1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ፍትሕ ፈላጊዎቹ የኮሬ ልጃገረዶች

ሐሙስ፣ ግንቦት 1 2016

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ኮሬ ዞን «ልጆቻችን ተጠልፈውብናል» ያሉ ቤተሰቦች ልጆቻቸውን ለማስመለሰም ሆነ ጠላፊዎቹን በሕግ ለመጠየቅ የአካባቢው አስተዳደር ተባባሪ ሊሆን አልቻለም አሉ ። «ከአንድ ወር በፊት በጠላፊዎች የተወሰደችው ልጄ አሁን ላይ የት እንዳለች እንኳን አላውቅም።»

https://p.dw.com/p/4ffu3
Sudan Äthiopien Frauen Symbolbild
ምስል Nariman El-Mofty/AP/picture alliance

«ልጆቻችን ተጠልፈውብናል»

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ኮሬ ዞን «ልጆቻችን ተጠልፈውብናል» ያሉ ቤተሰቦች ልጆቻቸውን ለማስመለሰም ሆነ ጠላፊዎቹን በሕግ ለመጠየቅ የአካባቢው አስተዳደር ተባባሪ ሊሆን አልቻለም አሉ ። «ከአንድ ወር በፊት በጠላፊዎች የተወሰደችው ልጄ አሁን ላይ የት እንዳለች እንኳን አላውቅም» ያሉ አንድ አባት ልጃቸውን ለማፈላለግ ከፀጥታ አባላት የውሎ አበል ክፍያ መጠየቃቸውን ነው ለዶቼ ቬለ የተናገሩት ። የተጠላፊ ቤተሰቦቸን አቤቱታ መቀበላቸውን ያረጋገጡት የኮሬ ዞን ፍትሕ መምሪያ ኃላፊ በበኩላቸው ጠላፊዎችን በህግ የመጠየቅ ሥራ ተፈጻሚ እንዲሆን ለወረዳ የፍትህ አካላት መመሪያ መተላለፉን አስረድተዋል ። ዘጋቢያችን ሸዋንግዛው ወጋየሁ ከሀዋሳ ተጨማሪ ዝርዝር አለው ።

ፍትሕ ፈላጊዎቹ የኮሬ ልጃገረዶች

በኮሬ ዞን የጎርካ ወረዳ ነዋሪ የሆኑ አባት የ15 ዓመት ሴት ልጃቸው ከወራት በፊት በጉዞ ላይ ሳለች መጠለፏን ይናገራሉ ፡፡ ልጃቸውን ለማስለቀቅና ጠላፊዎችን ለመያዝ ምስክሮችን አቅርበው የእስር መያዣ መጥሪያ ማውጣታቸውን ቅሬታ አቅራቢው አባት ገልፀዋል ፡፡ ነገር ግን ተጠርጣሪዎቹ ተሸሽገውበታል ወደ ተባለው ሥፍራ ለመንቀሳቀስ ከፀጥታ አባላት የተጠየቁትን የውሎ አበል ክፍያ መክፈል ባለመቻላቸው ጥረታቸው ሳይሳካ መቅረቱን ነው ለዶቼ ቬለ የተናገሩት  ፡፡ " ከአንድ ወር በፊት በጠላፊዎች የተወሰደችው ልጄ አሁን ላይ የት እንዳለች እንኳን አላውቅም " ያሉት እኝሁ  አባት ከፍትህ አካላት መፍትሄ እየጠበቁ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡

የ13 ዓመት ልጃቸው እንደተጠለፈችባችው የተናገሩት  ሌላኛው የዚሁ ወረዳ ነዋሪ በበኩላቸው " ልጄ ማንነታቸውን በማላውቃቸው ሰዎች መጠለፏን ሚያዚያ 5 ቀን 2016 ዓም ለወረዳው የፍትህ አካላት አመልክቻለሁ ፡፡ ነገር ግን እስከአሁን ምላሽ አላገኘሁም ፡፡ በዚህም ተስፋ በመቁረጥ  ከባለቤቴና ከቀሪ ልጆቼ ጋር እያለቀስኩ እገኛለሁ ብለዋል ፡፡

ሽምግልና እንደ ተግዳሮት 

በኮሬ ዞን የጎርካ ወረዳ የተጠላፊ ቤተሰቦች ባነሱት ቅሬታ ዙሪያ ዶቼ ቬለ ይመለከታቸዋል ያላቸውን የወረዳና የዞን የሥራ ሃላፊዎችን ጠይቋል ፡፡ በፀጥታ አካላት በኩል እነሱን የሚያጉላላ አካል ይኖራል ብዬ አላስብም ያሉት የጎርካ ወረዳ ሴቶችና ሕጻናት ጽህፈት ቤት ሃላፊ ወይዘሮ ባህሯ ብዙነህ " ነገር ግን ያንን ይበልጥ አጣርቼ  መረጃ እሰጣለሁ " ብለዋል ፡፡

