በአማራ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች የጸጥታው ሁኔታ እየተሻሻለ ስለመሆኑ
ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 28 2015ሰሞኑን በአማራ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች ተፈጥረው የነበሩ አለመረጋጋቶች በአንፃራዊ ሁኔታ እየተሸሻሉ መሆናቸውን የየአካባቢ ነዋሪዎች ተናገሩ፣ በጎንደር ከተማ መደበኛ እንቅስቃሴ የተጀመረ ሲሆን በሰሜን ሸዋ ደብረሲና ላይ ተዘግቶ የነበረው የአዲስ አበባ ደሴ መስመርም ተከፍቷል ተብሏል፡፡
ከልዩ ኃይል አዲስ አደረጃጀትጋር በተያያዘ በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የተፈጠረው ቅሬታ በተለያዩ አካባቢዎች መንገድ እስከመዝጋትና የንግድ ተቋማት እንዲዘጉ ያደረጉ ተቃውሞዎችን አስተናግል፣ ሰሞኑንም በተመሳሳይ መልኩ በማዕከላዊ ጎንደርና በሰሜን ሸዋ ዞን አንዳንድ አካባቢዎች ተመሳሳይ አለመረጋጋቶች ተከስተው ሰንብተዋል፡፡
በተለይ በጎንደር ከተማ ባለፉት ሁለት ቀናት የከተማ ውስጥ እንቅስቃሴ ተገድቦ የሰነበተ ሲሆን ለዚህም ምክንያት ነበር ያሉትን አንድ የከተማዋ ነዋሪ ለዶይቼ ቬሌ ተናግረዋል፡፡ዛሬ ግን በጎንደር ከተማ የተሸሻለ ነገር እንዳለ እኝሁ ነዋሪ አመልክተዋል፡፡
በተመሳሳይ በሰሜንሸዋ ዞን ሸዋሮቢት ከተማ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ወደ ስራ መመለሳቸውንና ለቀናት ተዘግቶ የነበረው የአዲስ አበባ ደሴ መስመር ለትራፊክ ክፍት መሆኑን የከተማዋ ነዋሪ አስረድተዋል፡፡
አንድ የጎንደር ከተማ የሀገር ሽማግሌ አንዳንድ የብዙሐን መገናኛ ተቋማትና ግለሰቦች የተጋነነና ያልተደረገ ነገርን እንደተደረገ አድርገው በመዘገብ ህዝብን እያደናገሩ በመሆኑ ሊጠነቀቁ እንደሚገባ አሳስበዋል
የኢትዮጵያ ሰብዐዊ መብት ኮሚሽን ሰሞኑን ባወጣው መግለጫ በአማራ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች ግጭቶች መኖራቸውን ጠቁሞ በህግ ማስከበር ሰበብ የሰብአዊ መብቶች እንዳይጣሱ አሳስቧል፣ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በበኩሉ መንግስት ችግሮችን ለመፍታት ውይይትን እንዲያስቀድም ጠይቋል፡፡
ዓለምነው መኮንን
ታምራት ዲንሳ