ማሕደረ ዜና፣ የኢትዮጵያና የኦነሰ ድርድር ተስፋና ቀቢፀ ተስፋ
ሰኞ፣ ኅዳር 3 2016
የኢትዮጵያ መንግስት ከፈትኩት የሚለዉ የሰላም በር ባለስልጣናቱ እንደሚሉት አሁንም አልተዘጋም።መንግስትን የሚወጋዉ የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት(ኦነሠ)ም አምስት ዓመት ያለፈዉን ግጭት በድርድር ለመፍታት ዝግጁነኝ ባይ ነዉ።በሁለቱ ወገኖች ዉጊያ ዘመድ-ወዳጁ የተገደለበት፣የተፈናቀለና ኑሮዉ የተቃወሰበት ህዝብም ተፋላሚዎች ጠባቸዉን በድርድር እንዲፈቱ እየገፋፋ፣ እየጠየቀ፣እየፀለየም ነዉ።የተፋላሚ ኃይላት ተወካዮች አምና ሚያዚያ ያደረጉት የመጀመሪያ ዙር ድርድር ግን የተፋላሚዎቹን ቃል፣ የሕዝቡን ጥያቄና ግፊትም መና ያስቀረ መስሏል።የመንግስትና የኦነሠ ተወካዮች ባለፈዉ ሳምንት ዳሬ ኤሰ ሠላም-ታኒዚያ ዉስጥ ሁለተኛ ዙር ድርድር ጀምረዋል።አምና ሚያዚያ የመከነዉ ተስፋ ያቀጠቅጥ ይሆን? ላፍታ አብረን እንጠይቅ።
ፀሐፍት በግጥም-ድርሰቶቻቸዉ ምሁራን በጥናታቸዉ፣ ከዓሊ ቢራ እስከ አብተዉ ከበደ የነበሩ ድምፃዉያን በማራኪ ዜማዎቸዉ ሐብት፣ዉበት፣ለምነቷን፣ ያደነቁ፣ የደጎች መኖሪያ፣ የአዋቂዎች መብቀያነቷን ያወደሱ-የመሰከሩላት ፀሐይ መጥለቂያቱ ምድር ባለፉት አምስት ዓመታት በርግጥ የዘር-ዛር የሚያስደልቃቸዉ እኩያን መፈንጫ ሆናለች።ወለጋ። ንፁሐን ክፉ ደጉን ያለዩ ሕፃናት፣ ሴቶች፣ ተጧሪዎች በግፍና በገፍ የሚገደሉ፣የሚዘረፉ፣ የሚፈናቀሉባት ምድር።
ከአምስት ዓመት በፊት እንደዘበት ወለጋ ላይ የተጀመረዉ የመንግስትና የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት (ኦነሰ) ግጭት፣ወደለየለት ዉጊያ ብቀላ፣ ግድያ፣ ማፈናቃል፣ እገታ አሁን ከጉጂ እስከ ሰሜን ሸዋ፣ ከምዕራብ ሸዋ እስከ አርሲ ደርሶ ሺዎች አልቀዋል፤ መቶ ሺዎች ቆስለዋል፤ ተፈናቅለዋል፤ከአምራችነት ወደ ለማኝነት ወርደዋልም።ለምን? ብዙዎች ብዙ ምክንያት ይደረድራሉ።የምስራቅ አፍሪቃ ተነሳሽነት ለለዉጥ-ኢስት አፍሪካን ኢንሼቲቭ ፎር ቼንጅ የተባለዉ ግብረ-ሠናይ ድርጅት የፕሮግራም የበላይ ሐላፊ ገረሱ ቱፋ የሆነዉ መሆን አልነበረበትም ይላሉ።
ግን ሆነ።ከፍተኛ ቀዉስና ችግርም ደረሰ።ለችግሩ መሰረታዊ ምክንያት ተፋላሚዎች ያዉ እንደ ጠላት ወግ አንዳቸዉ ሌላቸዉን ይወቅሳሉ።ሌሎች ብዙ ተንታኖች ብፋ ብዙ ምክንያት ይደረድራሉ።በሙኒክ ከተማ አስተዳደር የማሕበራዊ ጉዳይ ሠራተኛና የፖለቲካ አቀንቃኝ አብዶ ቃዲ አባ ጀበል እንደሚሉት ግን መሠረቱ የመንግስት «ቃል አባይነት» ነዉ።