ነዋሪው የሴት ልጆቹ ወጥቶ መግባት አሥግቶታል
ነዋሪው የሴት ልጆቹ ወጥቶ መግባት አሥግቶታልምስል Colourbox

የኮሬ ዞን ፍትህ መምሪያ በጠለፋና በአስገድዶ መድፈር ዙሪያ በሚቀርቡ ጉዳዮች ላይ ፍትህ ውሳኔ እየሰጠ እንደሚገኝ የተናገሩት የመምሪያው ሃላፊ አቶ ፍሬው ታሪኩ ጎርካን ጨምሮ በዞኑ የተለያዩ ወረዳዎች ውስጥ የጠለፋና የአስገድዶ መድፈር  በፈጸሙ ግለሰቦች ላይ የፍትህ ቅጣቶች መተላለፋቸውን  አሁንም በሂደት ላይ ያሉ ክሶች መኖራቸውን ተናግረዋል ፡፡ ዋናው ችግር ጉዳዩን በሽምግልና ለመያዝ የሚሞክሩ አካላት ጣልቃ እየገቡ ሂደቱን ለማደናቀፍ እንደሚሞክሩ የጠቀሱት አቶ ፍሬው " ለዚህ ሁሉም ቢተባበር ለውጥ ማምጣት እንችላለን የሚል እምነት አለኝ ፡፡ በተለይ  ህብረተሰቡ መረጃ በመስጠትና በመመስከር ተባባሪ መሆን አለበት " ብለዋል ፡፡

ተጠርጣሪዎችን ለመያዝ የውሎ አበል ክፍያ

በሴት ልጆቻችን ጠለፋ ፍትህ እንፈልጋለን በሚል ቅሬታቸውን ያቀረቡት ተበዳዮች ካነሷቸው ነጥቦች መካከል የፀጥታ አባላት ትብብር መጓደል አንዱ ነው ፡፡ በተለይም ተጠርጣሪዎችን ለመያዝ ከአባላቱ የውሎ አበል እንጠየቃለን በሚል ባቀረቡት ቅሬታ ላይ በዶቼ ቬለ የተጠየቁት የመምሪያ ሃላፊው " አቤቱታው እኛም ጋር ደርሷል " በማለት መልሰዋል ፡፡

መልከዓ ምድር በደቡብ ኢትዮጵያ
መልከዓ ምድር በደቡብ ኢትዮጵያምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

ተከሳሾችን ይዞ የማቅረብ ኃላፊነት የፖሊስ አባላት መሆኑን የጠቀሱት የዞኑ ፍትሕ መምሪያ ሃላፊው አቶ ፍሬው ታሪኩ " እንደዚህ አይነት አቤቱታ እየቀረበ ይገኛል ፡፡ አቤቱታው መሬት ላይ አለ ወይስ የለም የሚለውን ማጣራት አለብን ፡፡ በእኛ በኩል በወረዳው የሚገኙ የፍትህ አካላት ባላቸው የሦስትዮሽ መድረክ አማካኝነት ቅሬታውን አጣርተው ሪፖርት እንዲያደርጉ መመሪያ አውርደናል ፡፡ በዋናነት ግን ከጠለፋ ጋር ተያይዞ ለቀረቡ አቤቱታዎች አስቸኳይ ማጣራት ተካሂዶ ሪፖርት እንዲደረግ ለወረዳው የፀጥታና የፍትህ አካላት በሰርኩላር ደብዳቤ አሳውቀናል ፡፡ ውጤቱንም እየተከታተልን እንገኛለን "ብለዋል ፡፡፡

በደቡብ ኢትዮጵያ  ክልል ኮሬ ዞን ጎርካ ወረዳ ነዋሪዎች በወረዳው ሴት ልጆችን ትምህርት ቤት ለመላክ ጠለፋ ሥጋት እየሆነባቸው መምጣቱን በተደጋጋሚ መግለጻቸው ይታወቃል ፡፡ ጎርካን ጨምሮ በዞኑ ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ በ10 ፤ በ2015 ዓም ደግሞ በ14 ሴቶች ላይ የጠለፋ ድርጊት መፈጸሙን ከዞኑ የተገኘው መረጃ ያመለክታል ፡፡

ሸዋንግዛው ወጋየሁ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር