1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ፣ ኬንያ እና የኢትዮጵያው የድርድር ተስፋ

እሑድ፣ መስከረም 22 2015

አሁን ያለውን የግጭት ዐውድ ስንመለከት የአሁኑ የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ እና የቀድሞው የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ዑህሩ ኬንያታ ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ የነበሩበትን ሁኔታ ስናይ በማህበራዊ መገናኛና እና በመደበኛ መገናኛ ብዙኃን ለዘብተኛ ግጭት ውስጥ እንደነበሩ ማየት ይቻላል።

https://p.dw.com/p/4Heap
Kenia | Amtseinführung Präsident William Ruto
ምስል Baz Ratner/REUTERS

የኬንያ ነዋሪዎች አስተያየት

አዲሱ የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ የቀድሞው የሀገሪቱ መሪ ዑህሩ ኬንያታ በኢትዮጵያ ውስጥ እና በሌሎች ሀገሪቱ በምትዋሰንባቸው ቀጣናዎች ሰላም እና ፀጥታ እንዲሰፍን የጀመሩትን ጥረት አጠናክረው እንዲቀጥሉ ፍላጎታቸው መሆኑን በበዓለ ሲመታቸው ወቅት ባደረጉት ንግግር ገልፀው ነበር።

ፕሬዝዳንቱ በንግግራቸው ዑህሩ ኬንያታ በኢትዮጵያ እና በሌሎች አካባቢዎች የጀመሩትንና ሲሠሩበት የቆዩትን ሰላምን የማስፈን ጥረት አጠናክረው እንዲቀጥሉ ድጋፋቸውን እንደሚያደርጉ ገልፀዋል።
ይህንን ሥራቸውን በኬንያ ሕዝብ እና መንግሥት ሥም እንዲያጠናክሩም ፍላጎታቸውን ገልፀውላቸዋል።

ይህንን በተመለከተ ናይሮቢ ከተማ ውስጥ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንን እና ኬንያዊያን ወደ ናይሮቢ ተጉዞ ለነበረው የአዲስ አበባው ወኪላችን ሰለሞን ሙጩአስተያየታቸውን አጋርተውታል።

" ሥልታዊ ውሳኔ ይመስለኛል። ምክንያቱም የኬንያን የፖለቲካ ምህዳር ስትመለከተው በአብዛኛው ጎሳን መሠረት ያደረገ ነው። ስለዚህ ትስስርን ለማጠናከር አንዱ ዘዴ በጎሳ አስተሳሰብ ውስጥ ያለን ማህበረሰብ ማቀራረብ ነው። ያንን ማድረግ እጅግ በጣም ጠቃሚ ነው።
አሁን ያለውን የግጭት ዐውድ ስንመለከት የአሁኑ የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ እና የቀድሞው የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ዑህሩ ኬንያታ ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ የነበሩበትን ሁኔታ ስናይ በማህበራዊ መገናኛና እና በመደበኛ መገናኛ ብዙኃን ለዘብተኛ ግጭት ውስጥ እንደነበሩ ማየት ይቻላል።
እናም ያንን የመሰለ መልዕክት መተላለፉ ለእኛ ግጭት ውስጥ ተሳታፊ ላልሆነው እንኳን መተሳሰርን የሚያጠናክር ነው። መልዕክቱ ሰላምን፣ መተሳሰርን የሚያበረታታ ነው። በቀጣናው ጭምር። ምክንያቱም መልዕክቱ የተላለፈው ለኬንያ ብቻ አልነበረም።
ኬንያዊያን ያ ችግር ራሳቸውን የሚመለከት ቢሆንም በቀጣናው ተጽእኖ ማሳደር ይፈልጋሉ። ወዳጆች ነው ። በጠቅላላ በቀጣናው የእኛ ማህበረሰብ አለ።
ስለዚህ ያ መልእክት በጠቅላላው በቀጣናው ስር ይሰዳል ወይም ይሰርጻል ብለን እናምናለን።
በምርጫ ወቅት ተቀናቃኝህ የነበረ ሰው በዚያን ጊዜ ቢፎካከርህ የእኔ እና የአንተ ማህበረሰብ እየተጋጩ ይቀጥላሉ ማለት አይደለም። ስለዚህ መልዕክቱ [የአሁኑ የኬንያ ፕሬዝዳንት ሚካኤል ሩቶ በበዓለ ሲመታቸው ወቅት ኢትዮጵያን በተመለከተ የተላለፈው] ለቀጣናውም ይሠራል ብዬ አምናለሁ። "

