በምስራቅ ወለጋ ስጋትን አስከትሏል የተባለው የትጥቅ ማስፈታት ዉሳኔ
ማክሰኞ፣ ጥቅምት 19 2017
በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ወለጋ ዞን ኪረሙ እና ጊዳ አያና ወረዳዎች የሚኖሩ የአማራ ተወላጆች ትጥቅ እንዲፈቱ መወሰኑን ተቃወሙ።ነዋሪዎቹ እንደሚሉት በአከባቢው ሠላምና ፀጥታ ሳይሰፍን ጥቅት ከፈቱ ለጥቃት ይጋለጣሉ።ተቃዋሚዉ እናት ፓርቲም ዉሳኔዉ ዜጎችን ለጥቃት ያጋልጣል ብሎታል። የአከባቢው ባለስልጣንት ግን ትጥቅ የማስፈታትና የማደራጀቱ ዓላማ በአከባቢው ሰላምን ለማጽናት እንጂ ዜጎች እንዲጠቁ ታስቦ አይደለም ፤ ውሳኔውም ለሁሉም ብሔር እኩል የሚሰራ ነው ብለዋል፡፡
የነዋሪዎቹ ሥጋት ምክንያት
በምስራቅ ወለጋ ዞን የኪረሙ ወረዳ ነዋሪው አስተያየታቸውን ከሰጡን ናቸው፡፡ እንደ እኚህ አስተያየት ሰጪ፤ መንግስት ለአከባቢው ማህበረሰብ ሁሉም ይህንኑን ትጥቅ የማስፈታት ውጥኑን ይፋ ብያደደርግም ያንኑን በአዎንታዊነት ለመቀበል አስቸግሮናል ስላሉት ስጋታቸው እንዲህ አጋርተውናል፡፡ “አዎን እንግዲህ መንገዱም አልተከፈተም፡፡ ሰላሙ አልመጣም፡፡ ዙሪያውን የሸነ ታጣቂዎች አሉ፡፡ እናም ሰላም ባልሰፈነበት ሁኔታ ትጥቅ አውርዱ መባሉ ለኛ ስጋት አለው ብለን ስላሰብን ውሳኔውን ለመቀበል ተቸግረናል” ነው ያሉት፡፡
አስተያየት ሰጪው እንደሚሉት አሁን ላይ ትጥቅ እንዲፈቱ እየተጠየቁ ያሉት የአከባቢው ሚሊሻ የነበሩና ከዚህ በፊት ከመንግስት ሰራዊት ጎን ሆነው የአከባቢውን ሰላም ለማስጠበቅ ስንቀሳቀሱ የነበሩ ናቸው፡፡ “ያው ከዚህ በፊት በአከባቢው ባሉት ወረዳዎች ሰላምን በማስጠበቅ ላይ ተሰማርቶ የነበረ ሚሊሻ ነው፡፡ ያ ውለታ አሁን ተረስቶ ነው ከዚህ በፊት በነቂስ ወጥተን በህጋዊነት ያስመዘገብነውን መሳሪያ ነው ፊቱ እያሉን የሚገኙት” ብለዋል፡፡
ከጊዳ አያና ወረዳ አንዶዴ ቀበሌ አስተያየታቸውን ያከሉ ሌላው የአከባቢው ነዋሪ፤ “መንግስት ምን እንዳሰበ አናውቅም አሁን ስጋት ባለበት ነው መሳሪያ ፊቱ የሚለን፡፡ እንደ ቀበሌያችነን ካለው 688 አሁን ገና ሁለት መሳሪያ ብቻ ነው ያስፈቱት” ብለዋል፡፡
በጉዳዩ የአእናት ፓርቲ መግለጫ
እናት ፓርቲ ጉዳዩን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ በምሥራቅ ወለጋ ዞን ጊዳ አያና ወረዳ አንዶዴ ዲቾ ቀበሌ ማንነትን ማዕከል ያደረገ የከፋ እልቂት ከፊታችን ተደቅኗል፤ ያሉትን ነዋሪዎች አስተያየት መቀበሉን አስረድቶ፤ "መተማመን ባልሰፈነበት" የትጥቅ አውርዱ ጥያቄን ማህበረሰቡ ለመቀበል መቸገሩን አመልክቷል፡፡
የእናት ፓርቲ ከፍተኛ አመራር ጌትነት ወርቁ ለዶቼ ቬለ በሰጡት አስተያየትም፤ “ጥቅምት 12 ቀን 2017 ዓ.ም. ከጠዋት ጀምሮ እስከ 11 ሰዓት በዘለቀው ውይይት የጸጽታ አካላት በአከባቢው አሁን ሰላም ወርዷል በሚል ማህበረሰቡ ትጥቅ እንዲያወርድ ብጠይቃቸውም እነሱ ደግሞ በተቃራኒው፤ በአካባቢው በግምት 20 ኪ.ሜ ርቀት ላይ መንግሥት ሸኔ ብሎ የሚጠራውና ራሱን ኦ.ነ.ሰ የሚለው ኃይል ከፍተኛ እንቅስቃሴ የሚያካሂድበት ቦታ መሆኑንና እስከ አኹንም በጥቂቱም ቢሆን በዚኹ መንገድ ራሳቸውን እየተከላከሉ እንደቆዩ ተናግረዋል” ነው ያሉት፡፡
ፓርቲው በጭንቀት ያሉት ያሏቸው የአንዶዴ ዲቾ ቀበሌ ነዋሪዎች የመከላከያ ሠራዊት አመራሮች ጉዳዩን ከነባራዊ ኹኔታ ጋር የተገናዘበ መፍትሔ እንዲሰጡት ማሳሰባቸውንም አመልክቷል።
ዶይቼ ቬለ አስተያየታቸውን የጠየቃቸው የምስራቅ ወለጋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዋጋሪ ነገራ አንድ ብሔር ተለይቶ ሳይሆን ትጥቅ የሚያወርደው ሁሉም ነው ብለው ስልካቸው በመዝጋቱ የተብራራ መረጃን ከሳቸው ማግኘት አልተቻለም፡፡
የአከባቢው ባለስልጣን ሂርኪሳ መኮንን እንዳሉትም፤ “የተባለው ሚሊሻ በህግና ስርዓት እንዲደራጅ፤ ህገወጥ መሳሪያም በህግ እንዲመዘገብ ነው የተባለው እንጂ ብሔር ተለይቶ አንተ ታጠቅ አንተ ፊታ የተባለበት አግባብ የለም፡፡ መንግስት ባስቀመጠው አቅጣጫ በአንድ ቀበሌ ምን ያህል ሚሊሻ ያስፈልጋል የሚባለው የሚታወቅ ብሆንም በዚያች ቀበሌ ግን ከልክ በላይ በህገወጥም የታጠቁ አሉ፡፡ እድሜው መሳሪያ ለመያዝ የደረሰም ያልደረሰም እንዲሁም አዛውንት ወጣቱ ሁሉ ታጥቆ መሄዱ ያስጠይቃል ነው ያልነው፡፡ በአንድ ቀበሌ 75 መሳሪያ በቂ በመሆኑ እስከዚህ ቁጥር ያለው ሰልጥኖ እንዲታጠቅ ነው የታሰበውም” ብለዋል፡፡
ኦሮሚያ እና አማራ ክልሎች በሚዋሰኑባቸው የምስራቅ ወለጋ እና ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ወረዳዎች ውስጥ ከዚህ በፊት ተደጋግሞ በተከሰተው ግጭት የአከባቢው ማህበረሰብ ለደህንነት ስጋት ለመጋለጡ የተለያዩ ታጣቂዎችን ስከሱ እንደነበርም ይታወሳል፡፡
ስዩም ጌቱ
ነጋሽ መሐመድ
ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር