1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ማሕደረ ዜና፣ የኢትዮጵያ መንግስትና የኦነሰ ድርድር ክሽፈት

ሰኞ፣ ኅዳር 17 2016

የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊትም ትጥቅ ለመፍታት፣ ሰራዊቱ የፌደራሉን ወይም የኦሮሚያ ፀጥታ አስከባሪዎችን እንዲቀላቀል ፈቃደኛ እንደነበር ታዛቢዎች ገልፅዋ።ሁለቱን ወገኖች አላግባባ ካሉት ነጥቦች ዋነኞቹ በኦሮሚያ ክልል አዲስ ምርጫ እስኪደረግ ድረስ ሁሉን የፖለቲካ ፓርቲዎች ያሳተፈ የሽግግር አስተዳደር እንዲመሰረት፣የክልሉ የፀጥታ፣የልማትና ሌሎች ተቋማት--

https://p.dw.com/p/4ZV6I
የኦነግ-ኦነሰ አርማ
የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት አርማምስል Seyoum Getu/DW

ማህደረ ዜና፣ የኢትዮጵያ መንግስትና የኦነሰ ድርድር ክሽፈት

ዳሬ ኤስ ሰላም ሔዱ፤ ሁለት ሳምንት አወሩ፤ ወደየመጡበት ተመለሱ።እና 5 ዓመት እንደኖሩበት መወቃቀስ፣ መገዳደል-ማገዳደሉን ቀጠሉበት።የኢትዮጵያ መንግስትና የኦነሰ ባለስልጣት ሰሞናዊ ወግ።ወግ ሆኖ በቀረ በርግጥ «እሰየዉ» ባሰኘ ነበር።የሺዎች ንፁሐንን ሕይወት-የሚቀጭ፣ መቶ ሺዎችን የሚያፈናቅል፣ የሚሊዮኖችን ኑሮ የሚያቃዉስ፣ የድሆችን ጥሪት የሚያወድም ግጭት- መሆኑ እንጂ ሰቀቀኑ።የድርድሩ ክሽፈት መነሻ፣ ምክንያቶቹ ማጣቃሻ፣ የወደፊቱ እንዴትነት መድረሻችን ነዉ-ላፍታ አብራችሁን ቆዩ።

 የኢትዮጵያ መንግስትና መንግስት ኦነግ-ሸኔ በሚል ስም በአሸባሪነት የፈረጀዉ የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት (ኦነሰ) አምና ሚያዚያ አሩሻ-ታንዛኒያ ዉስጥ «የመጀመሪያ ዙር» ያሉትን ድርድር ሲጀምሩ ከሁነኛ ስምምነት እንዲደርሱ በግጭቱ የሚጎዳዉ አካባቢ ሕዝብ፣ ማሕበራት፣የሐገር ሽማግሌዎች፣ የምክር ቤት እንደራሴዎች ግፊት ሲያደርጉ፣ ሲጠይቁ ሲማፀኑም ነበር።የሰማ እንጂ የተቀበላቸዉ አልነበረም።ድርድሩም ፈረሰ።

ከሚያዚያ እስከ ዘንድሮ ከሰላሌ እስከ ፈንታሌ፣ ከሆሮ ጉድሩ እስከ ጨዋቃ በተደረገዉ ግጭት፣ጥቃትና እገታ የሞተ፣የቆሰለ የተፈናቀለዉን ህዝብ ተራፊዉ ቆጠረ-አስቆጠረ ሮሮ፣ስቃይ ሰቆቃን አላዘነ።መፍትሔ ግን የለም።ማሕደረ ዜና፣ የኢትዮጵያና የኦነሰ ድርድር ተስፋና ቀቢፀ ተስፋ

የሰሜን ኢትዮጵያን ጦርነት ያስቆመዉ የሰላም ስምምነት በሚገባዉ ልክ ገቢር አልሆነም መባሉና የስምምነቱ ተፈራራሚዎች መወቃቀስ ኢትዮጵያዉያንን ዛሬም እንዳሰጋ ነዉ።የኢትዮጵያ መንግስት ጦርና አማራ ክልል የሸመቀዉ የፋኖ አማፂ ቡድን የገጠሙት ግጭት የሰላማዊ ሰዎችን ሕይወት፣ አካል፣ ሐብትና ንብረት እያጠፋ ነዉ።ድርቅ፣ የምግብ እጥረት፣ የዉሐ ሙላት፣ የኑሮ ዉድነት ሚሊዮኖችን አፈናቅሏል ወይም ለከፋ ችግር አጋልጧል።

                           ድርድሩ የፈነጠቀዉ ተስፋ

አብዛኛዉ ኢትዮጵያዊ ካንዱ ቀበሌ ወደ ሌላዉ በነፃነት መጓዝ አይችልም።በዚሕ መሐል ከሚያዚያ ጀምሮ የተዳፈነዉ የኢትዮጵያ መንግስትና የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት ድርድር መቀጠሉ ሲነገር ከተደራራቢዉ ችግር ቢያንስ አንዱን ለማቃለል ይረዳል የሚል ተስፋ አጭሮ ነበር።

ዉስጥ አዋቂ ምንጮች እንዳሉት የኢጋድ፤የዩናይትድ ስቴትስ፣ የኖርዌና የኬንያ ባለስልጣናትና ዲፕሎማቶች በሽምግልናዉ ተካፍለዋል።ድርድሩ አንደኛ ሳምንቱን እንዳስቆጠረ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት የኮሙኒኬሽን ቢሮ የበላይ ኃይሉ አዱኛ ለጋዜጠኞች የሰጡት መግለጫ ተስፋዉን አጠናክሮታል።

«የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የጀመረዉን ዘላቂ ሰላም የማስፈን ስራዉን አጠናክሮ ይቀጥላል።ለሰላም የተዘረጉ እጆች አልታጠፉም።ሊታጠፉም አይችሉም።»

ሁሉም ግን በነበረ ቀረ።ድርድሩ ያለዉጤት ማብቃቱን ሁለቱም ወገኖች ባለፈዉ ሳምንት በየፊናቸዉ አስታወቁ።እዚሕ ጀርመን ሙኒክ የሚኖሩት የኦሮሞ የፖለቲካ አቀንቃኝ አብዶ ቃዲ አባጀበል እንደሚሉት የሕዝብ የሰላም ተስፋም ቢያንስ ላሁኑ በነነ።በመንግስት እና የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት የሰላም ድርድር የተፈናቃዮች ተስፋ

«ከድርድሩ በፊት በሁለቱም ወገን ተስፋ ያለዉ ነገር ሲነገር ስለነበር----ሕዝቡም በርግጠኝነት የሆነ ዉጤት ይዘዉ ይመጣሉ ብሎ ይጠብቅ ስለነበር።ያ ሳይሆን በመቅረቱ ከባድ ሐዘኔታን አስከትሏል።»

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ሊቀመንበር የዉጪ ግንኙነት አማካሪ ዶክተር ሽጉጥ ገለታም ሁለተኛዉ ዙር ድርድር መክሸፉን የሰላም ተስፋን ያሳጣ  ይሉታል።

የኢትዮጵያ መንግስትና የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት (አነሰ) ባለስልጣናት ለድርድሩ መክሸፍ ያዉ እንደሚጠበቀዉ አንዳቸዉ ሌላቸዉን እየወቀሱ ነዉ።መንግስትን ከወከሉት ተደራዳሪዎች አንዱ የጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ አሕመድ የፀጥታ ጉዳይ አማካሪ ሬድዋን ሁሴን በX (የቀድሞ ትዊተር) ገፃቸዉ ለድርድሩ መክሸፍ «ሸኔ/OLF-OLA» ያሉትን ቡድን ተጠያቂ አድርገዋል።

አምባሳደር ሪድዋን «የሌላዉ ወገን አደናቃፊ አቀራረብና ተጨባጭ ያልሆኑ ጥያቄዎች ለዚሕ ድርድር አለመሳካት ዋነኞቹ ምክንያቶች ናቸዉ» ይላሉ።

የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት (ኦነሰ) ባወጣዉ መግለጫ ባንፃሩ ለድርድሩ መክሸፍ የኢትዮጵያ መንግስትን ይወነጅላል።ኦነሰ በX (ትዊተር) ባሰራጨዉ መግለጫ እንዳለዉ «የኢትዮጵያ መንግስት ሐገሪቱ ለገጠማት መሠረታዊ ችግሮች ምንጭ የሆነዉን የፀጥታና የፖለቲካ ችግሮችን ከመፍታት ይልቅ፣ የኦነሰ አመራርን ከሌሎቹ ነጥሎ ሥልጣን ወይም ጥቅማ ጥቅም ለመስጠት በመፈለጉ ነዉ» ይላል መግለጫዉ።

ከኢትዮጵያ መንግስት  ጋር ተደራድረዉም፣ ተነጋግረዉም፣ ተኳርፈዉም በመንግስት ታስረዉም የመንግስትን ባለስልጣናትን የሚያዉቁት ዶክተር ሽጉጥ ገለታ የሕዝቡ ፍላጎት፤ ምኞትና ተስፋ ከፍተኛ የነበረ ቢሆንም መንግስት እዉነተኛ ሰላምና ዲሞክራሲ የማስፈን ፍላጎት እንደሌለዉ  እንጠረጥር ነበር ይላሉ።ምክንያታቸዉ የጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ አሕመድን ፓርቲ (ብልፅግናን) ባህሪን ይጠቅሳሉ።

