እንወያይ፤ የጠቅላይ ሚኒስትሩና የተቃዋሚ ፓርቲዎች ዉይይት ፋይዳዉ ምን ይሆን?
እሑድ፣ ሐምሌ 28 2016የጠቅላይ ሚኒስትሩና የተቃዋሚ ፓርቲዎች ስብሰባ ምን ፋይዳ ይኖረዉ ይሆን?
የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባላት የሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች ባለፈዉ ሳምንት መጀመርያ ከኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ጋር ተገናኝተው ተወያይተዋል። በኢትዮጵያ ወደ 69 የተቃዋሚ ወይም ደግሞ የተቀናቃኝ ፓርቲዎች ይገኛሉ። በዚህ ስብሰባ ላይ ፋይዳ አያመጣም ብለዉ በስብሰባው ለመሳተፍ ፈቃደኛ ያልሆኑ አንዳንድ ፓርቲዎች መኖራቸዉ ነዉ የተነገረዉ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያቀዱት የተባለዉ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር የተደረገዉ ዉይይት፤ በሦስት ወራት ዉስጥ ሲካሄድ ይህ ለሁለተኛ ጊዜ መሆኑ ነዉ። ከ97 በመቶ በላይ የሚሆነውን መቀመጫ በፓርላማ የያዘዉ ገዢው ፓርቲ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ንቁ ተሳትፎ እንዳያደርጉ አቅም አሳጥቶዋቸዋል፤ ተብሏል። ይሁንና ይህ ለሁለተኛ ጊዜ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር የተደረገዉ ዉይይት ተቃዋሚ ፓርቲዎቹ ያላቸዉን ጥያቄ በቀጥታ በማቅረባቸዉ በይሁንታ ታይቷል። ተቃዋሚ ፓርቲዎቹ በዉይይቱ ላይ ካነስዋቸዉ ነጥቦች መካከል በሃገሪቱ የፖለቲካ ምህዳር መጥበብ፤ በተቃዋሚዎች ላይ የሚታየዉ ጭቆና፤ ዛቻና እስራትን ጨምሮ የታሰሩ ተቃዋሚዎች እንዲፈቱ ያቀረቡት ጥያቄዎች ይገኙበታል። ከዚህ በተጨማሪ የፕሪቶሪያዉ ስምምነት አፈጻጸም ተግባራዊነት፤ ፍትሃዊ የህዝብ መገናኛ ብዙኃን አጠቃቀም፤ የዜጎች የመንቀሳቀስ መብት መጠበቅ፣ የፍትህ ስርዓት ነጻነት እና ሀገራዊ ውይይት ከተጠቀሱት ነጥቦች መካከል ይገኙበታል። በስብሰባዉ ላይ ገዥው ፓርቲ የቀረው ሁለት ዓመት ብቻ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በበኩላቸዉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች፤ ሰብሰብ ብለዉ፤ ተደራጅተዉ እንዲቀርቡ ፤በፖለቲካ ጉዳዮች ላይ ልዩነት ቢኖረንም፣ በሃገር ጉዳይ ላይ መንግሥትን በመደግፍ መስራት ለሚፈልግ ሁሉ በሩ ክፍት መሆኑን ገልፀዋል። ከውይይቱ ለሀገሪቱ ውጤታማ መፍትሄ ተገኝቶ ይሆን? የጠቅላይ ሚኒስትሩ እና የፖለቲካ ፓርቲዎች ዉይይት እንዴት ይገመገማል?
-የፖለቲካ ፓርቲዎች እና የጠቅላይ ሚኒስትሩዉይይትን እንዴት ይገመገማል?
-የፖለቲካ ምህዳሩ እንዲሰፋ፤ የታሰሩት እንዲፈቱ ፤ ዲሞክራሲን የማስፈኑ ጉዳይ እንዲቀጥል፤ ከሁሉም በላይ በሃገሪቱ የሚታየዉ ችግር ተቀርፎ ሰላም እንዲመጣ ፤ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ምን ይጠበቃል?
-መንግሥት እንዲሁም ነፍጥ ያነገቡ ተቃዋሚዎች ጠበንጃን ዘቅዝቀዉ ወደ ሰላም እንዲመጡ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ምን እኢደረጉ ነዉ?
-የፖለቲካ ምህዳሩ አሁንም አልሰፋም፤ ሰዎች ይታሰራሉ፤ ጦርነት እና የየዜጎች ስቃይ አሁንም በተለያዩ አካባቢዎች ይታያል። የፖለቲካ ምህዳሩ እንደጠበበ ነዉ፤ ይባላል እና ይህ መነጋገራችሁ እነዚህ እነዚህ ነገሮች ላይ ለዉጥ ካላመጣ፤ ምንድን ነዉ ፋይዳዉ? ነዉ ወይስ ለዉጥ አምጥቷል ብላችሁ ታስባላችሁ?
-መንግሥትስ ምን እንዲያደርግ ነዉ ቃል የገባላችሁ? ከናንተስ ምን ይጠበቃል?
-በአገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ዉጤታማ እንዲሆን በተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ዘንድ ምን እየተደረገ ነዉ?
-ከዉይይቱ በኃላ መንግሥትስ ለተገዳዳሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች ይሄን አደርጋለሁ ብሎ ቃል የገባዉ ነገር አለ?
በዚህ ዉይይት ላይ ሃሳባቸዉን ሊያካፍሉን፤
1.አቶ ደስታ ዲንቃ፤ የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ ዋና ፀሐፊ እና የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ)የኦዲት ፤ ኢንስፔክሽን እና ሥነ-ምግባር ኮሚቴ ፀሐፊ፤ እንዲሁም በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሊቀመንበር፤
2.አቶ ጌትነት ወርቁ የእናት ፓርቲ አመራር
3.አቶ ከበደ አሰፋ የትንሣኤ ሰባ እንደርታ ፓርቲ ሊቀ መንበር እንዲሁም
4.አቶ ልደቱ አያሌዉ፤ ታዋቂ ፖለቲከኛ ናቸዉ ።
ሙሉ ዉይይቱን የድምፅ ማድመጫ ማዕቀፉን በመቻን ይከታተሉ!
አዜብ ታደሰ