1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ውዝግቦችኢትዮጵያ

አማራ ክልል በጦርነቱ በርካታ ቢሊዮን ብር ግብር አልተሰበሰበም

ዓርብ፣ ኅዳር 14 2016

አማራ ክልል በቀጠለው ጦርነት የተነሳ መንግሥት በርካታ ቢሊዮን ብር ግብር ዘንድሮ መሰብሰብ አለመቻሉ ተገለጸ ። የአማራ ክልል የገቢዎች ጽ/ቤት ዘንድሮ በዓመቱ አራት ወራት ውስጥ 15 ቢሊዮን ብር ግብር ከፀጥታ ችግር ጋር በተያያዘ ሳይሰበሰብ መቅረቱን ለለዶይቸ ቬለ ዐስታውቋል ። በዚሁ ከቀጠለ በደመወዝ አከፋፈል ላይ ችግር ሊፈጥር ይችላል ተብሏል።

https://p.dw.com/p/4ZOrU
አማራ ክልል ገጠራማ መንገድ
አማራ ክልል አንድ ታጣቂ ገጠራማ መንገድ ላይ ነፍጥ አንግቦ ሲጓዝ ይታያል፤ ሌሎች ሰዎች ደግሞ ለዕለታዊ ክንውን ሸቀጦችን ተሸክመው ምስል AP/picture alliance

በዚህ ከቀጠለ ወደፊት ደሞዝ መክፈል ያዳግታል ተብሏል

አማራ ክልል በቀጠለው ጦርነት የተነሳ መንግሥት በርካታ ቢሊዮን ብር ግብር ዘንድሮ መሰብሰብ አለመቻሉ ተገለጸ ። ወቅታዊ የክልሉ የሰላም ሁኔታ በፈጠረው ጫና በቢሊዮን ብር የሚቆጠር ገቢ መሰብሰብ እንዳላስቻለው የአማራ ክልል ገቢዎች ጽ/ቤት ዐስታወቀ። ሁኔታው በዚሁ ከቀጠለ በደመወዝ አከፋፈል ላይ ችግር ሊፈጥር እንደሚፈጥርም አስታውቋል። የአማራ ክልል የገቢዎች ጽ/ቤት ዘንድሮ በዓመቱ አራት ወራት ውስጥ 15 ቢሊዮን ብር ግብር ከፀጥታ ችግር ጋ በተያያዘሳይሰበሰብ መቅረቱን ለለዶይቸ ቬለ ዐስታውቋል ። ሁኔታዎች በዚህ ከቀጠሉ ምናልባትም ወደፊት ለመንግሥት ሠራተኞች ደሞዝ መክፈል የማይቻልበት ደረጃ ሊደረስ እንደማይችል ተገልጿል ። አማራ ክልል ከዋና ከተሞች በስተቀር በአብዛኛው ወረዳዎች እና የገጠር ቀበሌዎች በፋኖ ታጣቂዎች ቁጥጥር ስር መሆኑ ይነገራል ።

በአማራ ክልል ከሐምሌ 2015 ዓ.ም መጨረሻ ጀምሮ የተፈጠረው የሰላም መደፍረስ በበርካታ የክልሉ አካባቢዎች በኢኮኖሚያዊና በማኅበራዊ እንቅስቃሴዎች ላይ ተፅዕኖ ፈጥሯል፤ በተለይም የክልሉን ገቢ ግብር ከመሰበሰብ አኳያ ታላቅ ጫና እንደፈጠረበትየአማራ ክልል ገቢዎች ጽ/ቤት አመልክቷል።

የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ

የቢሮው ኃላፊ አቶ ክብረት ማህሙድ በተለይ ለዶቼ ቬሌ በሰጡት መግለጫ ባለፉት 4 ወራት የተወሰነ ገቢ መሰብሰብ ቢቻልም እንደ አጠቃላይ ግን የግብር አሰባሰብ ሥራው እንቅፋት ተፈጥሮበታል ብለዋል። አቶ ክብረት እንዳሉት በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ሰላም በሆኑ አካባቢዎች ግብር ለመሰብሰብ ጥረት ቢደረግም መሰብሰብ የነበረበት 15 ቢሊዮን ብር ግብር ግን ለመሰብሰብ እንዳልተቻለ አብራርተዋል። ለግብር አሰባሰቡ ዋናው እንቅፋትም በክልሉ የተፈጠረው የሰላም መደፍረስ ተጠቃሽ እንደሆነ ነው አቶ ክብረት ተናገሩት። የገቢ ግብር በአግባቡ የሚሰበሰብ ካልሆነ ደግሞ በመንግስት ሠራተኛው ወርሀዊ ገቢ ላይ ከፍተኛ ችግር ሊፈጥር እንደሚችል ኃላፊው አመልክተዋል።

የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ፦ አቶ ክብረት ማህሙድ
የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ፦ አቶ ክብረት ማህሙድ በተለይ ለዶቼ ቬሌ በሰጡት መግለጫ በቢሊዮን የሚቆጠር ብር ዘንድሮ በግብር መሰብሰብ አልተቻለም ምስል Alemnew Mekonen/DW

የባለሞያ አስተያየት

የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ባለሞያ አቶ ይርጋ ተስፋዬ ለዶይቼ ቬሌ በሰጡት ተጨማሪ አስተያየት ሰላም በሌለበት ሁኔታምርትን አውጥቶ መሸጥ እንደማይቻልና ኢኮኖሚውም እንደሚዳከም አስረድተዋል። የጥሬ ገንዘብ እጥረት እንደሚከሰት የጠቆሙት አቶ ይርጋ የንግድ እንቅስቃሴውም ሕጋዊ ወዳልሆነ መስመር ይሔዳል ነው ያሉት። የመንገዶች መዘጋጋት ስለሚኖርም ገበሬው ምርቱን አውጥቶ ለመሸጥ እንደሚቸገር ገልጠዋል። በተለይ በሰፋፊ እርሻ የተሰማሩ ባለሞያዎች የባንክ ብድር መክፈል ስላማይችሉ ከፍተኛ ጫና ውስጥ እንደሚገቡና በቀጣይ ወደ ሥራ ለመግባት ይከብዳቸዋል ነው ያሉት።

የሰላም እጦቱ በኢንዱስትሪዎች ላይ የፈጠረው ጫና

በአማራ ክልል በተፈጠረው የሰላም መደፍረስ ምክንያት በክልሉ ከ 225 በላይ አነስተኛ፣ መካከለኛና ከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች ምርት ወደ ውጪ መላክና ጥሬ እቃ ወደ ፋብረካ ማስገባት ባለመቻላቸው በሺህ ከሚቆጠሩ ሠራተኞቻቸው ጋር ሥራ ማቆማቸውን ቀደም ሲል የክልሉ ንግድና ኢንቨስትመንት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ እንድሪስ አብዱ መግለፃቸው ይታወሳል።

ዓለምነው መኮንን

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር