አዲስ ጥቃት በምዕራብ ጎጃም
እሑድ፣ ኅዳር 2 2016
የኦሮሚያ ክልል ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን አሙሩ ወረዳ አዋሳኝ በሆነው በአማራ ክልል ምዕራብ ጎጃም ቡሬ ወረዳ በተቀሰቀሰው አዲስ ግጭት የሰዎች ህይወት መቀጠፉ ተነገረ፡፡
ከዓርብ ጥቅምት 30 2016 ዓ.ም. ጀምሮ የታጠቁ አካላት በወረዳው ሶንቶም እና በቆ ጣቦ በሚባሉ ቀበሌያት አደረሱ በተባለው ጥቃት ቢያንስ የሰባት ሰዎች ህይወት ሲልፍ ንብረት መዘረፉና ከሁለቱ ቀበሌያት ሰዎች መፈናቀላቸው ተገልጿል፡፡
አስተያየታቸውን ለዶቼ ቬለ የሰጡ ተፈናቃዮች ብሔር ተኮር ባሉት በዚህ ጥቃት የተፈናቀለ ማህበረሰብ በከፊል ወደ ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ አሙሩ ወረዳ ሲሸሹ በርካቶች ደግሞ በየጫካው ተበታትነው እንደሚገኙ አመልክተዋል፡፡
የጥቃቱ ሰለቦች አስተያየት
በአማራ ክልል ምዕራብ ጎጃም ዞን ቡሬ ዙሪያ ወረዳ የበቆ ጣቦ ቀበሌ ነዋሪ መሆናቸውን ገልጸው፤ ለደህንነታቸው ሲባል ግን ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁን አስተያየት ሰጪ ዓርብ ከእኩለ ቀን ጀምሮ ተከስቷል ባሉት ግጭት ቢያንስ ለ7 ሰዎች ህልፈት ምክኒያት ሆኗል፡፡ ጥቃቱ ብሔር ላይ ያነጣጠረ ነበር ያሉት አስተያየት ሰጪው ጥቃቱን በፈጸሙ ታጣቂዎች ዘረፋ እና ውክቢያም ተከናውኗል ብለዋል፡፡ “እኛ ከቅድመ አያታችን ጀምሮ ነው በዚህ ነው የኖርነው፡፡ ጥቅምት 30 ዓርብ ከቀኑ ስድስት ሰዓት ጀምሮ ድብደባው ቀጥሏል ነው፡፡ እኛ ሰላም ብለን በተቀመጥንበት ነው ፋኖ የተባሉ ታጣቂዎች መጥተው ተኩስ የከፈቱብን፡፡ እርግጠኛ ሆኜ መናገር የምችለው ቢንስ ሰባት ሰው ተገድሏል፡፡ ብዙ ሰው ወዴት እንደገባ አይታወቅም፡፡ ከብት የለ፤ የቤት እቃ እንዳለ ጥቃቱን በፈጸሙ ታጣቂዎች ተወስዷል” ሲሉም አስተያየታቸውን አክለዋል፡፡
ሌላኛው አስተያየት ሰጪ ደግሞ ከሶንቶም ቀበሌ መሆናቸውን ገልጸው ከዓርብ ጀምሮ ተከስቷል ያሉትን የአከባቢው ጸጥታ መናጋቱን የገለጹልን፡፡ “የተፈጠረው ነገር ጣቦ በሚባል የበረሃ ቀበሌ ላይ ህዝብ እህላችንን ጭነን እንውጣ ሲሉ አትወጡም በሚል በተጀመረው ጠብ ነውውጊያ የተከሰተው፡፡ በዚህ በሰንቶም ሁለት ሚሊሻ ገድለዋል፡፡ እስካሁን ሬሳም አልተነሳም፡፡ ህብረተሰቡ አሁን ወንዙን በዋናም በምንም ተሻግረው ወደ ኦሮሚያ ክልል የሸሹ አሉ፡፡”
ስሜን መግለጽ አልፈልግም ያሉት ሌላኛው አስተያየት ሰጪም ከዓርብ እኩለ ቀን የጀመረው አለመረጋጋት በሁለቱ ቀበሌያት እንደ ቀጠለ ቢሆንም የደረሰልን የጸጥታ አካል የለም ብለዋል፡፡ “እስካሁን ምንም ሳይቀር ንብረት ተዘርፏል፡፡ ወጥተን ለመጠጋት መንገድ አስጊ በመሆኑ ህጻናት ይዘን ጫካ ላይ ነን አሁን” በማለት አስረድተዋል፡፡
እንደ አስተያየት ሰጪዎቹ በዚህ በቡሬ ወረዳ በተለይም ሰንቶም እና በቆ ጣቦ በተባሉ ሁለት ቀበሌያት በስፋት የኦሮሞ ተወላጆች ይኖራሉ፡፡ የዓርቡ ጥቃትም ድንገተኛ ነበር ያሉት አስተያየት ሰጪዎቹ አሁን ላይ ቤተሰብ ተበታትኗል ነው ያሉት፡፡
በጉዳዮ ላይ የባለስልጣናት ምላሽ
ስለ ተፈናቃዮቹ እሮሮ እና አሁን ላይ በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ አጋጥሟል ስለተባለው አዲስ ግጭት ላይ ተጨማሪ ማብራሪያ እና ማረጋገጫዎችን ለማግኘት ለአማራ ክልል ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ የስራ ኃላፊዎች በስልክ እና በጽሁፍ መልእክት ጭምር ያቀረብነው ጥያቄ ለጊዜው ምላሽ አላገኘም፡፡
በኦሮሚያ ክልል በኩል በአሙሩ ወረዳ የአዋሳኙ ጆጅ ቀበሌ ሃላፊ አቶ ሲሳይ አቦዋይ ለዶቼ ቬለ እንደገለጹት ግን በርካታ ቁጥር ያላቸው ተፈናቃዮች ከአማራ ክልል ተነስተው አባይ ወንዝን እየተሻገሩ ወደ ቀበሌያቸው እየፈለሱ ነው፡፡ “እስካሁን በእጄ ላይ የያዝኩት ዳታ ትንሽ ነው፡፡ እስካሁን የመዘገብናቸው 550 ደርሰዋል። ህዝብ ወደኛ እየጎረፈ ነው፡፡ አባይን ተሻረው ወደ እኛ እየመጡ በትምህርት ቤት ውስጥ እያሰፈርናቸው ነው፡፡ የጽንፈኞች ጥቃት ነው ያፈናቀላቸው፡፡ አሁን እየደረሱ ያሉ የተቸገሩ ህጻናት እና አዛውንቶች ጭምር ነው፡፡ መኪና ከዚህ ከአገምሳ ከተማ እየላክን አባይ ወንዝ ላይ አቁመን ነው ከዚያ የሚያመጧቸው፡፡ የታመሙ ሰዎች ጭምር ይገኙበታል፡፡”
በምእራብ ኦሮሚያ በተለይም አማራ ክልልን በሚያዋስኑ አከባቢዎች ላለፉት ጥቂት ዓመታት የተከሰተው ግጭት ለበበርካቶች ህልፈትና መፈናቀል ምክኒያት ነበር፡፡ በነዚህ አከባቢዎች ከሰሞኑ ተፈናቃዮችን ወደ ቀዬያቸው ለመመለስ የሁለቱ ክልሎች አመራሮች ጥረት በማድረግ ላይ እንደነበሩም መዘገባችን ይታወሳል፡፡
ሥዩም ጌቱ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር