1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ተፈናቃዮችን የማቋቋም ውጥንና የተፈናቃዮች ሥጋት

ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 16 2016

ከኦሮሚያ ክልል ከተለያዩ ዞኖች ተፈናቅለው አማራ ክልል ውስጥ በመጠለያ ጣቢያዎች የቆዩ ተፈናቃዮች መንግስት በግዴታ ወደ ተፈናቀሉበት ቀዬያቸው ሊመልሳቸው መሆኑን በመግለጽ ተቃውሟቸውን አሰሙ ።

https://p.dw.com/p/4aaWv
ከኦሮሚያ ክልል የተፈናቀሉ ሰዎች
ከኦሮሚያ ክልል ጥቃት ሸሽተው የተፈናቀሉ ሰዎችምስል Alemenew Mekonnen/DW

ተፈናቃዮች ያፈናቀላቸው የፀጥታ ሥጋት አልተቀረፈም ብለዋል

ከኦሮሚያ ክልል ከተለያዩ ዞኖች ተፈናቅለው አማራ ክልል ውስጥ በመጠለያ ጣቢያዎች የቆዩ ተፈናቃዮች መንግስት በግዴታ ወደ ተፈናቀሉበት ቀዬያቸው ሊመልሳቸው መሆኑን በመግለጽ ተቃውሟቸውን አሰሙ ።

ተፈናቃዮቹ እንደሚሉት፦ ወደ ነባር ቀዬያቸው ለመመለስ ሙሉ ፈቃደኛ ቢሆኑም ያፈናቀላቸው የፀጥታ ችግር ግን አሁንም አለመቀረፉን ይናገራሉ ። ተፈናቃዮቹ ይመለሱበታል የተባሉት አከባቢዎች ባለስልጣናት በበኩላቸው በጉዳዩ ላይ ገና እየሠራንበት ነው እያሉ ነው ።

ተፈናቃዮችን ያፈናቀለው የፀጥታ ችግር አለመቀረፍና የተፈናቃዮች የደህንነት ሥጋት

ለደህንነታቸው ሲባል ስማቸውን ከመግለጽ ተቆጥበው አስተያየታቸውን የሰጡን የሰሜን ወሎ ኃይቅ ተፈናቃዮች መጠለያ ውስጥ የሚገኙ የኢትዮጵያ  የአገር ውስጥ ተፈናቃይ የግዳጅ መጠለያ ጣቢውን የማስለቀቅና ወደ ነባር ቀዬያቸው የመመለስ ተግባር ተጠናክሮ ቀጥሏል ነው የሚሉት፡፡ ከሦስት ዓመታት በፊት በብሔር ተኮር ግጭት ምክንያት ከምዕራብ ኦሮሚያ ሆሮጉዱሩ ወለጋ ዞን ጃርደጋ ጃርቴ ወረዳ ተፈናቅለው ኃይቅ ተፈናቃዮች ካምፕ መቀላቀላቸውን የገለጹልን እኚህ አስተያየት ሰጪ 400 ገደማ አባወራዎች ይገኙበታል ካሉት የተፈናቃዮች ካምፕ ከተወሰኑት ውጪ አብዛኞቻቸው ያፈናቀላቸው የፀጥታ ስጋቱ መቀረፉን ስለሚጠራጠሩ ወደ ቀዬያቸው ለመመለስ ፈቃደኛ አይደሉም፡፡

"አሁን ችግር ላይ ወድቀናል፡፡ ወለጋ አገራችን ነው፡፡ ተወልደን ያደግንበት፡፡ ዛሬ ጠርተውን አይደለም እኛ ጠይቀን የምንሄድበት ነበር፡፡ ግን አሁንም የፀጥታ ስጋት አለን፡፡ በዚህ ሁኔታ ነው እንግዲህ የሁለቱ ክልሎች አመራር ስለተፈራረሙ በሚል በግዳጅ ወደዚያ ሊመልሱን እንድንፈርም የሚስገድዱን” ብለዋል አስተያየት ሰጪው፡፡

