በአማራ ክልል በያዝነው ወር በተከሰተ የመሬት ናዳ በሶስት ወረዳዎች 19 ሰዎች ሞቱ
እሑድ፣ ነሐሴ 19 2016ባለፈው ዓርብ ለቅዳሜ አጥቢያ የክረምቱን ዝናብ ተከትሎ የጣለ ከባድ ዝናብ ባስከተለው ናዳ በሰሜን ጎንደር ዞን ጠለምት ወረዳ የ10 ሰዎች ህይወት ማለፉን የሰሜን ጎንደር ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የዞኑ ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ቢምረው ካሳ ዛሬ ለዶይቼ ቬሌ በስልክ ተናግረዋል፡፡ ከ200 በላይ እንስሳት በናዳው መሞታቸውን አቶ ቢምረው ገልፀዋል፡፡
የሰሜን ጎንደር ዞን አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ፅህፈት ቤት ተጠሪ አቶ ሰላምይሁን ሙላት በበኩላቸው በናዳው ህይወታቸው ካለፈው ወገኖች በተጨማሪ 8 ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸው በህክምና ጣቢያዎች ህክምና እየተደረገላቸው ነው ብለዋል፡፡ በዚህ የተፈጥሮ አደጋ 2700 ሰዎች የተፈናቀሉ ሲሆን በ1700 ሄክታር ማሳ ላይ የተዘራ ሰብልም መውደሙን አስረድተዋል፡፡
የዙኑ ምክትል አስተዳዳሪና የንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ኃላፊው አቶ ቢምረው እንዳሉት የትናንትናውን ጨምሮ በያዝነው ወር በተከሰተ ናዳ በጠለምት፣ በበየዳና አዲአርቃ ወረዳዎች 19 ሰዎች ህይወታቸው አልፏል፡፡
የተፈናቀሉ ወገኖችንና ስጋት ያለባቸውን አካላት ወደ ደረቃማ ቦታ ለማስፈር ግብረ ኃይል ተቋቁሞ እየተሰራ መሆኑን አቶ ቢምረው ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት የትንበያ እና ቅድመ ማስጠንቀቂያ ምርምር ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አሳምነው ተሾመ የአማራ ክልልን ጨምሮ ብዙ የሀገሪቱ አካባቢዎች በሚቀጥሉት 10 ቀናት ከመካከለኛ እስከ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚኖራቸው ለዶቼ ቬለ ሰሞኑን አመልክተዋል፡፡ ተቋማቸው ክረምት ዋነኛ የዝናብ ወቅታቸው በሆኑ አካባቢዎች "ከመደበኛ በላይ የሆነ የዝናብ ስርጭት" ይኖራል ሲል ትንበያ ማስቀመጡንም አብራርተዋል።
* በድምፅ ዘገባው የሰሜን ጎንደር ዞን የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ኃላፊ አቶ ሰላምይሁን ሙላት የሚለው/ የሰሜን ጎንደር ዞን አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ፅህፈት ቤት ተጠሪ አቶ ሰላምይሁን ሙላት በሚለው እንዲታረም በትህትና እንገልፃለን።
ዓለምነው መኮንን
ልደት አበበ