1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የፈንታሌ እና ምንጃር ሸንኮራ አዋሳኝ ግጭት

ማክሰኞ፣ መስከረም 8 2016

በምሥራቅ ሸዋ ዞን ፈንታሌ ወረዳና ሰሜን ሸዋ ዞን ምንጃር ሸንኮራ ወረዳ አዋሳኝ ላይ ከፍተኛ ግጭት መካሄዱን ነዋሪዎች ተናገሩ። በከባድ መሳሪያ ተካሂዷል በተባለው በዚህ ግጭት የወሰን ውዝግብ ትልቁ የግጭቱ መንስኤ ነበር ተብሏል፡፡ በግጭቱም የሰዎች ህይወት ማለፉና ቆርኬ (አውራ ጎዳና) ከሚባል ስፍራ ከ2 ሺህ በላይ ነዋሪዎች መፈናቀላቸው ተነግሯል።

https://p.dw.com/p/4WZ8C
የአማራ ክልል ገበሬ
የአማራ ክልል ገበሬ በጦርነት ተፈናቅሏልምስል AP/picture alliance

ሰሜን ሸዋ ዞን ምንጃር ሸንኮራ ወረዳ አዋሳኝ ላይ ከፍተኛ ግጭት መካሄዱን የአከባቢው ነዋሪዎች ተናገሩ

በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሸዋ ዞን ፈንታሌ ወረዳ እና አማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ምንጃር ሸንኮራ ወረዳ አዋሳኝ ላይ ከትናንት በስቲያ እሑድ ከፍተኛ ግጭት መካሄዱን የአከባቢው ነዋሪዎች ለዶቼ ቬለ ተናገሩ፡፡ በከባድ ጦር መሣሪያ ታግዞ ተካሂዷል በተባለው በዚህ ግጭት የወሰን ውዝግብ ትልቁ የግጭቱ መንስኤ ነበር ተብሏል፡፡ በግጭቱም የሰዎች ሕይወት ማለፉና በአንደኛው ወገን ቆርኬ በሌላኛው ወገን አውራ ጎዳና በመባል ከሚጠራው ስፍራ ከ2 ሺህ በላይ ነዋሪዎች መፈናቀላቸው ተነግሯል።

ኢድሪስ የተባሉ የኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሸዋ ዞን ፈንታሌ ወረዳ ነዋሪ ቆርኬ ባሉት ስፍራ እሁድ መስከረም 06 ቀን 2016 ዓ.ም. ለተከሰተው ግጭት ምክኒያት ነው ያሉትን ሲያስረዱ፤ ፋኖ ያሉት የአማራ ታጣቂዎች ወደ ኦሮሚያ ክልል ገብተው ተክለውት የነበረው ምንጃር ሸንኮራ ወረዳ የሚል ፅሁፍ ቅዳሜ መነቀሉ ነው፡፡ እንደ ነዋሪው አስተያየት ፋኖ ያሏቸው እነዚህ ታጣቂዎች በተለያዩ ጊዜያት ወደ ኦሮሚያ ክልል ገብተው የተለያዩ ጥቃትና ዘረፋ ስለሚፈጽሙ በእለቱ ከኦሮሚያ ፖሊስ ጋር በመሆን የአከባቢው ህብረተሰብ  ታጣቂዎቹን ተዋግተዋል፡፡ ቆርኬ (አውራጎዳና) በተባለች ስፍራ ይኖሩ የነበሩ መላው ነዋሪዎች ተፈናቅለዋል ነው ያሉት፡፡የአማራ ክልል ፀጥታና ኢንተርኔት

“የነበረው ግጭት የኦሮሚያ ፖሊስ ከአከባቢው ማህበረሰብ ጋር በመሆን የአማራ ፋኖ ከሚባልና አከባቢውን ከወረረው ሃይል ጋር ያደረገው ነው፡፡ የነበረው ግጭት ከባድ የነበረ ቢሆንም አሁን ፋኖን ከአከባቢው ማስወጣት ተችሏል፡፡ ፋኖዎቹ አሁን ወደ ክልላቸው ተመልሰዋል፡፡ እዚህም የነበሩ የአማራ ተወላጆች አስቀድሞም ከፋኖ ጋር እንደነበሩ ሁለቱም ክልሎች አሳምረው ያውቁታል፡፡ በዚያ እየተመላለሱ ነው ፋኖዎች ሲያሳድዱን የቆዩት፡፡ ይህ ደግሞ ግልጽ ነው፡፡”

አዎል የተባሉ የአይን እማኝ ደግሞ አውራ ጎዳና ካሉት ስፍራ ተፈናቅለው አሁን ላይ አማራ ክልል እንደሚገኙ ሲያስረዱ ይህቺ ስፍራ በአማራ ክልል ስር እንደምትተዳደር በመሞገት ነው፡፡ እኚህ ነዋሪ እንዳሉን በእሁዱ ግጭት ከኦሮሚያ ፖሊሶች ጋር የተዋጋው በአከባቢው የሚኖሩ ማህበረሰብ እንጂ ፋኖ የሚባል ኃይል በዚያ የለም፡፡ “ከችግሩ መከሰት አስቀድሞ በስፍራው የነበረው መከላከያ ነበር፡፡ የእኛ ማህበረሰብም በኮማንድ ፖስት ምክኒት መሳሪያ ይዛችሁ እንዳትንቀሳቀሱ ተባልን፡፡ መከላከያ ከዚ ከተነሳ በኋላ የኦሮሚያ ልዩ ኃይል በቦታው ተተካ፡፡ በአከባቢው የነበሩ የፉዱራል ፖሊስ አባላትም ለቀው ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ነው ተውክስ ተከፍቶ ብዙ ሰው የተጎዳና በርካቶችም የሸሹት፡፡ ዘረፋም የተካሄደው፡፡”

ፎቶ ማህደር፤ የፋኖ ታጣቂ
ፎቶ ማህደር፤ የላሊበላ ዉቅር ቤተክርስትያን እና የፋኖ ታጣቂ ምስል Solan Kolli/AFP/Getty Images

እኚህ ነዋሪ እንዳሉን አሁን ላይ አከባቢው ላይ የመከላከያ ሰራዊት ተሰማርቷል፡፡ የከባድ መሳሪያ ተውክስም ቆሟል፡፡ አስቀድሞ ግን የነዋሪዎች ሃብት ንብረት መዘረፉንም አንስተዋል፡፡በአማራ ክልል የመከላከያና የፋኖ ግጭት

ሌላው አስተያየት ሰጪያችን የፈንታሌ ነዋሪው አቶ ኢድሪስም እንደሚሉት አሁን ለጊዜው ግጭት ባይኖርም ዛሬም ድረስ ስጋቱ ግን በስፋት አለ፡፡ እንደ ነዋሪው አስተያየት ቆኘ እና እስላምአምባ በሚባሉ አከባቢዎች ዛሬም ድረስ የመሳሪያ ድምጽ ይሰማል፡፡

የፈንታሌ ወረዳው አስተያየት ሰጪያችን ፋኖ ያሉት የታጠቀ ቡድን ከዚህ በፊትም ተደጋጋሚ ጥቃት ያደርሳል ብለዋል፡፡ “በዚህ በወሰን አከባቢ ቦርጨታ በሚባል ስፍራ ሬንጀር ለብሰው ገብተው የዉኃ ማውጫ ሞተር የዘረፉት አሁን በቅርብ ጊዜ ነው፡፡ በዚያ በወሰን አከባቢው የአርሶ አደር ቤትም አቃትለው በማፈናቀላቸው ዘንድሮ ወደ 50 ሺህ ሄክታር እርሻ አልታረሰም፡፡ ይሄን ያደረገው ይህ ፋኖ የሚባል ታጣቂ ቡድን ነው፡፡ በዚህ ሳምንት ብቻ እዚሁ አስፓልት ድረስ መጥተው ጨርጨር በሚባል አከባቢ 80 ከብቶችን ዘርፈው ሄደዋል፡፡”

የምንጃር ወረዳው አስተያየት ሰጪችን አቶ አወል ደግሞ በዚያ ፋኖ የሚባል አካል የለም ሲሉ ነው የሚሞግቱት፡፡ በእሁዱ ግጭት በትንሹ ከ2 ሺህ በላይ ሰዎች ከመኖሪያቸው መፈናቀላቸውንም ያመለክታሉ፡፡ “ፋኖ የሚባል ጭራሽ በዚያ የለም፡፡ አርሶ አደሩ ነው ጦርነት ስከፈትበት ባለው ነገር የተከላከለው፡፡ በዚያ የነበሩ የአማራ ተወላጆች ብቻ ናቸው፡፡ አሁን ላይ ታፔላው ተገንትሎ ከ2 ሺህ በላይ ነዋሪዎች ሸሽተዋል፡፡”

አስተያየት ሰጪው ከተፈናቀሉት በተጨማሪ የአምስት ሰዎች ህወት ማለፉንና ከ10 በላይ መቁሰላቸውንም ያረጋግጣሉ፡፡ “አምስት ሰው ሞቷል፡፡ ቁስለኛ ከአስር በላይ ነን፡፡ ከዚያኛው ወገን የደረሰውን ጉዳት ግን አናውቅም፡፡”በአማራ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች የጸጥታው ሁኔታ እየተሻሻለ ስለመሆኑ

የፈንታሌው ነዋሪ አቶ እድሪስ በበኩላቸው አንድ ህወታቸው ያለፈና አራት ቁስለኛ ወደ መታሃራ ሆስፒታል ሲወሰዱ ማየታቸውን አረጋግጠዋል፡፡ “ውጊያው ከባድ ስለነበር የሞቱት ይህን ያህል ነው ለማለት ያስቸግር ነበር፡፡ በኛ በኩል ወደ ወለንጪቲ የተወሰዱትን ሰዎች ቁጥር ባላውቅም ወደ መታሃራ የተወሰዱት ባይነ ያየሁት አንድ ሙትና አራት ቁስለኞች ብቻ ነው፡፡ በነሱ በኩል ግን ቁጥሩን ባላውቅም ብዙ ሰው መሞቱን አውቃለሁ፡፡ ታፔላ ተነቀለ ብለው ጦርነቱን የከፈቱትም እራሳቸው ነበሩ፡፡”

ስለ እሁዱ የሁለቱ ክልሎች አዋሳን ግጭትና ጉዳቱ ዶቼ ቬለ ከአከባቢው የወረዳ እና ዞን አመራሮች ለማረጋገጥ ያደረገው ጥረት አልሰመረም፡፡ መረጃውንም ከሶስተኛ ወገንም  ማረጋገጥ አልተቻለም፡፡ አስተያየት የሰጡን የሁለቱ ወረዳዎች ነዋሪዎች ግን አሁንም ድረስ አለመረጋጋቱ እና የግጭት ስጋቱ እንዳንዣበበ አለ ሲሉ ስጋታቸውን ይግልጻሉ፡፡

ሥዩም ጌቱ

አዜብ ታደሰ

ማንተጋፍቶት ስለሺ