ከዚሁ የተፈናቃዮች መጠለያ ጣቢያ አስተያየታቸውን የሰጡን ሌላኛው አስተያየት ሰጪም፤ "አገራችሁ ሰላም ነው፡፡ ካምፕ ለቃችሁ ትሄዳላችሁ እያሉን ነው፡፡ ትናንት ነበር እንደውም ካምፑን ትለቃላችሁ ያሉን፡፡ ዛሬም መጥተዋል ጫና እያደረጉብን ነው፡፡ እኛ ግን አንሄድም አገራችን ሰላም አይደለም እያልን ነው፡፡ መንግስት እና መንግስት ተፈራርመዋል ትሄዳላችሁ እያሉን ነው” ብለዋል፡፡

ከኦሮሚያ ክልል ተፈናቃዮች
ከኦሮሚያ ክልል ተፈናቃዮች፦ ወደ ትውልድ ቀዬያቸው እንዳንመለስ የፀጥታ ሥጋት አለብን ብለዋልምስል Alemenew Mekonnen/DW

ከዚያው ከሰሜን ወሎ ጃራ የተፈናቃዮች ካምፕ አስተያየታቸውን የሰጡን ተፈናቃይም ተፈናቃዮችን በግዳጅ ወደ ነባር ቀዬያቸው የመመለሱ ጥረት በሁሉም ቦታ የሚስተዋል ነው ብለዋል፡፡ "በግድ ትሄዳላችሁ፡፡ ካምፑንም ትለቃላችሁ ብለውናል፡፡ አንሄድም የምትሉ ከሆነ የሚሰጣችሁ አገለግሎት ቆሞ ከካምፕ ትወጣላችሁ ተብለናል፡፡ ኅብረተሰቡ ግን አከባቢው ወደ አስተማማኝ ሰላም ሲመለስ በራሱ ወጪ እንኳ ወደ ቀዬው ለመመለስ ፈቃደኛ መሆኑንና አሁን ግን አከባቢው ባለመረጋጋቱ ስጋት እንዳለው ገልጸውላቸዋል” ሲሉም ሃሳባቸውን አብራርተዋል፡፡

የተፈናቃዮች ርዳታ መቋረጥ

አስተያየት ሰጪ ተፈናቃዮቹ ርዳታ ተቋርጦባቸው አስቸጋሪ ያሉት ሁኔታ ውስጥ ከወደቁም ወራት እየተቆጠሩ መሆኑን ያስገነዝባሉ፡፡ "ርዳታ የለም፡፡ ርዳታ ካገኘን ሦስት ወር ተቆጥሯል አሁን ፡፡ መንግስት ወደ አገራችሁ ካልተመለሳችሁ አትረዱም ብሎናል” ያሉን የኃይቅ መጠለያ ጣቢያ ተፈናቃይ ሲሆኑ፤ በጃራ መጠለያ ጣቢያ የተጠለሉት አስተያየት ሰጪም በተመሳሳይ "አመልድ የተባለ ግብረሰናይ ድርጅት ርዳታውን ሲሰጠን ቢቆይም መንግስት ወደ ቀዬያችሁ ካልተመለሳችሁ ርዳታ አይሰጥም እያለን ነው” ይላሉ፡፡

ተፈናቃዮች እየተገደድንበት ነው ስላሉት ጉዳይ ላይ ማብራሪያ እና አስተያየት ለመጠየቅ ለአማራ ክልል ኮሚዩኒኬሽን ጽ/ቤት እና ለክልሉ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ኮሚሽን የሥራ ኃላፊዎች ከዶይቼ ቬለ ቢደወልም ስልካቸው ባለመነሳቱ አስተያየታቸውን ማካተት አልተቻለም፡፡

ተፈናቃዮች ያለፈቃዳቸው መመለስን አልፈለጉም
ተፈናቃዮች፦ መንግስት ወደ ቀዬያችሁ ካልተመለሳችሁ ርዳታ አይሰጥም እያለን ነው ብለዋልምስል Alemenew Mekonnen/DW

