በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን የታጣቂዎች ጥቃት
ዓርብ፣ መስከረም 4 2016በኦሮሚያ ክልል ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን ታጣቂዎች በሦስት ወረዳ ፖሊስ ጣቢያዎች ላይ ጥቃት ማድረሳቸው ተነግሯል፡፡ ጥቃቱ በውል ባልታወቁ ታጣቂዎች በቱሉ ቦሎ፣ በኢሉ ገላን ወረዳ ተጂ ከተማ እና በሰደን ሶዶ ወረዳ አርቡ ጩሉሌ ከተማ መፈጸሙ ነው የተገለጸው።
የአዲሱ ዓመት መስከረም 01 ቀን፣ 2016 ዓ.ም. በበዓሉ እለት ሌሊት በሦስቱ ወረዳዎች ላይ በተመሳሳይ ቀን በተቀራራቢ ሰዓት በታጠቁ አካላት ተጠርጥረው የታሰሩ ሰዎች በሚገኙባቸው ፖሊስ ጣቢያዎች ላይ ባነጣጠረው ጥቃት የሰው ሕይወት ስለማለፉም ተነግሯል፡፡
ጥቃቶቹን ማን አደረሰ?
ለደህንነታቸው ሲባል ስማቸው እና የሚኖሩበት ከተማ ተለይቶ እንዳይገለጽ ጠይቀው አስተያየታቸውን የሰጡን አንድ የዞኑ ነዋሪ ተጨባጭ ብለው በሰጡን አስተያየታቸው በቱሉ ቦሎ እና በሰደን ሶዶ ወረዳ አርቡ ጩሉሌ ከተማ በስም ጭምር የሚያውቃቸው ፖሊሶች መገደላቸውንና በተለያዩ ወንጀሎች ተጠርጥረው የታሰሩ መለቀቃቸውን ገልጸዋል ። እንደ እኚ አስተያየት ሰጪ ማብራሪያ የመስከረም 1 ቀን፣ 2016ቱ ክስተት ከሁለቱ ወረዳዎች በተጨማሪ በኢሉ ገላን ወረዳ ተጂ ከተማም መከሰቱን መረጃ ቢኖራቸውም በጥቃቱ የደረሰውን ጉዳት መጠን ግን እንደማያውቁ አስረድተውናል ።
በኦሮሚያ ክልል ሰላምና መረጋጋትን ለማምጣት ድጋፍ ተጠየቀ
«በሁለቱ ወረዳዎች በሰደን ሶዶ እና በቾ ወረዳ ቱሉ ቦሎ ከተማ የሰው ህይወት አልፏል። ከሞቱት መካከል ደግሞ በበቾ እኔም የማውቀው ፖሊስ አለ፡፡ ከዚህ በእለቱ ከሞተው ፖሊስ በተጨማሪ አንድ የማውቀው ሌላኛው ፖሊስም ቆስሎ አሁን በህክምና ላይ ነው። በዚህ በቱሉ ቦሎ ፖሊስ ጣቢያ እነዚህ ታጥቀው በጫካ የሚንቀሳቀሱትን ትደግፋላችሁ ተብለው ተጠርጥረው የታሰሩ በርካቶች ነበሩ። በእለቱ እኩለ ሌሊት ስድስት ሰዓት ገደማ ጀምሮ እስከ አስር ሰኣት በቀጠለው የተውክስ ልውውጥ እስረኞቹ መለቀቃቸውን ሰምተናል።»
እኚው አስተያየት ሰጪ አክለው እንደነገሩን በሰደን ሶዶ ወረዳ አርቡ ጩሉሌ ከተማም በተመሳሳይ እለት ከሌሊት 4፡00 ሰዓት እስከ 8፡00 ሰዓት ተደርጓል ባሉት የተኩስ ልውውጥ እስረኞች መለቀቃቸው፣ የሁለት ፖሊስ ሕይወት ማለፉና ፖሊስ ጣቢያው ላይ ጉዳት መድረሱን ተናግረዋል። «በሰደን ሶዶ ጩሉሌ ከተማ ደግሞ ሁለት ሰው ከፖሊስ መካከል እንደሞቱ አረጋግጫለሁ። ጥቃት አድራሾቹ ፖሊስ ጣቢያውንም አቃጥለውታል። ተኩስ ልውውጥ የነበረው ከምሽት 4 ሰኣት እስከ ሌሊት 8 ሰዓት ነበር። የተኩስ ልውውጡ ያው ከሁለት አቅጣጫ ስለነበር ጠንካራ ነው የነበረው። በእለቱ ሌላው አደጋ የደረሰው በኢሉ ወረዳ ተጂ ከተማ ቢሆንም በዚያ ላይ ተጨባጭ ዝርዝር መረጃ የለኝም፡፡ ስለሁለቱ ወረዳዎች ግን እንደነገርኩህ ነው።»
