የፍራንኮ ቫሉታ መፈቀድ ጥቅሙና የጎንዮሽ ጉዳቱ
ማክሰኞ፣ ነሐሴ 14 2016መንግሥት በሕግ ክልከላ ከተደረገባቸው ዕቃዎች ውጪ ሌሎች ዕቃዎች በፍራንኮ ቫሉታ ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ መፍቀዱን አስታውቋል። ነሐሴ 13 ቀን 2016 ዓ.ም በገንዘብ ሚኒስትር ድዔታ ኢዮብ ተካልኝ ተፈርሞ ለጉምሩክ ኮሚሽን የተሰራጨው ደብዳቤ ክልከላ ከተደረግባቸው ዕቃዎች፣ ከነዳጅ አውቶሞቢሎች እና ከፀጥታ እና ደህንነት ዕቃዎች ውጪ ሌሎች ዕቃዎች ያለ ውጭ ምንዛሪ ክፍያ (ፍራንኮ ቫሉታ) እንዲገቡ መፈቀዱን ይጠቅሳል።
በጉዳዩ ላይ ያነጋገርናቸው አንድ የኢኮኖሚ ባለሙያ ፍራንኮ ቫሉታ "ቋሚ የፖሊሲ መሣሪያ" እንዳለሆነ ገልፀው እርምጃው በየጊዜው ክለሳ ሊደረግለት የሚገባ ነው ብለዋል።
ውሳኔው የፍጆታ ዕቃዎችን ለማስገባት ያለውን የውጭ ምንዛሪ እጥረት በማቃለል የዋጋ ግሽበት ለመከላከል የሚረዳ ቢሆንም ሕገ ወጥ ንግድ እንዲሁም ጥቁር ገበያን ሊያባብስ ስለሚችል ጥንቃቄ እንደሚያሻው ባለሙያው ገልፀዋል።
መንግሥት መሰል ውሳኔዎችን የሚያሳልፈው ለምንድን ነው?
መንግስት የሀገርን ኤኮኖሚያዊና ማህበራዊ ዕድገት ለማፋጠን፣ ገበያ እንዲዳብር፣ የወጪ ምርቶችና አገልግሎቶች በዓይነት፣ በመጠንና በጥራት እንዲጨምሩ ለማድረግ፣ የውጭ ምንዛሪ ግኝት እንዲያድግ ብሎም ለሀገር ውስጥ ፍጆታ ከውጭ ምርቶችን ለማስገባት የሚወጣውን የውጭ ምንዛሪ ለማዳን ለግል ዘርፉ ከሚዘረጋቸው አሠራሮች እና ከሚወስዳቸው እርምጃዎች አንዱ ፍራንኮ ቫሉታ ነዉ።
የምጣኔ ኃብት ማሻሻያ በዋና ዋና የንግድ ማሳለጫ መስኮች ምን አስከተለ?
መንግሥት የዉጭ ምንዛሪ ለባንክ ሳይከፈል ከራስ ኪስ በሚወጣ አሠራር (ፍራንኮ ቫሉታ) መሠረታዊ የምግብ ፍጆታዎች ከውጭ እንዲገቡ ከሦስት ዓመታት በፊትም ወስኖ ነበር።
ይህ ውሳኔ በገቢ ንግድ ላይ የሚወሰድ እና ጫናን ለመቀነስ ሲባል የደረግ ነው የሚሉት የምጣኔ ሐብት ባለሙያው አቶ ሁሴን ዓሊ፣ የውጭ ምንዛሪ በገበያ እንዲመራ ሲደረግ ይህን መሳዩ አሠራር መዘርጋቱ የሚጠበቅ ነው ብለዋል።
ይህ እርምጃ የፍጆታ ዕቃዎች ገቢ ላይ ያለውን የውጭ ምንዛሪ እጥረት በማቃለል በሌላ በኩል በውድ ገንዘብ ተገዝተው የሚገቡ ምርቶች በገበያ ላይ ሊያስከትሉ የሚችሉትን የዋጋ ግሽበት መከላከል አንዱ ዓላማው መሆኑን ይገልፃሉ። "አንደኛ የዋጋ ንረትን ኢላማ በማድረግ ያግዛል። ሁለተኛ የውጭ ምንዛሪ ገበያ ላይ ያለውን ጫና መሠረታዊ የፍጆታ ዕቃዎች እንዳይስተጓጎሉ ለማድረግ ያግዛል።"
የፍራንኮ ቫሉታ መፈቀድ የጎንዮሽ ጉዳት
መንግሥት በፍራንኮ ቫሉታ ዕቃዎችን ማስገባት "የሕዝብን ተጠቃሚነት ያረጋግጣል፣ መሠረታዊ ፍላጎት መሙያ የሆኑ ሽቀጦች እንዲገቡ ለማድረግ ያስችላል፣ ባለ ሀብቶች መዋዕለ ነዋያቸዉን ለኢንቨሰትመንት እንዲያዉሉ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል" የሚል እምነት አለው።
የምጣኔ ሃብት ማሻሻያው በአማራ ክልል ግብይት ላይ ምን አስከተለ?
ባለሙያው እንደሚሉት እርምጃው የሚሰጠውን ጥቅም ያኽል፣ ምርቶች በገፍ በሕገ ወጥ የንግድ መረብ ከውጭ ወደ ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ ብለዋል። በሌላ በኩል ወርቅ፣ ቡና የቁም እንስሳትን ጨምሮ ራሱ ዶላር እና ሌሎች ለውጭ ገበያ የሚውሉ የሀገር ውስጥ ምርቶች የሕገ ወጥ ንግድ ቀጣና ወደሆኑ ጎሩቤት ሀገራት በከፍተኛ ሁኔታ በኮንትሮባንድ ሊወጡ ይችላሉም ሲሉ ገልፀዋል። አክለውም የጥቁር ገበያውን ሊያባብስ እና የማይጨበጥ ሊያደርገው እንደሚችል አብራርተዋል።
"ከተለያየ ምንጩ በማይታወቅ ዶላር ኮንትሮባንድም ጭምር ዶላር ከሀገር ወጥቶ ተመልሶ ወደ ሀገር ውስጥ ማስግቢያ ሆኖ ይመጣል። ይሄ የዋጋ ግሽበትን ያባብሳል።"
በዚህ በፍራንኮ ቫሉታ የቅንጦት ዕቃዎች ብርቱ ክልከላ ካልተደረገባቸው አስመጪዎች በአትራፊ ምርቶች ላይ ብቻ በማተኮር ደሃውን ማህበረሰብ የሚጠቅሙ ተገቢ ምርቶች ከማስገባት ይልቅ ለኢኮኖሚውም ሆነ ለሸማቹ የረባ ዋጋ የሌላቸውን ምርቶች በማስገባት ዓላማውን እንዳያስቱት ሥጋት አለ።
የገበያ ዋጋ ለማረጋጋት መንግስት ምን እያደረገ ይሆን ?
ሀሳባቸውን በአደባባይ የሚገልፁት የፋይነንስ ባለሙያው አቶ ሙሼ ሰሙ "ፍራንኮ ቫሉታ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እጥረትና ከፍተኛ ግሽበት የሚያጋጥማቸው ሀገራት ለአጭር ጊዜ እንደማስተንፈሻ የሚገለገሉበት የአስመጭነት ፈቃድ" መሆኑን በመጥቀስ ይሄው ሥርዓት "ባልተረጋጋ ኢኮኖሚ ውስጥ ሕገ ወጥ የውጭ ምንዛሪ ፍላጎትን በማሳደግ አቻ ተመኑ እንዲጨምር በማድረግ የአቅርቦትን ዋጋ የማናር አሉታዊ ተጽእኖው አለው" ሲሉ ጽፈዋል።
በተቃራኒው በምንዛሪ መናር የሚፈጠረው የዋጋ ንረት እንደተጠበቀ ሆኖ በአጭር ጊዜ በአቅርቦትና በፍላጎት መካከል ያለውን ክፍተት በማጥበብ በአቅርቦት እጥረት ምክንያት የሚፈጠርን የዋጋ ንረት ሊያለዝብ ይችላል የሚል ሀሳብ ሰንዝረዋል።
ሰለሞን ሙጬ
እሸቴ በቀለ
ዮሐንስ ገብረእግዚዓብሔር