«በኦሮሞ ነፃነት ግንባር ላይ የደረሰዉ ክሕደት፣ ሌሎችንም ተቃዋሚ ወይም የዛሬዎቹ ተፎካካሪ ፓርቲዎችን እንዴት Co-opt እንዳደረገ የብልፅግና ፓርቲ----የራስን ስልጣን ለመቆጣጠር ብቻ ለሰዎች ሥልጣን ሰጥቶ በዚያዉ ማዕቀፍ ዉስጥ እንዳይንቀሳቀሱ የማድረግ ባሕሪ ያለዉ ፓርቲ ስለሆነ፣እና ክሕደትም ስለደረሰብን----»

የኢትዮጵያ መንግስት የኮሙኒኬሽን አገልግሎት መራር መግለጫ   

የኢትዮጵያ መንግስት የኮሙኒኬሽን አገልግሎት ያወጣዉ መግለጫ  ከአምባሳደር ሪድዋን ሁሴን መልልዕክት፣ ከኦነሰ መግለጫም ሆነ ድርድሩን ከሩቅ ከታዘቡት ፖለቲከኞች አስተያየትም ጠንከር፣ መረር-ከረር ያለ ነዉ።መግለጫዉ የሰላም ድርድሩን «ዉይይት» ይለዋል።ኦነሰን ደግሞ አንዴ ሸኔ፣ ሌላ ጊዜ «የሽብር ቡድን» እያለ ይገልፀዉና ሶስተኛዉ አንቀፅ ላይ፣-

«በዚሕ ዉይይት ወቅት የሽብር ቡድኑ ከ60 ዓመታት በፊት የኦሮሞም የሌሎች የኢትዮጵያ ብሔረሰቦችም ሁሉ ጥያቄዎች የነበሩና ተመልሰዉ ያደሩ ጥያቄዎችን አንስቷል።----በሥራ ላይ የዋሉ ጉዳዮችን ከማነብነብ ዉጪ የሚቆጠርና የሚቋጠር አጀንዳ ምምጣት ስላልቻለ---» እያለ አትቶ «በሽብር ቡድኑ ዘንድ በዚሕኛዉ ዙርም መንግስት አዝሎ መንግስት ያድረግኝ ከሚል አጉራ ዘለልነት ባለፈ ----እያለ የመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት ለሁለት ሳምንት ሲደራደሩት የነበረዉን ቡድን አጣጥሎ ይነቅፋል።

በኦሮሚያ ክልል በሚካሄደዉ ግጭት ከተፈናቀሉት ጥቂቱ
በኢትዮጵያ መንግስትና በኦነሰ መካከል በሚደረገዉ ዉጊያ ከተፈናቀሉት ጥቂቱምስል Seyoum Getu/DW

የሁለቱ ወገኖች ተደራዳሪዎች የተነጋገሩባቸዉን ነጥቦች፣ከተነጋሩባቸዉ ነጥቦች ዉስጥ  የተስማሙና የተፋረሱባቸዉን ጉዳዮች እስካሁን በግልፅ አላስታወቁም። ሁለቱም በየፊናቸዉ እንወክልሐለን ወይም ቆመንልሐል ለሚሉት ግን ለሚፈጁና ለሚያስፈጁት ሕዝብ የተስማሙና የተፋረሱበትን ጉዳይ በግልፅ ከማሳወቅ ይልቅ ለሌላ ዉጊያ አንዳቸዉ ሌላቸዉን መወነጀላቸዉ የግጭቱ መዘዝ ለሚያሰቃየዉ ሕዝብ ተጨማሪ ስጋት፣ ለሩቁ ነዋሪ አሳዛኝ፣ ለታዛቢ ደግሞ አቶ አብዶ ቃዲ አባጀበል እንደሚሉት  ግራ አጋቢ ነዉ።

«የድርድሩ ይዘትም ግልፅ ስላልሆነ ብዙ ሰዎች የሚሰሙት ሁለቱም ሲወቃቀሱ ነዉ---ግልፅ ስላልሆነ በምን ፌይል እንዳደረገ በጣም ትልቅ ዲስአፖይትመንት ነዉ ያለዉ።»

የተፋረሱባቸዉ ነጥቦች-ታዛቢዎች

በአደራዳሪነት ወይም በሽምግልናዉ የተሳተፉት ዲፕሎማትና ፖለቲከኞች እስካሁን በይፋ ያሉት ነገር የለም።ሥለድርድሩ ሒደትና ክሽፈት እናዉቃለን ባዮች እንደሚሉት ግን የኢትዮጵያ መንግስት ተደራዳሪዎች ለኦነሰ መሪዎች ሥልጣን ለመስጠት፣ ቡድኑ እስካሁን ላደረሰዉ ጥፋት በወንጀል ላለመጠየቅ፣ እስረኞችን ለመልቀቅና ቡድኑ የሚቆጣጠራቸዉን አካባቢዎች እንዲያስተዳድር ፈቅዶሞ ነበር።ያልሰመረው የመንግስት እና የኦነግ-ኦነሰ ድርድር

የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊትም ትጥቅ ለመፍታት፣ ሰራዊቱ የፌደራሉን ወይም የኦሮሚያ ፀጥታ አስከባሪዎችን እንዲቀላቀል ፈቃደኛ እንደነበር ታዛቢዎች ገልፅዋ።ሁለቱን ወገኖች አላግባባ ካሉት ነጥቦች ዋነኞቹ በኦሮሚያ ክልል አዲስ ምርጫ እስኪደረግ ድረስ ሁሉን የፖለቲካ ፓርቲዎች ያሳተፈ የሽግግር አስተዳደር እንዲመሰረት፣ የክልሉ የፀጥታ፣ የልማትና ሌሎች ተቋማት በአዲስ መልክ እንዲደራጁ ኦነሰ ያቀረባቸዉ ጥያቄዎች በመንግስት በኩል ተቀባይነት አላገኘም።

የኦነግ እጅ አለበት ይሆን?

ስማቸዉ እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ታዛቢዎች እንደሚሉት አምባሳደር ሪድዋን «ተጨባጭ ያልሆነ ጥያቄ » ያሉት ወይም ካሉት አንዱ፣ ኦነሰ በኦሮሚያ ክልል ሁሉን አቀፍ የሽግግር መንግስት ይመስረት የሚለዉ ጥያቄ ሳይሆን አይቀርም።

ጥያቄዉ ከዚሕ ቀደም በፌደራል ደረጃ የተለያዩ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ፣በኦሮሚያ ደረጃ ደግሞ ኦነግን ጨምሮ በርካታ የኦሮሞ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ያነሱት ጥያቄ ነዉ።አዲስ አይደለም።በዚሕም ምክንያት የኦነሰ አቋም ከፍተኛ የሆነ የኦነግ ተፅዕኖ የሚንፀባረቅበት ነዉ የሚሉ አስተያየት ሰጪዎች አሉ።የኦነግ ሊቀመንበር የዉጪ ግንኙነት አማካሪ ሽጉጥ ገለታ ግን ኦነግ ኦነስ ላይ ተፅዕኖ ያሳድራል የሚለዉን አስተያየት «በፍፁም» ባይ ናቸዉ።

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ደጋፊዎች ሰልፍ
የኦነግ ደጋፊዎች ሰልፍ ምስል Michael Tewelde/AFP

«በፍፁም፣ በፍፁም።የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት የራሱን አመራር (ይዞ) በራሱ የመደራደሪያ ነጥቦች ነዉ የቀረበዉ።በምንም አይነት ተዓምር የኦሮሞ ነፃነት ግንባር በሱ ላይ ተፅዕኖ የለዉም።»

ሁለቱ ወገኖች ከድርድሩ መፍረስ በኋላ በየፊናቸዉ ካወጡት መግለጫ ምናልባት ተስፋ ላለማጣት የሰጡት ተስፋ ልዩነታቸዉን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት መፈለጋቸዉን በየፊናቸዉ ማስታወቃቸዉ ነዉ።

ግጭቱ ግን ድርድሩ በሚደረግበት መሐል እንኳ  አልቆመም።የድርድሩ መፍረስ በይፋ ከተነገረ ወዲሕ ደግሞ እንደ ፕሮፓጋንዳዉ ሁሉ ዉጊያዉም ተጠናክሯል።የተለያዩ አካባቢዎች ነዋሪዎች እንደሚሉት ካለፈዉ አርብ ወዲሕ ሆሮ ጉዱሩ፣ ቡኖ በደሌ በተለይ ጨዋቃ ወረዳ፣ ሰላሌ፣ ሰገን ሶዶ፣ ፈንታሌ ወረዳዎችና ቀበሌዎች ዉስጥ ግጭቱ ተባብሶ ቀጥሏል። እስከ መቼ?

ዶክተር ሽጉጥ እንደሚሉት መላዋ ኢትዮጵያም ሆነች ኦሮሚያ ከግጭት፣ ጦርነት፣ መከራዉ እንዲላቀቁ መፍትሔዉ ከዚሕ ቀደም ኦነግ ያቀረበዉና ቀላል ነዉ።ሲሆን ሐገር አቀፍ ይህ ቢቀር ኦሮሚያ አቀፍ ግን ሁሉን አሳታፊ የሽግግር መንግስት መመስረት።ይሆን ይሆን? ቸር ያሰማን።

ነጋሽ መሐመድ

አዜብ ታደሰ