«ይሕ ችግር ወደ ጦርነት እንዲያመራና የኦሮሞ ወጣቶችም በብዛት የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊትን እንዲቀላቀሉ ምክንያት የሆነዉ መንግስት ቃሉን በማጠፉ ነዉ።ለምሳሌ የኦሮሞ ወጣቶች ለዉጡን ያመጡ ቄሮዎች ሲገደሉ ነበር፤ በግፍ ሲታሰሩ ነበር።ታዋቂ የኦሮሞ ፖለቲከኞችን ማስፈራራት፣ የፖለቲካ ድርጅቶችን ቢሮዎችን መዝጋት በጣም የሚያሳዝኑ ከለዉጡ በኋላ ይመጣሉ ያልተባሉ ጉዳዮች ለዚሕ ግጭት ዋናዉ መንስኤ ናቸዉ ብዬ ነዉ የማምነዉ።»
የችግሩን መሠረታዊ ምክንያት ለማረም የተወሰደ ርምጃ ሙከራም የለም።እንዲያዉም የኢትዮጵያ ፌደራዊ መንግስትና ሕዝባዊ ወያኔ ሐርነት ትግራይ (ህወሐት) በዋናነት የገጠሙት ሽኩቻ ሲንር ሁለቱም ወገኖች የጦር ተሻራኪ ፍለጋ ይባትሉ ገቡ።
ሽኩቻዉ ንሮ የሰሜኑ ጦርነት ሲግም መንግስት ኦነግ ሸኔ በሚል ስያሜ በአሸባሪነት የፈረጀዉ (ኦነሠ) ከሕወሐት ጋር የጦር ተሻራኪ ትብብር መሠረተ።አምና ጥቅምት የኢትዮጵያ መንግስት በጦርነቱ ከጎኑ ሆነዉ የተዋጉትን ኤርትራን፣ የአማራና የአፋር ኃይላትን፣ ህወሓት ባንጻሩ የጦር ተሻራኪዉን የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊትን ጥለዉ መስማማታቸዉ የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚሉት በአማራ ክልል የዲስ ዉጊያ ሠበብ ፣ለኦሮሚያዉ ግጭት መባባስ ምክንያት ሲሆን እንዲባባስ ምክንያት ሲሆን፣ አስመሮችን አስኮርፏል።
የፕሪቶሪያዉ የሰላም ስምምነት በመላዉ ኢትዮጵያ ሰላም የማስፈን ዕድሉም መክኗል።ይሁንና የመንግስና የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ተወካዮች ባለፈዉ ዓመት ሚያዚያ አሩሻ ታንዛኒያ ዉስጥ መደራደራቸዉ የመከነዉን ዕድል ለማካካስ ተስፋ ተጥሎበት ነበር።ድርድሩ ለአግባቢ ስምምነት ባለምብቃቱ ከወለጋ እስከ ጉጂ ያለዉ ሕዝብ የተጨማሪ ወገኖችን ሕይወትና አካልና ሐብት ለመገበር ተገዷል።ሌላዉ ተፈናቅሏል።
ባለፈዉ ሳምንት የተፋላሚ ኃይላት ተወካዮች ዳሬ ኤስ ሰላም-ታንዛኒያ ዉስጥ ሁለተኛ ዙር ድርድር ጀምረዋል።የኦሮሚያ ክልል የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ ኃይሉ አዱኛ ባለፈዉ አርብ እንዳሉት መስተዳድራቸዉ ለሰላም የዘረጋዉን እጅ አላጠፈም።
ሌላ ተስፋ።የኦሮሞ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች ግን የመንግስትን ቃል አያምኑትም።ስማቸዉ እንዳይጠቀስ የፈለጉ አንድ ተቃዋሚ ፖለቲከኛ እንደነገሩን መንግስት ድርድሩን ከልብ ከፈቀደዉ ለድርድሩ ስኬት ቁርጠኝነቱን የሚያሳዩ እርምጃዎች መዉሰድ ነበረበት።
ፖለቲከኛዉ እንደሚያምኑት መንግስት የፖለቲካ እስረኞችን መፍታት፣ ግጭት በሚደረግባቸዉ አካባቢዎች ላለዉ ህዝብ ሰብአዊ እርዳታ እንዲደርስ መፍቀድ፣ መንገዶችን መክፈት የመሳሰሉ ምልክቶችን (ጀስቸርስ) ማሳየት፣ ሁለቱም ተፋላሚዎች ደግሞ ቢያንስ ድርድር በሚያደርጉበት ጊዜ ተኩስ ማቆም ነበረባቸዉ።
የሁለቱን ወገኖች ተደራዳሪዎች የሚመሩት ተፋላሚዎችን በቀጥታ በሚያዙ የጦር መሪዎች ናቸዉ።በአደራዳሪነት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የኢጋድ፣ የዩናይትድ ስቴትስና የኖሪዌ ዲፕሎማቶች መሳተፋቸዉ እየተዘገበ ነዉ።
ዉስጥ አዋቂ ምንጮች እንደሚሉት የኢትዮጵያ መንግስትንና ሕወሓትን አስማምተዋል የሚባሉት በአፍሪቃ ቀንድ የዩናይትድ ስቴትስ ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሐመር ዳሬ ኤስ ሰላም ድረስ ወርደዉ የድርድሩን ሒደት እያቀለጣጠፉት ነዉ።በዚሕም ምክንያት አቶ ገረሱ ቱፋ እንደሚያምኑት ሁለቱም ወገኖች ከሁነኛ ስምምነት ላይ ለመድረስ ሳይቆርጡ አልቀሩም።
«ያሁኑ ሚያዚያ ከነበረዉ የተሻለ ነዉ ብዬ ነዉ የማስበዉ።አንደኛ ጦሩን የሚያዙ አመራሮች ናቸዉ በሁለቱም በኩል የሚሳተፉት።ረጅም ጊዜ ነዉ የቆዩት።ብዙ ጊዜ ድርድሮች ባጭር ጊዜ ነዉ ችግር የሚገጥማቸዉ።መቆየታቸዉ ነገሩ እንዲሳከ ከመፈለግም ሊሆን ይችላል ብዬ ነዉ የማስበዉ።»
አቶ አብዶ ቃዲ አባ ጀበልም በተመሳሳይ ምክንያት ተመሳሳይ ተስፋ አላቸዉ።አቶ አብዶ እንደሚሉት ያሁኑን ድርድር ሁለቱም ወገኖች ከልብ የተዘጋጁበት መሆኑን የሚያመለክቱ ፍንጮች አሉ።
«በዚሕ ዙር ሲርየስ የሆነ ድርድር መደረግ እንዳለበትና ፍላጎቱም በሁለቱም ወገኖች እንዳለ የሚጠቁሙ መረጃዎች አሉ።የጦር አዛዦቹ እዚያ ባሉበት ሁኔታ አንዳድ ዉሳኔዎችን ለመወሰን ይጠቅማል።የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት የፖለቲካ ክፍሉም አብሮ እንደተጋዘ ነዉ እኔ ባለኝ መረጃ መሰረት።-----»
ሁለቱ ወገኖች ስምምነት ላይ ደርሰዉ አምስት ዓመት ያስቆጠረዉን ሁከት፣ ግጭትና እልቂት እንዲያስቆሙ ግጭቱ በሚደረግባቸዉ አካባቢዎች ያሉ ነዋሪዎች በየአጋጣሚዉ እየጠየቁ ነዉ።ከዚሕ ቀደምም ከሕዝብና ከተለያዩ ማሕበራት ተመሳሳይ ጥያቄዎች ቀርበዉ ነበር።የሰማ እንጂ ሁነኛ መልስ የሰጠ ወገን ግን የለም።አቶ ገረሱ እንደሚሉት አብዛኛዉ ህዝብ የሚፈልገዉ ተደራዳሪዎች የሚፋረሱበትን ምክንያት ሳይሆን ምንም ብለዉ ምን መስማማታቸዉን ነዉ።
«ሕዝብ ደግሞ ምን ላይ መስማማት እንዳለባቸዉ ብዙ የሚያሳስበዉ አይመስለኝም።ብዙ ሰዉ ይሕን ነገር መገላገል ነዉ የፈለገዉ።ምንም ዓይነት ነገር ላይ ይስማሙ ግጭቱ መቆሙን ብቻ ነዉ (ህዝብ) የሚፈልገዉ።የህዝቡን ሁኔታ ማዳመጥ አለባቸዉ----»
የኢትዮጵያ መንግስት በአሸባሪነት የፈረጀዉ የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ሙሉ በሙሉ ትጥቅ መፍታት አለበት ከሚል አቋሙ እስካሁን በይፋ አልተለሳለሰም።የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ባንጻሩ ጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ አሕመድ የሚመሩት መንግስት ከስልጣን ወርዶ የሽግግር መንግስት መመስረት አለበት የሚል አቋሙን ስለመቀየሩ በግልፅ የታወቀ ነገር የለም።
አምስት ዓመት ባስቆጠረዉ ግጭትና ዉጊያ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ለደረሰዉ ግፍና የሰብአዊ መብት ጥሰት አንዳቸዉ ሌላቸዉን መዉቀሳቸዉን አሁንም እንደቀጠሉ ነዉ።
በተለያዩ የኦሮሚያና ኦሮሚያን ከአማራ ክልል ጋር በሚያዋስኑ አካባቢዎች የሚደረገዉ ግጭት፣ ጥቃትና ግድያም ድርድሩ በሚደረግበት መሐል እንኳን አልቆመም።በዚሕም መሐል ከወደ ዳሬ ኤስ ሰላም የሕዝቡን ፍላጎትና ተስፋ የሚያለመልም ስምምነትይሰማ ይሆን? አቶ አብዶ ቃዲ አባ ጀበል እንደሚሉት ከመስማማት በመለስ ሌላ ምርጫ ያለ አይመስልም።
«መንግስትም የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ካለዉ ጦሩን (ትጥቁን) ይፍታ የሚል ጥያቄ ሳይሆን ይኽ የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ግጭት ባለበት አካባቢ ሰላም የማምጣት ሂደት ላይ እንዲሳተፍ ማግባባት፣ የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ደግሞ መንግስት ፈርሶ የሽግግር መንግስት ይቋቋም ብሎ ጠይቋል።እንግዲሕ ጉዳዩ ሰጥቶ መቀበል ከሆነ----»
የዘመኑ የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች የመንግስት ይባሉ ተቃዋሚ ወይም አማፂ ሕዝብ የሚያስጨርሱበትን ግጭታቸዉን ለመፍታት በቅርቡ ከፕሪቶሪያ እስከ ናይሮቢ መጓዝ፣ አሁን ደግሞ ከአሩሻ እስከ ዳሬ ኤስ ሰላም መኳተኑን እንደ ጥሩ ፌንጥ ይዘዉታል።ያሁኑ ድርድር ሰመረም ሳተ ኢትዮጵያ የህዝቧን ጥያቄ ሙሉ በሙሉ ሳትመልስ፣ የአዲስ አበባ መቀሌዎችን መጠራጠር በቅጡ ሳታረግብ፣ የአማራ ግጭትን ሳታስወገድ ሙሉ ሰላም ታገኛለች ብሎ ማሰብም ሆነ በየግጭቱ አሸናፊ ኃይል ይወጣል ብሎ መጠበቅ በርግጥ ብዙዎች እንደሚያምኑት የዋሕነት ነዉ።
ነጋሽ መሐመድ
ታምራት ዲንሳ