ከታላቁ ሩጫ ታዳሚያን 12ቱ በእስር ላይ ናቸው ተባለ
ዓርብ፣ ኅዳር 14 2016ባለፈው እሁድ አዲስ አበባ ውስጥ በታላቁ ሩጫ ወቅት የተቃውሞ ድምፆች ካስተጋቡ መካከል ለእስር የተዳረጉ እንዳሉ ተገለጸ ። ባለፈው እሁድ፤ ኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም የታላቁ ሩጫ ተሳታፊዎች በተለያዩ ጭፈራዎች ታጅበው ሆታ እና መፈክሮችን ሲያስተጋቡ ተደምጠዋል ። «አዲስ አበባ ውስጥ ኹከት እና ብጥብጥ ለመፍጠር አስባችኋል» እንዲሁም «ፖለቲካዊ ይዘት ያለው ንግግር አድርጋችኋል» የተባሉ 12 ተጠርጣሪዎች በአዲስ አበባ ፖሊስ ተይዘው በእሥር ላይ እንደሚገኙ ተገልጿል ። ባለፈው ሳምንት እሁድ በታላቁ ሩጫ ላይ ከተሰሙ መፈክሮቹ መካከል፦ አዲስ አበባን የሚመለከት ይገኝበታል ። «እየመጡ ነው» የሚሉ መፈክሮችም ተስተጋብተዋል ።
በውድድሩ ማስጀመሪያ መርኃ ግብር ላይ ፕሬዚዳንት ሣኅለወርቅ ዘውዴ፤ የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ እንዲሁም ሌሎች ከፍተኛ አመራር ተገኝተውም ነበር ። በታላቁ ሩጫ ተቃውሞ ከተስተጋባ እና መፈክሮች ከተሰሙ በኋላአንዳንድ ለመንግሥት ድጋፋቸውን የሚገልጹ የማኅበራዊ መገናኛ አውታር ተጠቃሚዎች ከእስርም ባሻገር መጥፎ ነገሮች እንዲከሰቱ ጥሪ ሲያስተላልፉ ነበር ።
ታላቁ ሩጫ ላይ ብጥብጥ ለመፍጠር ሞክረዋል የተባሉ ታሠሩ
ባለፈው እሁድ፤ ኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም በተደረገው 23 ኛው የታላቁ ሩጫ ውድድር ላይ «አዲስ አበባ ላይ ኹከት እና ብጥብጥ ለመፍጠር አስባችኋል» በሚል እንዲሁም «ፖለቲካዊ ይዘት ያለው ንግግር አድርጋችኋል» የተባሉ 12 ተጠርጣሪዎች በአዲስ አበባ ፖሊስ ተይዘው በእሥር ላይ እንደሚገኙ ተገለፀ። ተጠርጣሪዎቹን ዛሬ በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ሦስተኛ ፖለስ ጣቢያ ውስጥ በአካል እንዳገኟቸው እና በነፃ ጥብቅና እንደሚቆሙላቸው እንደገለፁላቸው የነገሩን ጠበቃ ሰለሞን ገዛኸኝ ከ12ቱ ተጠርጣሪዎች በተጨማሪ ሌሎች ሦስት ወጣቶች ተይዘው እንደነበር እና ከምርመራ በኋላ መለቀቃቸውን መስማታቸውን ተናግረዋል።
በተመሳሳይ ሰለሞን አላምኔ የተባሉ የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ የብሔራዊ ምክር ቤት አባል «ከታላቁ ሩጫ ጋር ተያይዞ ውድድሩ ከመካሄዱ አስቀድሞ ሩጫው ላይ ኹከት እና ብጥብጥ ሊፈጠይ ይችላል ከሚል ሥጋት» ተጠርጥረው መያዛቸውንና ፍርድ ቤት ቀርበው የአሥር ቀናት የጊዜ ቀጠሮ እንደተሰጣቸው ፓርቲው ለዶቼ ቬለ ገልጿል።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን
ስለ ጉዳዩ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽንን ምላሽ ለማካተት ወደ ኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ በተደጋጋሚ የተደረገው የስልክ ጥሪ ባለመነሳቱ የኮሚሽኑን ምላሽ ለጊዜው ማካተት አልተቻለም።
45 ሺህ ሰዎች እንደተሳተፉበት በአዘጋጆቹ በተነገረለት 23ኛው የ2016 ዓ.ም ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ 10 ኪ.ሜ ውድድር ላይ የፖለቲካ ይዘት ያለው መልእክት አስተላልፋችኋል በሚል ተጠርጥረው ከተያዙት 12 ሰዎች በተጨማሪ የታሠሩ ጓደኞቻቸውን ለመጠየቅ ወደ ፖሊስ ጣቢያ የሄዱ ሌሎች ሰዎች መካከልም ተይዘው የነበሩ የተለቀቁ ሰዎች መኖራቸውንም ስለመስማታቸው ጠበቃ ሰለሞን ገዛኸኝ ለዶቼ ቬለ ገልፀዋል።
ጠበቃ ሰለሞን ገዛኸኝ 12ቱ ሰዎች በምን ምክንያት ተጠርጥረው እንደተያዙ እንደገለፁላቸውም ነግረውናል።
«የተጠረጠሩበት በአዲስ አበባ ላይ ኹከትና ብጥብጥ ለመፍጠር አስባችኋል እና ፖለቲካዊ ይዘት ያለው ንግግር አድርጋችኃል የሚል ነው።»
እነማንስ ተፈቱ ወይንም ይፈቱ ተባሉ?
በተመሳሳይ የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ የብሔራዊ ምክር ቤት አባል የሆኑ ግለሰብ ውድድሩ ከመካሄዱ አስቀድሞ ቅዳሜ እለት ሩጫው ላይ ኹከት እና ብጥብጥ ሊፈጠይ ይችላል ከሚል ሥጋት ተጠርጥረው መያዛቸውንና ፍርድ ቤት ቀርበው የጊዜ ቀጠሮ እንደተሰጣቸው የፓርቲው አመራር ወይዘሮ ቀለብ ስዩም ለዶቼ ቬለ ገልጿል።
ጠበቃ ሰለሞን ገዛኸኝ ከ12ቱ ተጠርጣሪዎች በተጨማሪ ሌሎች ሦስት ወጣቶች ተይዘው እንደነበር እና ከምርመራ በኋላ መለቀቃቸውን መስማታቸውን ተናግረዋል።
በጉዳዩ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ ኮሚሽንን ምላሽ ለማካተት ያደረግነው ጥረት ለጊዜው አልተሳካም።
በሌላ በኩል ከ47 ቀናት በፊት የተያዙት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቅዱስ ሲኖዶስ ቃለ ጉባኤ ያዥ መሪጌታ ብርሃኑ ተክለያሬድ ከእሥር እንዲለቀቁ ዛሬ ብይን መሰጠቱን ጠበቃ ሰለሞን ገዛኸኝ ነግረውናል።
ሰለሞን ሙጬ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር