኖሩት  በአማራ ክልል ምዕራብ ጎጃም ዞን ሲሆን በአሁኑ ሰዓት ልጆቻቸው እየተማሩ አይደለም።  « እስከ 2015 ድረስ ሰላም ነበር። አሁን ግን ባለው ጦርነት ምክንያት በእኛ ወረዳ ከመስከረም አንስቶ ትምህርት እየተሰጠ አይደለም።» የሚሉት ወላጅ ትምህርት በመዘጋቱ ከፍተኛ ጫና ገጥሟቸዋል። « ትምህርት በመዘጋቱ እኔ ትምህርቱን የማስኬደው እና የማስቆመው እስኪመስል ድረስ ልጆቹ ጫና እየፈጠሩብኝ ነው።» ለግዜው ልጆቻቸው እቤት ትምህርታቸውን እየከለሱ እንዲያጠኑ ያላቸው ብቸኛ አማራጭ ነው።

መቀሌ ትምህርቱን የጨረሰው ፍሪያት

ቀደም ሲል በደብረ ማርቆስ  ዩንቨርስቲ ተማሪ የነበረው ወጣት ፍሪያት በኮሮና ወረርሽኝ እና በሰሜኑ ጦርነት የተነሳ ለዓመታት ትምህርቱን ካቋረጠ በኋላ በመጨረሻ በሚኖርበት መቀሌ ከተማ ትምህርቱን ማጠናቀቅ በመቻሉ ዛሬ ላይ ደስተኛ ነው።  « በ2012 ምረቃ ነበር። በመሀል ኮቪድ ሲመጣ እኛው ወደቤታችን እንድንሄድ ውሳኔ ተወሰነ። » በጥቅምት ወር ወደ ትምህርት ቤት እንዲመለሱ ጥሪ እንደደረሳቸውም የሰሜኑ ጦርነት ተከሰተ።  ጦርነቱ አብቅቶ የሰላም ስምምነት ከተደረገ በኋላም ፍሪያት በአማራ ክልል ባለው ጦርነት ወደ ደብረ ማርቆስ መመለስ አልቻለም።  ስለሆነም ትምህርቱን መቀሌ ዩንቨርስቲ ሊያጠናቅቅ ችሏል። ይሁንና ፍሪያት የተመረቀበት ወረቀት በእጁ ስላልገባ እስካሁን ለስራ ማመልከት አልቻለም። 

ወጣቱ የ12ኛ ክፍል ተማሪ ወንድም አለው። «እሱም ከረዥም ዓመታት በኋላ መልሶ ወደ ትምህርት ገበታው ተመልሷል።» ይላል።  « የከሰሩበት አመታት እንዲካካስ የሁለት ሴሚስተር ትምህርት በአንድ ሴሚስተር እየተማሩ ወደ ትምህርት ገበታቸው ተመልሰው እየተረጋጉ ነው። በአጠቃላይ ሲታይ እሱ በሚኖርበት አካባቢ ያሉ «ተማሪዎች ባለፉት ዓመታት ያሳለፉት ሁኔታ ከፍተኛ ሥነ ልቦናዊ ጉዳት ጥሎባቸዋል» የሚለው ፍሪያት ተማሪው ራቅ ያለ ቦታ ሄዶ የመማር ፍላጎት እንደሌለውም ይናገራል።  « አንድ ተማሪ ወደ ሌላ ክልል ሄዶ እንዲማር የወላጅም ፣ የተማሪም ፍላጎት የለም እና ከባድ ነው»

ትምህርት ቤት በጎርፍ ተሞልቶ
በኦሞ ወንዝ መሙላት የተነሳ ትምህርት ቤቶች በዚህ ዓመት ማስተማር አቋርጠው ነበር።ምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

 « ተማሪዎች ያለውን ሀገራዊ እና አካባቢያዊ ሁኔታ ተቋቁመው ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ይገኛሉ»

በደቡብ ክልል ማጂ ወረዳ ቱም ከተማ ነዋሪ የሆኑ አስተያየት ሰጪ እንደገለፁልን ተማሪዎች ያለውን ሀገራዊ እና አካባቢያዊ ሁኔታ ተቋቁመው ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ይገኛሉ። « ሁለት የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች አሉ። እስከ 10ኛ እና እስከ 8ኛ እንዲሁም ከዚያም በታች የሚያስተምሩ ትምህርት  ቤቶች አሉ።  ስለዚህ የትምህርት ሁኔታው አልተስተጓጎለም። ከእነ ችግሩም ቢሆን እንደቀጠለ ነው።

በኦሮሚያ ክልል ሐረማያ ዩንቨርስቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ዓለምእሸት ተሾመ እንደገለፁልን የመማር ማስተማር ሂደቱ በሚሰሩበት የከፍተኛ ተቋም በተያዘው የትምህርት ካሌንደር መሠረት እየተከናወነ ይገኛል። የተማሪዎች የመማር ፍላጎት « የተለያየ ነው። » ይላሉ። « ለፍተው ብዙ ፈተናዎችን አልፈው የሚመጡ ተማሪዎች አሉ የዛን ያህል ደግሞ አልፎ አልፎ አንዳንድ ተማሪዎች ከቤተሰብ ቁጥጥር ነፃ የሚሆኑበት ጊዜ ስለሆነ ወደ መዝናናቱ ትኩረት የሚያደርጉ እና መስመር የሚስቱ ይኖራሉ።»

ባለፉት ሁለት ዓመታት ኢትዮጵያ ውስጥ እንደተስተዋለው ወደ ዩንቨርስቲ የሚያልፉት ተማሪዎች ቁጥር ቀንሷል። ዩንቨርስቲው መቀበል ከሚችለው አቅም ያነሰ እየተቀበለ እንደሆነ የገለፁልን ዓለምእሸት ይህም «   እነዛ ልጆች ላይ አተኩሮ እንዲሰራ በቅርብ ለመከታተል እና ለመመዘን ለመምህራን ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል። ብዙ ቁጥር ሲያዝ እና ውስን ቁጥር ሲሆን ለውጥ ይኖረዋል።»

መምህራን ለምን በቂ ድጋፍ ይሻሉ?

«የቀን ሰራተኛ ከአንድ መምህር የበለጠ ገቢ አለው » በማለት እውቀት በሚያስጨብጡት መምህራን ዘንድ ተስፋ መቁረጥ እንደሚስተዋል የገለፁልን የወልቂጤ ዩንቨርስቲ መለሰ ታድያ መምህር ሆነው እንዲቆዩ ብርታት የሆናቸው ምን ይሆን?   «  ትውልድን መቅረፅ ትልቅ ነገር ነው። ሁሉም ከሸሸ ከባድ ነው። ሁለተኛው ደግሞ አማራጭ ማጣት ነው። የድሬደዋው ዩንቨርስቲ መምህሩም ቢሆኑ ሌላ አማራጭ ቢኖራቸው ይመርጣሉ። የጤና ባለሙያ መሆን የመጀመሪያ ምርጫቸው ነበር። ቀደም ሲል ባስተማሩበት ሶማሌ ክልል «ይገባኛል» የሚሉትን ክፍያ ባለማግኘታቸው ክልል ቀይረዋል።  « የኑሮ ውድነትን ያገናዘበ ደሞዝ ብቻ አይደለም። ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞችም መከበር ይኖርባቸዋል። መንግሥት እሱን ትኩረት ሰጥቶ ቢሰራበት» የሚሉት መምህር ሶማሌ ክልል የአንድ አመት የJEG ክፍያ እንዳላገኙ ይናገራሉ። 

ልደት አበበ

ነጋሽ መሐመድ