ተፈናቃዮች ይመለሱበታል የተባሉ አከባቢዎች ያሉ ዝግጅቶች

ተፈናቃዮቹ ይመለሱበታል ከተባለላቸው አከባቢዎች የምስራቅ ወለጋ ዞን ኪረሙ እና ጊዳ አያና ወረዳዎች ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ከዚሁ ጋር በማያያዝ አስተያየታቸውን ከጠየቅናቸው ደግሞ የምስራቅ ወለጋ ዞን ምክትል ዋና አስተዳዳሪ አቶ ገመዳ ተፈራ ይገኛሉ፡፡ ኃላፊው እንደሚሉት በአከባቢው የተፈናቀሉትን ወደ ነባር ቀዬያቸው ከመመለስ ባሻገር በአሁኑ ወቅት ከክልሉ ወጥተው ወደ ሌላ ክልል የተፈናቀሉትን ወደ ቀዬየያቸው የመመለስ ዝግጅት አልተጠናቀቀም፡፡

"የሁለቱ ክልሎች አመራር ተወያይተው የተግባቡበት በተጠና መንገድ ብቻ ተፈናቃዮችን መመለስ ነው፡፡ ሁለት ነገሮች አሉ፡፡ አንደኛው ለአሁኑ ለምሳሌ ከኪረሙ ወረዳ ውስጥ በዚያው ወረዳ ከቦታ ቦታ የተፈናቀሉ አሉ፡፡ ሁሉም ማህበረሰብ ነው በመጠራጠር የተፈናቀለው፡፡ እነዚህ አሁን ላይ በውይይት እርቅ እየፈጠሩ በመንግስት መዋቅርም ድጋፍ የተረጋጋ የፀጥታ ይዞታ በመኖሩ ወደ ቀዬያቸው እየተመለሱ ነው፡፡ ከኪረሙ በተጨማሪ በጊዳ እና ሊሙ ወረዳዎች ተመሳሳይ ተግባራት ተከናውነዋል፡፡ ሌላኛው ግን ከኦሮሚያ ወደ አማራ ክልል የተፈናቀሉትን በተመለከተ ግን ወደ ፊት የምንሄድበት እንጂ ለአሁኑ ይህ ነው የምልህ ምንም ነገር የለም” ብለዋል፡፡

ተፈቃዮች እና ሰብአዊ መብታቸው

የኢትዮጵያ ሰብኣዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በቅርቡ ባወጣው መግለጫ እንዳመለከተውም ለአገር ውስጥ ተፈናቃዮች  የሚደረገው ድጋፍ እና እንክብካቤ አመርቂ አለመሆኑን ጠቅሷል፡፡ ተፈናቃዮችን ወደ ነባር ቀዬያቸው የመመለስ ውሳኔን በተመለከተም ከዚህ በፊት ከዶይቼ ቬለ ጋር ቆይታ ያደረጉት የኮሚሽኑ የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች፣ ስደተኞችና ፍልሰተኞች ጉዳይ ኃላፊ እንጉዳይ መስቀሌ ተፈናቃዮችን በዘላቂነት ለማቋቋም አስቀድሞ መሠራት ያለበት ተግባር አለ ብለዋል ።

ከኦሮሚያ ክልል ተፈቃዮች
ተፈቃዮች ብርቱ የሰብአዊ መብት ጥሰት መኖሩን ይገልጻሉምስል Alemenew Mekonnen/DW

"በዋነኛነት ተፈናቃዮችን ያፈናቀላቸው መንስኤ መቀረፍ አለበት፡፡ ግጭት ከሆነ ያፈናቀላቸው ወደ ቀዬያቸው ስንመልሳቸው ዳግም ላለመፈናቀላቸው ዋስትና የሚሆን ሥራ መሠራት አለበት፡፡ የተፈናቃዮች ፈቃደኛነትና ክብራቸውም መጠበቅ አለበት” ብለውናል፡፡ ባጠቃላይም ተፈናቃዮች በዘላቂነት በሚቋቋሙበት አማራጭ ኑሮያቸውን በዘላቂነት ለመምራት የሚስችላቸው ሥራ መከወን አለበትም ነው የተባለው፡፡

ዓለማቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት (IOM) በቅርቡ ባወጣው መረጃ መሰረት በኢትዮጵያ ውስጥ 4.3 ሚሊየን ገደማ የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች ይገኛሉ፡፡

ሥዩም ጌቱ 

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ኂሩት መለሰ