መንግስት ሸኔ ያለውና እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ብሎ የሚጠራው ታጣቂ ቡድን
አስተያየት ሰጪያችን የተውክስ ልውውጡ ሌሊት የተፈጸመ እንደመሆኑ ከመላምት ውጪ በማን እና በማን መካከል ተከናወነ ነው ለሚለው ጥያቄ አስረግጠው የሚሰጡት ምላሽ አለመኖሩን ገልጸውልናል። በነዚህ ወረዳዎች ከየፖሊስ ጣቢዎቹ ከተለቀቁት መካከል ግን አሁን ላይ ታጥቆ መንግስትን የሚፋለመው መንግስት ሸኔ ያለውና እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ብሎ የሚጠራው ታጣቂ ቡድንን በመደገፍ ተጠርጥረው የታሰሩ ወጣቶች ነበሩ ብለዋል።
ስለዚህ ጥቃት እና ስለደረሰው ጉዳት እስካሁን በመንግስት በኩል የተባለ ነገር የለም። ዶይቼ ቬለ ለተከታታይ ሁለት ቀናት በጉዳዩ ላይ አስተያየት እንዲሰጡበት ለደቡብ ምእራብ ሸዋ ዞን ኮሚዩኒኬሽን ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኃይሉ አብዶ ቢደውልም ስብሰባ ላይ መሆናቸውን ገልጸው ጥያቄውን በጽሁፍ እንድንልክላቸው በጠየቁን መሰረት ጥያቄውን ብንልክላቸውም እስካሁን ምንም አስተያየት አልሰጡበትም።
አንድ የዞኑ የመንግስት ባለስልጣን ግን ኃላፊነታቸው ባለመሆኑ በጉዳዩ ላይ ዝርዝር መረጃ ባይሰጡም የጥቃቱን መፈጸም አረጋግጠውልናል። «በኢሉ ወረዳ ሙከራ ተደርጎ ነበር። በተደረገው ሙከራ ሁለት ፖሊሶች አልፈዋል፡፡ ከዚህ ባለፈ ግን በዚያ የከፋ ችግር አልተፈጠረም። በበቾ እና ሰደን ሶሰዶ ወረዳዎችም የተደረገው ተመሳሳይ የጥቃቱ ሙከራ አለ። ያው አሁን እኔ ኃላፊነቴ ስላልሆነ ሙሉ መረጃ ለመስጠት እቸገራለሁ።»
ፍሬ ያላፈራው የሰላም ድርድር
በኦሮሚያ ክልል በኢትዮጵያመንግስት እና በኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት መካከል ከዚህ በፊት በታንዛንያ የተሞከረው የሰላም ድርድርፍሬ ሳያፈራ ከተቋረጠ ወዲህ በተለያዩ አከባቢዎች የሚደረገው ደም አፋሳሽ ግጭት ማገርሸቱ ይነገራል። መንግስትን በትጥቅ በሚፋለመው ታጣቂ ቡድኑ ከዚህ በፊት በቡሌ ሆራ፣ ባቱ፣ ወለንጪቲ፣ ነቀምቴ እና ሌሎችም አከባቢዎች በፖሊስ ጣቢያ የሚገኙ ታሳሪዎችን የማስለቀቅ ሙከራን ያነገበ ጥቃት መፈጸሙን ከዚህ በፊት በተለያዩ ጊዜያት መዘገቡ አይዘነጋም።
ሥዩም ጌቱ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ታምራት ዲንሳ