"በእርግጥ  ሰላምን ያሳድጋል ብየ አስባለሁ። ምክንያቱ ደግሞ ኬንያ በብዙ ኬንያን የመሰሉ የምስራቅ አፍሪካ ሀገሮች ላይ  ወሳኝ ሚና እየተጫወተች ትገኛለች።
የቀድሞው የኬንያ ፕሬዝዳንት ሰላም እንዲመጣ መሰየሙ እና ኬንያ ያንን ኃላፊነት መውሰዷ ሰዎች ኬንያን እንደ ታላቅ ወንድም ማየታቸውን ያሳያል።
ስለዚህ ይህ የኬንያ ኃላፊነት እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ተመሳሳይ ጉዳይ ላለባቸው ሀገሮች ጠቃሚ ነው። ስለዚህ ሰላምን የሚያሳድግ ጉዳይ ነው ወይ ? አዎ ይመስለኛል።
የቀድሞው ፕሬዝዳንት ዑህሩ በተቃውሞ ጎራ እንዲሁም ሩቶ ፕሬዝዳንት የመሆናቸው ለውጥ እንዳለ ሆኖ በጋራ መቆማቸው የሚያሳየው ፖለቲካ ፖለቲካ ነው ፣ በመጨረሻው ሰዓት ሁላችንም ወንድምና እህት መሆናችንን ነው። ልዩነቶች በስተመጨረሻም ቢኖሩም እንኳን ወደ አንድ መጥተን አፍሪካን እናሳድግ። ስለዚህ የፖለቲካ ልዩነቶች በቀጣናው ላይ ግጭት እንዲባባስ ምክንያት ሊሆኑብን አይገባም።"

"ኢትዮጵያ እና ኬንያ ለረጅም አመታት የዘለቀ ወንድማማቻዊ ግንኙነት አላቸው። ይህ ግንኙነታቸው ከንጉሠ ነገሥት ዳግማዉ ቀዳማዊ ዐፄ ኃይለስላሴ እና ከመጀመሪያው የኬንያ ፕሬዝዳንት ጆሞ ኬንያታ ጀምሮ የነበረ ነው። ይህ ወንድማማችነታቸው በዓመታት ውስጥ የተገነባ ነው። የኬንያ እና የኢትዮጵያ መንግሥታት ይህንን እውቅና ይሰጣሉ ብየ አስባለሁ።
አሁን በምንናገርበት ጊዜም የቀድሞ የኬንያ ፕሬዝዳንት በነበሩበት ያለፉት አስር ዓመታት የስልጣን ዘመንም ይሁን  ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ወንድማማችነቱን አጠናክረዋል።
ፕሬዝዳንት ዑህሩ አዲስ አበባ በተጓዙ ጊዜ ሁሉ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ጋር እየተገናኙ የቀጣናውን ጉዳዮች በተመለከተ የአካባቢውን ችግሮች ለመፍታት የእኛ ሀሳብ ይህ ነው እያሉ ይወያያሉ። ምክንያቱም ኢትዮጵያ በቃጣናው ቁልፍ ሚና የምትጫወት ሀገር ናት። ስለዚህ ይህንን ግንኙነታቸውን ታሳቢ በማድረግ የታሰበው ይሳካል የሚል የእርግጠኝነት አምነት አለኝ።"

"ብዙ ምቾት የሚሰጥ ንግግር አይደለም ያደረገው።
[ ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ በበዓለ ሲመታቸው ላይ የቀድሞው የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት የኢትዮጵያን እና የቀጣናውን የሰላም ጉዳይ እንዲመለከቱ መሰየማቸውን በተመለከተ የተናገሩት]
ምክንያቱም ኢትዮጵያ ሉዓላዊ ሀገር ነች። ባለባት የውስጥ ችግር መፍትሔ ከውስጥ ይመነጫል እንጁ የሌላ ሀገር መሪ ያደራድራችሁ የሚለው ነገር በፍፁም አሳማኝ ጉዳይ አይደለም"

ሰለሞን ሙጬ

ታምራት ዲንሳ