በምዕራብ ሸዋ ዞን ጀልዱ ወረዳ 19 የመንግስት ታጣቂዎች መገደላቸውን
ቅዳሜ፣ ጥቅምት 9 2017በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን ጀልዱ ወረዳ ባለፈው ረቡዕ ለሓሙስ አጥቢያ ታጣቂዎች አደረሱ በተባለ ጥቃት ቢያንስ 19 ሰዎች መገደላቸውን የአይን እማኞች ለዶቼ ቬለ ገለጹ፡፡
እንደ አስተያየት ሰጪዎች ኪልቤ አቦ ቀበሌ በተባለ ገጠራማ ስፍራ አከባቢውን በመጠበቅ ላይ ነበሩ የተባሉ የአከባቢው አርሶ አደር ምሊሾች ላይ ታጣቂዎች ተኩስ ከፍተው ደም መፋሰስ ተከስቷል፡፡
አንድ የአከባቢው ባለስልጣን በዚህ ውጊያ በሁለቱም በኩል በተፈጠረው ግጭት የሰው ህይወት ማለፉን አረጋግጠዋል፡፡
በጀልዱ ወረዳ ምን ተከሰተ?
ጥቅምት 06 ቀን 2017 ዓ.ም. ሌሊት ለሃሙስ አጥቢያ ኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን ጀልዱ ወረዳ ውስጥ ታጣቂዎች አደረሱት በተባለ ጥቃት አንድ ፖሊስን ጨምሮ 19 ሰዎች ተገድለዋል፡፡ ለደህንነታቸው ሲባል ስማቸውን እና ድምጻቸውን እንዳንጠቀም አስጠንቅቀው አስተያየታቸውን የሰጡን አንድ ጉዳዩን በቅርበት የተመለከቱት አስተያየት ሰጪ ለዶይቼ ቬለ በሰጡት አስተያየት “ታጥቀው በጫካ የሚንቀሳቀሱ አካላት ከንጋት 11፡00 አከባቢ ኪልቤ አቦ በምትባል ቀበሌ የነበሩት የአከባቢው ሚሊሻዎች ላይ በከፈቱት ተኩስ አንድ ፖሊስ እና 18 የሚሊሻ አባላት ተገድለዋል” ብለዋል፡፡ አክለውም ሆዱ የቆሰለ አንድ ሰው በአከባቢው መታከም ባለመቻሉ ወደ ተሻለ ህክምና ተልከዋልም ነው ያሉት፡፡ ታጣቂዎቹ የተወሰኑ ያሉትን በቁጥር ያልገለጿቸው ሰዎችንም ይዘው መሰወራቸውን የአይን እማኙ አስረድተዋል፡፡ አሁን ላይ የመንግስት የፀጥታ ኃይሎች አከባቢው ላይ በስፋት በመስፈራቸው አከባቢው መረጋጋቱንም የገለጹት የአይን እማኙ፤ በተፈጠረው የግድያ ድርጊት የአከባቢው ማህበረሰብ ክፉኛ ማዘኑንና ለስነልቦናዊ ስብራት መዳረጉንም በአስተያየታቸው አመልክተዋል፡፡
ዶይቼ ቬለ ስለ ክስተቱ አስተያየታቸውን የጠየቃቸው የምዕራብ ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዲዳ ጉደታ በእለቱ የሆነውን ሲያስረዱ፤ “በተፈጠረው ውጊያ ምን ያህል ህይወት አለፈ በሚለው ጉዳይ እኔ የጦር አዋጊ ስላልሆንኩ ይህን ያህል ነው ለማለት እቸገራለሁ፡፡ ግን ለማረጋገጥ የምፈልገው በውጊያው ሚሊሾቻችን እና ውጊያውን በከፈተው ኦነግ ሸነ ላይ የህይወት መስዋእትነት ጨምሮ ጉዳቶች ደርሷል፡፡ ሚሊሾቹ ቀበሌያቸውን በመጠበቅ ላይ ሳሉ ነበር ጠላት ውጊያ የከፈተባቸው፡፡ በዚያም ላይ የተለያዩ ዋጋ ተከፍሏል” ብለዋል፡፡
በአከባቢው የነበረው የሰላም ተስፋ
በምዕራብ ሸዋ ዞን በተለይም ጀልዱ እና ግንደበረት ወረዳዎች በርካታ የኦነግ-ኦነሰ ታጣቂዎች ናቸው የተባሉ ትጥቅ አውርደው ለመንግስት እጅ በመስጠት ወደ ተሃድሶ ስልጠና መግባታቸው ሲነገር ነበረ፡፡ በቅርቡ የታጣቂ ቡድኑ ማዕከላዊ ኦሮሚያ አዛዥ ሰኚ ነጋሳ ከታጣቂ ቡድኑ ዋና አዛዥ ጋር ልዩነት መፍጠራቸውንና በታጣቂ ቡድኑ መካከል አለመግባባት መፈጠሩን ለመገናኛ ብዙሃን ከገለጹም ገና አንድ ወር እንኳ አልተቆጠረም፡፡
ያንኑን ተከትሎም የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ በክልሉሰላም ለማውረድ አለን ባሉት ቁርጠኝነት ከዚህ ኮማንድ ጋር ለውይይት ለመቀመጥ መታቀዱን የገለጹትም ባለፈው ሳምንት ነበር፡፡
የምዕራብ ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪው አቶ ዲዳ እንዳሉትም፤ “እውነት ነው ይህ ኃይል ለአገር ሽማግሌዎች እጅ ሲሰጥ ነበር፡፡ በዚህም እራሱን ገንጥሎ የወጣ አካል ስለነበር በዚያ ብስጭት ይመስላል እንዲህ ያለ የቂም መወጣጫ የሚመስል ጥቃት የፈጸመው፡፡ አሁንም ዛሬ አንኳ አከባቢው ላይ ሚሊሻ ተጠናክሮ እየተዋጋቸው ወደ ቆላ እየሸሹ ነው ያሉት” ብለዋል፡፡
ያለፉትን ጥቂት ዓመታት ክፉኛ መፈተናቸውን የሚገልጹት የአከባቢው ነዋሪዎች ግን አላባራ ባለው ግጭት መሰቃየታቸውን ይገልጻሉ፡፡ ስሜ ይቆይ ብለው አስተያየታቸውን የሰጡ ነዋሪ እንዳሉትም፤ “ይህ ግጭት በአከባቢው ለሶስት አራት ዓመታት ተራዝሞ በሁለቱም ተፋላሚ ቡድኖች በኩል በሚሰነዘር ጥቃት ሰላማዊ ዜጎች ዋጋ ሲከፍሉ የቆዩበት ነው፡፡ በአከባቢው ኢኮኖሚ እና እንደ ጤና ያሉ ማህበራዊ መገልገያዎች በእጅጉ ተዳክሟል፡፡ አልፎ አልፎ ደግሞ አሁን እንደተከሰተው በአስሮች የሚቆጠሩ ሰዎች በግጭቱ መዘዝ ሲረግፍ ይስተዋላል፡፡ በተገደሉ 18 ግድም አርሶ አደሮች በአከባቢው እጅግ የከፋ ሃዘን ሆኗል፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ቤተሰብ የሚያስተዳድሩ፣ ልጆች የሚያስተምሩ ናቸው፡፡ ብዙ መቋሰልም ስለሚፈጥር የሚሳዝን ነው ማለት ነው” ሲሉም ሀሳባቸውን አስረድተዋል፡፡
ሥዩም ጌቱ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር