1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በአማራ ክልል የንግድ ሥራ ድባቴ ተጭኖታል፤ ግብርና ሌላ ሥጋት ተጋርጦበታል

Eshete Bekele
ረቡዕ፣ ነሐሴ 17 2015

በደብረ ማርቆስ፣ ባሕር ዳር እና ጎንደር የሕዝብ እና የሸቀጥ ማጓጓዣ በቅጡ ሥራ አለመጀመሩን፤ የንግድ እንቅስቃሴ መቀዝቀዙን ነዋሪዎች ተናግረዋል። በአማራ ክልል ዘይት እና ሽንኩርትን በመሳሰሉ ሸቀጦች ላይ የዋጋ ጭማሪ ታይቷል። የአፈር ማዳበሪያ እጥረት የሚፈትነው ገበሬ በክልሉ በተፈጠረው ቀውስ ሳቢያ የሚደርስበት ተጽዕኖ ባለሙያዎችን አስግቷል

https://p.dw.com/p/4VVxa
የደብረ ማርቆስ ገበያ
በአማራ ክልል በተፈጠረው ቀውስ ምክንያት ደብረ ማርቆስ "ሁለት ሣምንት ሙሉ ከንግድ እንቅስቃሴ ውጪ" የከተማው ነዋሪ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። በከተማው የፍጆታ ዕቃ ንግድ እንቅስቃሴ የመነቃቃት አዝማሚያ ቢያሳይም ነዋሪው እንደሚሉት የመንግሥት ተቋማት ሥራ አልጀመሩም። ምስል DW/E. Bekele

በአማራ ክልል የንግድ ሥራ ድባቴ ተጭኖታል፤ ግብርና ሌላ ሥጋት ተጋርጦበታል

ከሦስት ሣምንታት ገደማ በፊት በአማራ ክልል የኢንተርኔት አገልግሎት ሲቋረጥ የኢንተርኔት ካፌ ባለቤት የሆኑት የደብረ ማርቆስ ከተማ ነዋሪ መተዳደሪያ ቆሟል። ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁት የደብረ ማርቆስ ነዋሪ እንደሚሉት ከአዲስ አበባ በ295 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቀት ላይ የምትገኘው ከተማ የለት ተለት እንቅስቃሴዋ ፈዟል። አዲስ አበባ እና ባሕር ዳርን ከመሳሰሉ ከተሞች የሚያገናኛት የመጓጓዣ አገልግሎት ተዳክሟል።

ከተማው "ሁለት ሣምንት ሙሉ ከንግድ እንቅስቃሴ ውጪ" እንደነበር የሚናገሩት የደብረ ማርቆስ ነዋሪ "የንግድ እንቅስቃሴ የጀመረው ዛሬ ነው። ዛሬ የፍጆታ ዕቃ [ንግድ] እንቅስቃሴ አለ" ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። ይሁንና "ማኅበራዊ አገልግሎት፣ ቢዝነስ ወይም የመንግሥት ተቋማት እስካሁን አገልግሎት አይሰጡም" ሲሉ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁት የደብረ ማርቆስ ነዋሪ የከተማውን ሁኔታ አስረድተዋል።

የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት መቀመጫ የሆነችው ባሕር ዳር እንደ ደብረ ማርቆስ ሁሉ ድባቴ ተጭኗታል። በድለላ ሥራ ላይ የተሰማሩት አቶ ብሩክ አጋዤ ደብረ ማርቆስ እና ጎንደርን ከመሳሰሉ ከተሞች ወደ ባሕር ዳር የነበረው የመጓጓዣ አገልግሎት መቀዛቀዙን ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። አቶ ብሩክ "የንግድ እንቅስቃሴውም ሙሉ በሙሉ ባይሆንም እንኳ 50 በመቶ" እንደቀነሰ ታዝበዋል።

የአማራ ክልል ከተሞች የሰዓት ዕላፊ ገደብና የዕለቱ እንቅስቃሴ

በአንዳንድ የግል ባንኮች "ጥሬ ገንዘብ የለንም" በሚል ምክንያት ማውጣት የሚቻለው 5,000 ብር ድረስ መሆኑን የገለጹት አቶ ብሩክ "በጥቅሉ የንግድ እንቅስቃሴው እንደ ሰንሰለት የተያያዘ ስለሆነ አሁን ፓሲቭነው ማለት ነው፤ አክቲቭ አይደለም" ሲሉ ተናግረዋል።

የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት መቀመጫ ባሕር ዳር ከተማ
የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት መቀመጫ በሆነችው ባሕር ዳር የንግድ እንቅስቃሴው እንደወትሮው እንዳልሆነ ዶይቼ ቬለ ያነጋገራቸው የከተማዋ ነዋሪ ተናግረዋል። ከጎንደር እና ከደብረ ማርቆስ ከተሞች ወደ ባሕር ዳር የነበረው የሕዝብ ማጓጓዣ አገልግሎትም ወደነበረበት አልተመለሰምምስል DW/J. Jeffrey

በደብረ ማርቆስ እና ባሕር ዳር ከተሞች የተፈጠረው ድባቴ የጎንደር ከተማን ጭምር የተጠናወተ ነው። የጎንደር ነዋሪ የሆኑት የሒሳብ እና ንግድ ሥራ አማካሪ አቶ አቶ ሳሙኤል ሙሉነህ "ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ያን ያክል አክቲቭ የምንለው እንቅስቃሴ የለም። [ጎንደር] ካለው ገናናነት፣ ካለው ኤኮኖሚያዊ እምቅ አቅም፣ ካለው እንቅስቃሴ አንጻር ያን ያክል አክቲቭ አይደለም" ሲሉ ተናግረዋል።

ደብረ ማርቆስ፣ ባሕር ዳር እና ጎንደርን ጨምሮ የአማራ ክልል ሐምሌ 28 ቀን 2015 በታወጀ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሥር ነው። በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች በመከላከያ ሠራዊት እና የፋኖ ታጣቂዎች መካከል በተደረገ ውጊያ በርካታ ሰዎች ተገድለዋል። በክልሉ በተፈጠረው ቀውስ "በብዙ ቦታዎች አካባቢያዊ የመንግሥት መዋቅሮች ጊዜያዊ መፍረስ እንዳጋጠማቸው" የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ነሐሴ 8 ቀን 2015 ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

የባሕር ዳር ነዋሪ የሆኑት የንግድ ሥራዎች አማካሪው አቶ እንዳልካቸው አቤ በክልሉ በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት "ከአዲስ አበባ መምጣት ያለባቸው ምርቶች ወደ አማራ ክልል ሳይመጡ ይቀራሉ፤ እንዲሁም ደግሞ ከአማራ ክልል ተነስተው ወደ አዲስ አበባ መሔድ የሚገባቸው ምርቶች ወደዚያ ባለመሔዳቸው የገበያ ንረት አጋጥሟል" ሲሉ ተናግረዋል። ዘይት፣ ሽንኩርት እና ድንችን በመሳሰሉ የምግብ ግብዓቶች ላይ የዋጋ ጭማሪ መታየቱን የገለጹት አቶ እንዳልካቸው "አጠቃላይ የግብርናም ይሁን በኢንዱስትሪ ምርቶች ላይ የገበያ ንረት አጋጥሟል" ሲሉ ተናግረዋል።

የጎንደር ከተማ
ዶይቼ ቬለ ያነጋገራቸው የጎንደር ነዋሪ በአማራ ክልል ከተፈጠረው ቀውስ በኋላ የከተማው እንቅስቃሴ በኃይል እንደተቀዛቀዘ ገልጸዋል። ከተማው "ካለው ገናናነት፣ ካለው ኤኮኖሚያዊ እምቅ አቅም፣ ካለው እንቅስቃሴ አንጻር ያን ያክል አክቲቭ አይደለም" ሲሉ ተናግረዋል።ምስል DW/J. Jeffrey

 

የአማራ ገበሬ ሌላ ቅርቃር

የአማራ ክልል ቀውስ የተቀሰቀሰው የኢትዮጵያ ገበሬ ፊቱን ወደማሳ ባዞረበት ክረምት ነው። ይኸ ቀውስ ከመቀስቀሱ በፊት የአፈር ማዳበሪያ እጦት የገጠማቸው ገበሬዎች የእርሻ ወቅት እንዳያመልጣቸው ሥጋታቸውን ሲገልጹ ቆይተዋል። በሰሜን ወሎ ዞን ሐብሩ ወረዳ በሚገኘው ስሪንቃ የግብርና ምርምር ማዕከል ተመራማሪው ዶክተር ሥዩም አሰፌ የአማራ ክልል ገበሬ ከአፈር ማዳበሪያ በተጨማሪ ምርጥ ዘር፣ ጸረ-አረም እና ጸረ-ተባይ የመሳሰሉ የግብርና ግብዓቶችን በቅጡ እንዳላገኘ ተናግረዋል።

ዶክተር ሥዩም እንደሚሉት ከዚህ ቀደም የጦርነት ቀጠና የነበረው የምሥራቅ አማራ አካባቢ በሐምሌ ወር በቂ ዝናብ ባለማግኘቱ ጤፍ አልዘራም። የዘራ ገበሬም ቢሆን በነሐሴ የአረም፣ ለተዘራው ሰብል ማዳበሪያ የመርጨት፣ ተባይን የመቆጣጠር እና ጎርፍ ከተከሰተ የመከላከል ሥራዎች ይጠብቁታል።

ዶክተር ሥዩም "የጸጥታ ሁኔታው አስጊ ከሆነ በተለይ አምራቹ ወጣት ኃይል ግብርናው ላይ እንዳያተኩር አሉታዊ ተጽዕኖ ይኖረዋል። ወጣቶች የጦር ቀጠና በሚባሉ አካባቢዎች ተንቀሳቅሰው የሚሰሩበት ሁኔታ እንዳልተፈጠረ ያሳያል" ሲሉ ተናግረዋል። "ባለው ሁኔታ [ገበሬዎች] ምርታቸውን ወደ ገበያ ለማቅረብ እንኳን የሚቸገሩበት ሁኔታ እንዳለ አስተውለናል" የሚሉት ዶክተር ሥዩም "የገበያ ቀናቶች መስተጓጎል" መፈጠሩን ገልጸዋል።  

የአፈር ማዳበሪያ ጥያቄ የሚያቀርቡ የአማራ ክልል ገበሬዎች
በአማራ ክልል በመከላከያ ሠራዊት እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ግጭት ከመቀስቀሱ በፊት የአፈር ማዳበሪያ ያልደረሳቸው ገበሬዎች አቤቱታቸውን እስከ ባሕር ዳር እየተጓዙ ሲያቀርቡ ነበር። ምስል Alemnew Mekonnen/DW

የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ዳፋ

በሰሜን ወሎ ዞን የሚገኘው ሲሪንቃ ግብርና ምርምር ማዕከል ሥራውን በቅጡ ለማከናወን እንደተቸገረ ዶክተር ሥዩም ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። የግብርና ምርምር ማዕከሉም ሆነ የወሎ አካባቢ ከሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ገና በቅጡ አላገገሙም። "አርሶ አደሩ በጣም ተጎድቷል። እንስሳቶቻቸው፣ ቤቱ ሁሉ የተቃጠለበት አርሶ አደር አለ። አሁን አንድ ቤት ለመሥራት ምን ያክል አስቸጋሪ እንደሆነ ይታወቃል። አንድ በሬ ለመግዛት አርሶ አደሩ ምን ያክል እንደሚያስፈልገው ይታወቃል" የሚሉት ዶክተር ሥዩም የአካባቢው ገበሬ ገና ከሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በቅጡ እንዳላገገመ ገልጸዋል።

ወሎ "የደረሰበትን ልቁጠር ብል በአገሬ ሰው የቀለድኩ ይመስለኛል" ከመርሳ የተፈናቀሉ ነጋዴ

"አርሶ አደሩን ሊያቋቁሙ የሚችሉ የብድር ተቋማት አሉ። እነዚያ ተቋማት ሥራቸውን በአግባቡ እየሰሩ እንዳልሆነ ይታያል" የሚሉት የግብርና ምርምር ባለሙያው "አርሶ አደሩን ከነበረበት ከዚያ ከፍተኛ ውድመት እንዲያገግም መሥራት ሲገባ ሌላ ተጨማሪ እንቅፋቶች መከሰታቸው" በምርት ላይ ሊያሳድር ከሚችለው ተጽዕኖ በተጨማሪ "የህልውና ሥጋት" መፍጠራቸውን ገልጸዋል።

የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ከትግራይ ወደ ደቡብ ሲገሰግስ በደረሰባቸው የአማራ እና የአፋር ክልሎች የሕክምና ተቋማት፣ ትምህርት ቤቶች እና ፋብሪካዎች ብርቱ ውድመት ደርሶባቸዋል። የክልሉ መንግሥት ባሰራው ጥናት በጦርነቱ  522 ቢሊዮንብር የሚደርስ ውድመት በአማራ ክልል ላይ ብቻ ደርሷል። የንግድ እና መዋዕለ-ንዋይ አማካሪው አቶ አብነት በላይ እንደሚሉት ጦርነቱ በክልሉ ለመሥራት ፍላጎት የነበራቸውን ባለወረቶች ጭምር አሽሽቷል።

