የመሬት ናዳ በቡኖ በደሌ ዞን
ዓርብ፣ መስከረም 10 2017የመሬት ናዳ በቡኖ በደሌ ዞን
ከጋምቤላ ተነስቶ በኢሉባቦር እና ቡኖ በደሌ ዞኖች በጅማ አዲስ አበባን የሚገናኝ አውራ መንገድ በመሬት ናዳ ምክንያት በመቆረጡ መንገደኞችን አጉላልቷል፡፡
ትናንት ሓሙስ መስከረም 09 ቀን 2017 ዓ.ም. ጠዋት 3፡00 ገደማ የተከሰተው ይህ አስፓልቱን ለሁለት የከፈለው የመሬት መንሸራተት አደጋ በቡኖ በዴሌ ዞን ዲዴሳ ወረዳ መሰራ ቀበሌ ውስጥ ነው፡፡ በዚህ የመሬት ናዳ የተነሳ ከጋምቤላ ክልል እና ኢሉባቦር ዞን ተነስተው በጅማ ዞን አጋሮ ከተማ በኩል በተለመደው መልኩ ወደ አዲስ አበባ እና ሌሎች ከተሞች ለማምራት የወጡትን መንገደኞች ከጉዞአቸው ገቷቸዋልም ነው የተባለው፡፡
በመደርመስ የተከፈለውን አስፓልት ለመጠገን ትልቅ አቅምና ጊዜ የሚወስድ በመሆኑ በዛሬው እለት መንገደኞችን በተለያዩ አማራጮች ለማሻገር ጥረት እየተደረገ እንደሆነም የአከባቢው ባለስልጣናት ለዶይቼ ቬለ ገልጸዋል፡፡
የአስፓልት ናዳ አደጋ
አስደንጋጭ የተባለው ይህ የመሬት ናዳ ትናንት ጠዋት ሶሰድት ሰዓት ግድም መከሰቱ ነው የተነገረው፡፡ በቡኖ በደሌ ዞን ዴዴሳ ወረዳ የተከሰተው ከፊል ምዕራብ እና ደቡብ ምዕራባዊ የኢትዮጵያ አከባቢዎችን ከመሃል የአገሪቱ አከባቢዎች ጋር የሚያገናኘውን አውራ የአስፓልት መንገድን ለሁለት የከፈለው ይህ የመሬት ናዳ አደጋ ከሰሞኑ በተከታታይ በጣለው እጅግ ከባድ ዝናብ ምክንያት ሳይሆን እንዳልቀረም አስተያየቶች ተሰጥቷል፡፡የመሬት መንሸራረት መንስኤና መፍትሄው
የመሬት ናዳው ሲከሰት በአከባቢው እንደነበሩና ክስተቱን የታዘቡት ሳሊያ የተባሉ በአከባቢው በንግድ ስራ ላይ የተሰማሩት አስተያየት ሰጪ፤ “ይህ አደጋ ትናንት ጠዋት ነው የተከሰተው፡፡ ከዚሁ ከአጠገቤ አንድ ሲኖትራክ እንጨት ጭኖ የነበረ አሽከርካሪ በዚህ አደጋው በተከሰተበት ስፍራ ሲያልፍ ቦታው ላይ የመንጣጣት ደምጽ ይሰማል፡፡ ከዚያን ልክ ያቺን ስፍራ ተሻግሮ ወደ ኋላው ሲመለከት አስፓልቱ ተደርምሶ ለሁለት ተከፍሏል፡፡ እሱን ይከተል የነበረው ኑሬ የሚባል አሽከርካሪ ከዚሁ ተነስቶ ወደ አጋሮ ሲጓዝ ወደ ገደሉ ልገባ ለጥቂት ነው የተረፈው ፡፡ ከዚያን አሽከርካሪዎች እየበረሩ እንዳይገቡበት እርጥብ ቅጠሎችን ቦታው ላይ እያኖሩ ሁሉም እንዲሰማ ሆነ፡፡ ተደርምሶ የተከፈለው አስፓልት አሁን እየሰፋ ነው፡፡ ወደ 20 ሜትር ሆኗል ስፋቱ መንገደኞች እጅግ በጣም እየተቸገሩ ነው” ብለዋል፡፡
መንገደኞችን ለማጓጓዝ ጊዜያዊ መፍትሄ
ይህ ቦታ ከዚህ በፊት መጠነኛ የመሰንጠቅ ምልክት አሳይቶ እንደነበርና ከዚያ በአግባቡ አለመሰራቱንም የአይን እማኝ የአከባቢ ነዋሪዋ ለዶይቼ ቬለ አስረድተዋል፡፡ አሁን ላይ ከጋምቤላ እና መቱ ወደ መሃል አገር ሲጓዙ የነበሩ መንገደኞች እየተጉላሉ እየተቸገሩም ነው ብለዋል በአስተያየታቸው፡፡በአማራ ክልል በያዝነው ወር በተከሰተ የመሬት ናዳ በሶስት ወረዳዎች 19 ሰዎች ሞቱ
