1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በዞሊንገን ሦስት ሰዎች ስለ ተገደሉበት ጥቃት መረጃ ነበረው የተባለ ተጠርጣሪ በቁጥጥር ሥር ዋለ

ቅዳሜ፣ ነሐሴ 18 2016

በምዕራብ ጀርመን በምትገኘው ዞሊንገን ከተማ ሦስት ሰዎች ከተገደሉበት እና ሌሎች ስምንት ከቆሰሉበት ጥቃት ጋር ግንኙነት ሳይኖረው አይቀርም የተባለ ተጠርጣሪ በቁጥጥር ሥር መዋሉን የሀገሪቱ ባለሥልጣናት አስታወቁ። ፖሊስ ለጥያቄ ይፈለጋል በሚል በቁጥጥር ሥር የዋለው የ15 ዓመት ታዳጊ እንደሆነ አስታውቋል።

https://p.dw.com/p/4jsws
የጀርመን ፖሊስ
በዞሊንገን ከተማ ሦስት ሰዎች ተገድለው ስምንት የቆሰሉበትን ጥቃት ተጠርጣሪ በቁጥጥር ሥር ለማዋል ልዩ ፖሊሶችን ጨምሮ የጀርመን የጸጥታ ኃይሎች ኃይለኛ ፍለጋ  እያደረጉ ነው። ምስል Christoph Reichwein/dpa/picture alliance

በምዕራብ ጀርመን በምትገኘው ዞሊንገን ከተማ ሦስት ሰዎች ከተገደሉበት እና ሌሎች ስምንት ከቆሰሉበት ጥቃት ጋር ግንኙነት ሳይኖረው አይቀርም የተባለ ተጠርጣሪ በቁጥጥር ሥር መዋሉን የሀገሪቱ ባለሥልጣናት አስታወቁ። ፖሊስ ለጥያቄ ይፈለጋል በሚል በቁጥጥር ሥር የዋለው የ15 ዓመት ታዳጊ እንደሆነ አስታውቋል። መርማሪዎች ዛሬ ቅዳሜ በሰጡት መግለጫ በስለት ጥቃት የፈጸመው ተጠርጣሪ ማንነት እንዳልታወቀ እና ፍለጋ እየተካሔደ መሆኑን ገልጸዋል። 

መራኄ መንግሥት ኦላፍ ሾልስ “ጥቃት ፈጻሚው በፍጥነት በቁጥጥር ሥር ውሎ በሕግ ሙሉ ኃይል ሊቀጣ ይገባል” ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል። ሾልስ “በዞሊንገን የተፈጸመው ጥቃት በጣም ያሳዘነኝ አስከፊ ክስተት ነው” ብለዋል።

 በጀርመን ዞሊንገን ከተማ ሦስት ሰዎች ስለ ተገደሉበት ጥቃት መረጃ ነበረው የተባለ ተጠርጣሪ በቁጥጥር ሥር ዋለ

ከኮሎኝ በቅርብ ርቀት ላይ በምትገኘው ዞሊንገን ትላንት አርብ ምሽት በተጸፈመው ጥቃት ሁለት ወንዶች እና አንዲት ሴት ተገድለዋል። በፖሊስ መረጃ መሠረት በጥቃቱ ከቆሰሉ ስምንት ሰዎች መካከል አምስቱ ብርቱ ጉዳት የደረሰባቸው ናቸው።  

ጥቃቱ የተፈጸመው ዞሊንገን የተመሠረተችበት 650ኛ ዓመት ሲከበር በተዘጋጀ የሙዚቃ ድግስ አጠገብ ነው። በስለት የሰለባዎቹን አንገት ላይ አነጣጥሮ ተፈጽሟል የተባለው ጥቃት ገፊ ምክንያት እስካሁን አልታወቀም። በጥቃቱ ሳቢያ እስከ ነገ እሁድ ሊካሔድ የታቀደው ፌስቲቫል እንዲቋረጥ ተደርጓል።

ምርመራውን የሚመሩት ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ማርኩስ ካስፐርስ “የጥቃቱ መነሾ ምን እንደሆነ ድምዳሜ ላይ አልደረስንም። ነገር ግን አጠቃላይ ሁኔታዎች ላይ በመመሥረት በሽብርተኛ አነሳሽነት የተፈጸመ ጥቃት ሊሆን ይችላል የሚለው የመጀመሪያ ጥርጣሬ ውድቅ ሊሆን ይችላል ብለን አንገምትም” ሲሉ ዛሬ ቅዳሜ ተናግረዋል። 

የጀርመን ፖሊስ
መራኄ መንግሥት ኦላፍ ሾልስ “ጥቃት ፈጻሚው በፍጥነት በቁጥጥር ሥር ውሎ በሕግ ሙሉ ኃይል ሊቀጣ ይገባል” እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል።ምስል Thilo Schmuelgen/REUTERS

ታዳጊው በቁጥጥር ሥር የዋለው ስለ ጥቃቱ መረጃ ኖሮት ለባለሥልጣናት ሳያሳውቅ በመቅረት ተጠርጥሮ እንደሆነ ፖሊስ ገልጿል። “ማንነቱ የማይታወቅ ግለሰብ ከጥቃቱ በፊት ተመሳሳይነት ያለው ወንጀል ለመፈጸም ያለውን ዕቅድ ከታዳጊው ጋር መወያየቱን” የዐይን እማኞች እንደተናገሩ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ማርኩስ ካስፐርስ ገልጸዋል።

በናዚ ጀርመን በግፍ የተጨፈጨፉት የሲንቲ ሮማዎች 80ኛ ዓመት መታሰቢያ በአውሮጳ 

ከጥቃቱ በኋላ የሸሸውን ተጠርጣሪ በቁጥጥር ሥር ለማዋል ልዩ ፖሊሶችን ጨምሮ የጀርመን የጸጥታ ኃይሎች ኃይለኛ ፍለጋ  እያደረጉ ነው። የጀርመን ፕሬዝደንት ፍራንክ ቫልተር ሽታይን ማየር የሀገሬው ሰዎች “በጋራ ጥላቻ እና ኹከትን” እንዲቃወሙ ጥሪ አቅርበዋል።