ገበሬ ማሳ በማረስ ላይ
በስሪንቃ የግብርና ምርምር ማዕከል ተመራማሪው ዶክተር ሥዩም አሰፌ የአማራ ክልል ገበሬ ከአፈር ማዳበሪያ በተጨማሪ ምርጥ ዘር፣ ጸረ-አረም እና ጸረ-ተባይ የመሳሰሉ የግብርና ግብዓቶችን በቅጡ እንዳላገኘ ተናግረዋል። ዶክተር ሥዩም እንደሚሉት ከዚህ ቀደም የጦርነት ቀጠና የነበረው የምሥራቅ አማራ አካባቢ በሐምሌ ወር በቂ ዝናብ ባለማግኘቱ ጤፍ አልዘራም።ምስል Alemnew Mekonnen/DW

ጦርነቱ ከመቀስቀሱ በፊት በደብረ ብርሀን፣ ደሴ፣ ኮምቦልቻ እና ባሕር ዳር ዙሪያ በጣም "ከፍተኛ የሆነ 'የኢንቨስት እናድርግ' ጥያቄ ከተለያዩ ነጋዴዎች" ቀርቦ እንደነበር የንግድ እና መዋዕለ-ንዋይ አማካሪው አቶ አብነት በላይ ተናግረዋል። "በባሕር ዳር ዙሪያ ብቻ ወደ 600 'ኢንቨስት እናድርግ፤ ሥራ እንሥራ' የሚል ጥያቄ አቅርበው መሬት እስኪሰጣቸው የሚጠባበቁ ነጋዴዎች ነበሩ" ያሉት አቶ አብነት ሁሉም ጦርነት ሲቀሰቀስ እንደቆመ አስረድተዋል።

  ጦርነቱ የአማራ ብድር እና ቁጠባ ተቋምን ከ6 ቢሊዮን ብር በላይ አክስሯል ፤ ተቋሙ

"እነዚህ ከ600 በላይ የሆኑ ኢንቨስተሮች ሊፈጥሩት የሚችሉት የሥራ ዕድል ለክልሉ ሊፈጥሩት የሚችሉት ገቢ እና ያገቢ ቀጥታ ወደተለያየ የኤኮኖሚ ዘርፍ ተሰራጭቶ ክልሉ ላይ ሊፈጥረው የሚችለው አዎንታዊ ተጽዕኖ በጦርነቱ የተነሳ ቆሟል ማለት ነው" የሚሉት አቶ አብነት ወሎ፣ ጎንደር እና ሸዋ በጦርነቱ ከደረሰባቸው የኤኮኖሚ ውድመት ለማገገም "ከአስር እና ከአስራ አምስት ዓመታት በላይ" እንደሚፈጅባቸው ይገምታሉ።

የአማራ ክልል ቀውስ፦ ገፊ ምክንያቶች፣ ዳፋው እና በውይይት የመቋጨት ተስፋ

ከአማራ ክልል በተጨማሪ በትግራይ እና አፋር ክልሎች ብርቱ ሰብአዊ ቀውስ ያስከተለው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት አገሪቱን ለ28.7 ቢሊዮን ዶላር ኪሳራ ዳርጓታል። መንግሥት ላቀደው መልሶ ግንባታ 19.7 ቢሊዮን ዶላር ይፈልጋል።

ዶይቼ ቬለ ያነጋገራቸው የደብረ ማርቆስ፣ ባሕር ዳር እና ጎንደር ነዋሪዎች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከተደነገገ ወዲህ በየከተሞቻቸው የነበረው ውጥረት መርገቡን ቢታዘቡም ጉዳዩ ኹነኛ መፍትሔ ለማግኘቱ እርግጠኛ አይደሉም። የክልሉ የንግድ እንቅስቃሴ እና የግብርና ሥራ የገጠሟቸውን ፈተናዎች የታዘቡት ባለሙያዎችም ቢሆኑ ቀውሱ መፍትሔ ካላገኘ የሚያስከትለው ዳፋ ያሰጋቸዋል።

ኢትዮጵያ ከ19 ቢሊዮን ዶላር በላይ ለሚፈጅ መልሶ ግንባታ የሚሆን ፋታ አላት?

አቶ እንዳልካቸው ግን "ችግሩን ቁጭ ብሎ መነጋገር ያስፈልጋል። ምክንያቱም መጋጨት፤ የአንዲት አገር ሰዎች በሁለት ጎራ ሆኖ ተከፋፍሎ ጦርነት ማካሔድ ምን ያክል ዋጋ እንዳስከፈለ የትላንትና ታሪክ ነው። ዛሬም ይኸ የሚደገም ከሆነ በጥፋት ላይ ጥፋት ከመጨመር ውጪ ሌላ ጠቀሜታ የለውም" ሲሉ ያስጠነቅቃሉ።

እሸቴ በቀለ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ዘገባና ትንታኔ

ዘገባና ትንታኔ