የአዲስ አበባ ጸጥታና የሚታሰሩ ወጣቶች ጉዳይ
ዓርብ፣ መጋቢት 9 2014ማስታወቂያ
ከአድዋ በዓል አከባበር ጋር ተያይዞ አዲስ አበባ ውስጥ ብዙ ወጣቶች ምስላቸው ከማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች እየተፈለገ እና በዕለቱ በተለያዩ ቦታዎች የመንግሥት ሰዎች ባስቀመጥዋቸው ካሜራዎች በተቀጹ ምስሎች ደጋፊነት በጅምላ እየተያዙ እየታሰሩ ነው ተባለ። ይህንን ያለው የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትሕ ( ኢዜማ )ድርጊቱ የከተማው ወጣት ሀሳብ እንዳይሰጥ፣ እንዳይቃወም ለማሸማቀቅ ነው ብሏል። የከተማዋ ወጣት አንገቱን እንዲደፋ እየተደረገ ነው ያለው ኢዜማ ታሳሪዎቹ እንዲፈቱ ፣ ወንጀል ሰርተዋል ከተባለም በግልጽ ለፍትሕ እንዲቀርቡ ጠይቋል። ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ በበኩሉ ከሰሞኑ ታስረው አባ ሳሙኤል የተባለው እሥር ቤት የተወሰዱ ወጣቶች በምግብ ፣ በመድኃኒት እና በውኃ እጦት እንዲማረሩ እየተደረገ ነው በዚህም ከፖለቲካ ተሳትፎ እንዲርቁ እየተሠራ ነው ብሏል። ከታሰሩት ወጣቶች መካከል 20 ዎቹ ትናንት ወደ አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን እንዲመጡ ከተደረገ በኋላ ዛሬ ጥዋት ቤታቸው እንዲበረበር ተደርጓልም ብሏል። የደንብ ጥሰት ፈጽመዋል ያላቸውን 146 አባላቱን እንዳሰናበተ የተናገረው የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የሚታፈስ ወጣት የለም በማለት እሥሩን በተመለከተ ለሚቀርበው ቅሬታ ትናንት ምላሽ ሰጥቷል።
ሰሎሞን ሙጬ
ሸዋዬ ለገሠ
ኂሩት መለሰ