ጎርፍን ለመከላከል የሃረማያ ዩኒቨርሲቲ ጥረት
ሐሙስ፣ ነሐሴ 20 2013ለድሬደዋ ኅልውና ስጋት ከሆኑ ተፈጥሯዊ ክስተቶች ቀዳሚ የሆነው ጎርፍ መነሻውን ከምስራቅ ሀረርጌ ከፍተኛ ቦታዎች ያደረገ ስለመሆኑ ከሳይንሳዊ ጥናት መነሻ ባለፈ በተፈጥሮ ሀብት መመናመን ተራቁተው የሚታዩት ከፍታ ቦታዎች ምስክር ለመሆናቸው አንዱ ማሳያ የደንገጎ ተራራ ነው። ሀረማያ ዩኒቨርሲቲ በአንድ በኩል የጎርፍ ስጋትን የሚቀንስ በሌላ መልኩ በደንገጎ አካባቢ ላለው ከሁለት ሺህ በላይ አባወራ ደግሞ ወደ ምርታማነት የሚያሸጋግር ፕሮጀክት እየተገበርኩ ነው ብሏል።
ለድሬደዋ የጎርፍ አደጋ መንስዔ የሆኑት የምስራቅ ሀረርጌ ከፍተኛ ቦታዎች መራቆት መሆኑን የተናገሩት በሀረማያ ዩኒቨርሲቲ የደንገጎ ፕሮጀክት አስተባባሪ ዶ/ር ተሰማ ቶራ ከተለያዩ አካላት ጋር በመሆን ለችግሩ መፍትሄ ከሚሆኑ ተግባራት ትልቁን ስራ በመስራት መሆናቸውን ተናግረዋል።
በሀረማያ ዩኒቨርሲቲ የደንገጎ ተራራን መሰረት አድርጎ እየተሰራ ያለው የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ በአቅራቢያ ላሉት የሀረማያ እና አዴሌ ሐይቆች ማገገም እንዲሁም ለአካባቢው ወጣቶች የስራ ዕድል በመፍጠር የበኩሉ ፋይዳ እንዳለው የዩኒቨርሲቲው ባለሞያ የሆኑት ዶ/ር ተሰማ ገልፀዋል።
ሀረማያ ዩኒቨርሲቲ ሞዴል በማድረግ እየተገበረው ስለመሆኑ በሚገልጸው በዚህ ፕሮጀክት ህብረተሰቡን በማሳተፍ የተለያዩ ስራዎች መሰራታቸውን የሚናገሩት በሀረማያ ወረዳ የተፈጥሮ ሀብት ልማት ቡድን መሪ አቶ ዓለማየሁ እሸቴ ፕሮጀክቱ ለደንገጎ አካባቢ አርሶ አደሩ ጠቀሜታ ያመጣል ብለዋል።
መሳይ ተክሉ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ሸዋዬ ለገሰ