በትግራይ በወባ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በ60 በመቶ መጨመሩ የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ
ቅዳሜ፣ ሰኔ 29 2016በትግራይ ክልል በወባ በሽታ የሚለከፉ ሰዎች ቁጥር በስልሳ በመቶ መጨመሩ የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ። በክልሉ የአጎበር ተደራሽነት መጠን መቀነስ፣ የመድሃኒቶች ውሱንነት እና ሌሎች የበሽታው ስርጭት እንዲጨምር እንዳደረገው ተነግሯል። በሌላ በኩል የህፃናት ክትባት በክልሉ ላሉ ሁሉም ህፃናት ለማዳረስ ጥረት እየተደረገ መሆኑ ተመልክቷል።
ጦርነቱ ተከትሎ በትግራይ የጤና ስርዓቱ በመፍረሱ እንዲሁም በሌሎች ተደራራቢ ችግር ምክንያት በክልሉ ወባ ጨምሮ የተለያዩ በሽታዎች እየተንሰራፉ፥ የስርጭት መጠናቸው እየጨመረ መሆኑ መረጃዎች ያመለክታሉ።
የትግራይ ክልል ጤና ቢሮ እንደሚለው በትግራይ ሰሜን ምዕራብ ዞን፣ ማእከላዊ ዞን ወርዒ አካባቢ እና ራያ ዓዘቦ በአጠቃላይ 18 ወረዳዎች የወባ በሽታ በስፋት እየታየ መሆኑ የሚገልፅ ሲሆን በተለይም በአስር ወረዳዎች በሽታው በወረርሽኝ ደረጃ እየተንሰራፋ መሆኑ አመልክቷል።
በትግራይ ጤና ቢሮ የበሽታዎች ቁጥጥርና መከላከል ዘርፍ ሐላፊ አቶ አረጋይ ገብረመድህን "ከ18 እስከ 20 በሚሆኑ ወረዳዎች ከፍተኛ የወባ በሽታ ዝርጋታ የሚታይባቸው ናቸው። ከእነዚህ መካከል አስር በሚሆኑት ወረዳዎች የወባ በሽታ በወረርሽኝ ደረጃ የሚታይባቸው ናቸው" ብለዋል።
በተለይም በያዝነው ግንቦት እና ሰኔ ወራት የወባ በሽታ ስርጭት በትግራይ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱ ሐላፊው ጨምረው የሚገልፁ ሲሆን አስቀድሞ የነበረው በሳምንት የሚመዘገብ አራት ሺህ ገደማ የወባ በሽታ ተጠቂዎች መጠን አሁን ላይ ወደ ሰባት ሺህ ማደጉ አመልክተዋል።
ኃላፊው "አሁን ባለው የግንቦት እና ሰኔ የወባ በሽታ ስርጭት መጠን ስንመለከተው፥ ካለፈው ግዜ ጋር ሲነፃፀር 60 በመቶ በሚሆን ነው የጨመረው። በሳምንት በወባ የሚለከፉ ሰዎች ቁጥር ከአራት ሺህ ወደ ሰባት ሺህ የጨመረ በመሆኑ፥ 60 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል ማለት ነው" ሲሉ አክለዋል።
በክልሉ የወባ አምጪ እንስሳ መከላከያ አጎበር እጥረት ማጋጠሙ የሚገልፀው የትግራይ ጤና ቢሮ መዳረስ ከሚገባው አጠቃላይ የአጎበር መጠን እስካሁን የተገኘው እና የተሰራጨው 50 በመቶ ብቻ መሆኑ ይገልፃል። በመድሃኒት በኩልም ቢሆን እጥረት ቢኖርም ከፌዴራሉ መንግስት ይህ ለማገዝ እየተሰራ መሆኑ ተመልክቷል።
የትግራይ ጦርነት ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸዉ መመለስ ጀመሩ
በሌላ በኩል በትግራይ በጦርነቱ ምክንያት በተደጋጋሚ ሲስተጓገል የነበረ የህፃናት ክትባት ሙሉ በሙሉ ለማዳረስ ጥረቶች መቀጠላቸው የክልሉ ጤና ቢሮ ይገልፃል። የትግራይ ጤና ቢሮ ሐላፊ ዶክተር አማኑኤል ሃይለ ክትባት ያላገኙ ወይም ያቋረጡ በትግራይ ያሉ ህፃናት ለመለየት ዘመቻ መጀመሩ ተናግረዋል።
ዶክተር አማኑኤል "ክትባት ፈፅሞ ያልወሰዱ አልያም ያልጀመሩ፣ ጀምረው ያቋረጡ ህፃናት፣ ዕድሜያቸው ደግሞ ከአምስት አመት በታች የሆኑት፥ ቤት ለቤት በሚደረግ ዳሰሳ ለይተን ልናውቃቸው፥ አውቀን ደግሞ ልንከትባቸው የምንጀምረው ዘመቻ ነው" ብለዋል።
ሚሊዮን ኃይለሥላሴ
እሸቴ በቀለ