የትናንቱ የአስፓልት መናድ አደጋ መከሰትን ተከትሎ በአከባቢው ተገኝተው መንገደኞች እልባት እንዲያገኙ እያስተባበሩ መሆናቸውን የነገሩን ኢንስፔክተር ዓለሙ እምሩ የተባሉ የአከባቢው የትራፊክ አስተባባሪ ከጂማ ወደ ምዕራብ የሚመጡ ተሽከርካሪዎች እና ጋምቤላና መቱን ጨምሮ ከምዕራብ ወደ ጅማ እና መሃል አገር የሚያመሩ የህዝብ እና እቃ ጫኝ አሽከርካሪዎች ከናዳው ማዶ ለማዶ ቀርተዋልም ነው ያሉት፡፡
“አደጋው የተከሰተበት ስፍራ ከከተማ ወደ 30 ኪ.ሜ ወጣ ብሎ ነው የሚገኘውና የጸጥታ ሃይሎች እና የትራፊክ ባለሙያዎችን ወደ ስፍራው አሰማርተን መንገደኞችን እንዲረዱ እያደረግን ነው፡፡ ማዶ ለማዶ የቀሩት ተሽከርካሪዎች ተሳፋሪዎችን እንዲቀያየሩ እቃ የጫኑም ተቀያይረው ወደ መጡበት አቅጣጫ እንዲመለሱ ለጊዜያዊነት እያስተባበርን ነው፡፡ መንገደኞች በእግራቸው እየተሸገሩ እቃዎችንም ናዳውን አሻግረው እየጫኑ ነው ወደሚፈልጉት አቅጣጫ እየተጓዙ ያሉት” ብለዋል፡፡
የናዳው ጊዜያዊና ዘለቄታዊ እልባት
ይህ አደጋው ያጋጠመው አውራ መንገድ አዲስ አበባን በጅማ በኩል በደሌ፣ መቱ እና ጋምቤላ ከመሳሰሉ ከተሞችና አከባቢዎች ጋር የሚገናን አስፓልት ነው፡፡ የዲዴሳ ወረዳ የመንገድና ሎጂስቲክ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ባጫ መርጋ ትናንት ሶስት ሰዓት አከባቢ ይህን አውራ መንገድ ለሁለት የከፈተለው አደጋ በጣሊያን የተሰራው ከአስፓልቱ ስር ያለው ገረጋንት በመንሸራተቱ የተከሰተ ነው ብለዋል፡፡ የአከባቢው ባለስልጣን በአስተያየታቸው “ከሰሞኑ በአከባቢው የጣለ ከፍተኛ ዝናብ በጎርክ ሁለት አስተኛ ድልድዮችን አፍርሶ አሁን ህን የአውራ ጎዳናው አስፓልት ስንድ ሶስተኛው አደጋ ነው” ብለዋል፡፡ አክለውም ከአዲስ አበባ 420 ኪ.ም. ላይ በሚገኝ ስፍራም አስፓልቱ እየተሰረሸረ ተጨማሪ አደጋዎች እየጣለ ካለው ከፍተኛ መጠን ካለው ዝናብ ጋር ሊከሰት እንደሚችል አንስተዋል፡፡በአማራ ክልል በያዝነው ወር በተከሰተ የመሬት ናዳ በሶስት ወረዳዎች 19 ሰዎች ሞቱ
አስፓልቱ በ2003 አከባቢ በሜድሮክ ኢትዮጵያ መስራቱን የጠቆሙት የአከባቢው ባለስልጣን አሁን እየተንሸራተተ የሚገኘው የድልድ ኮንክሪት ከ90 ዓመታት ግድም በፊት በጣሊያን እንደተሰራ አለመቀየሩን አስረድተዋል፡፡ አሁን የመንገደኞች መጉሏላትን ተከትሎ የተናደውን አስፓልት መልሶ መጠገን ቀላል ባለመሆኑ ሌሎች የመንገድ ጥገና አማራጮች እየተወሰዱም ነው ብለዋል፡፡ “የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ጅማ ቅርንጫፍ ማሽነሪዎችን ወደዚህ በማምጣት ተለዋጭ መንገዶችን ሊሰራ ነው” ያሉት ኃላፊው የወረዳና ቀበሌዎች አገናኝ አነስተኛ መንገዶችን ተጨማሪ 15 ኪ.ሜ ግድም በመተገን እንደመፍትሄ ለመውሰድም እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
ስዩም ጌቱ
ኂሩት መለሰ
ፀሐይ ጫኔ