ዶክተር ደሳለኝ ጫኔ ታሰሩ፣ ታሳሪ የምክር ቤት አባላት ከአዋሽ አርባ ወደ አዲስ አበባ ተወሰዱ
ሐሙስ፣ ጥር 23 2016የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ( አብን ) የመጀመርያው ሊቀመንበር እና በኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አበል የሆኑት ዶክተር ደሳለኝ ጫኔ ትናንት ምሽት በፀጥታ አካላት ከቤታቸው ተይዘው መታሠራቸው ተገለፀ።
የዶክተር ደሳለኝ ቤተሰብ መሆናቸውን የገለፁ ሰው ለዶቼ ቬለ እንዳሉት የምክር ቤት አባሉ ትናንት ምሽት 3 ሰዓት ገደማ አዲስ አበባ ውስጥ ከመኖሪያ ቤታቸው አምስት በሚደርሱ የፀጥታ አካላት "በሕግ ትፈለጋለህ" በሚል ተይዘው መወሰዳቸውን አረጋግጠዋል።
በሌላ በኩል አዋሽ አርባ በተባለው ሥፍራ ለወራት በእሥር ላይ የቆዩት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፣ የአማራ ክልል እና የአዲስ አበባ ምክር ቤት አባልት እና አንፍ ጋዜጠኛ ወደ አዲስ አበባ መወሰዳቸውን ጠበቃቸው ለዶቼ ቬለ አረጋግጠዋል።
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ከተመሠረተ ጀምሮ በፈቃዳቸው ኃላፊነታቸውን እስካስረከቡበት ወቅት ድረስ የፓርቲው የመጀመርያው ሊቀ መንበር ሆነው ያገለገሉት ዶክተር ደሳለኝ ጫኔ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከተወከሉ ጥቂት የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አባላት መካከል አንደኛው ናቸው።
ዶክተር ደሳለኝ ጫኔ ባለፉት ጥቂት ወራት ይደረጉ በነበሩ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤዎች ላይ ሲሳተፉ አልታዩም። በፓርላማው ውስጥ አነጋጋሪ ሀሳቦችን ከሚያነሱ የተፎካካሪ ፓርቲ አባላት መካከል አንዱ የሆኑት እኒሁ የምክር ቤት አባል ዛሬ ጥር 23 ቀን፣ 2016 ዓ.ም ቤታቸው መበርበሩን እና በፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ ታሥረው እንደሚገኙ ቤተሰባቸው መሆናቸውን የገለፁ ተዋበ የተባሉ ሰው ነግረውናል።
እሥረኞችን ጠበቃቸው ማየት አልቻሉም
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ ክርስቲያን ታደለ፣ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ ምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ ዮሐንስ ቧያለው፣ የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አባል የሆኑት ዶ/ር ካሳ ተሻገር እና ጋዜጠኛ በቃሉ አላምረው ለወራት ታስረው ከቆዩበት አዋሽ አርባ እሑድ እለት ወደ አዲስ አበባ መወሰዳቸውን ጠበቃቸው ሰለሞን ገዛኸኝ ተናግረዋል።
ጠበቃው ግለሰቦቹ ወደታሠሩበት የፌዴራል ወንጀል ምርመራ ቢሮ ለመጠየቅ ቢሄዱም እንዳልተፈቀደላቸው እና በአካል ሊያገኟቸው እንዳልቻሉ ገልፀዋል።
በአዋሽ አርባ የቆዩት ታሳሪዎች ስለመጎሳቆላቸው ቤተሰቦቻቸው ተናግረዋል
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን እነዚህን ተጠርጣሪዎች ጨምሮ 53 ሰዎች በአማራ ክልል በተደነገገው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እዝ አዋሽ አርባ ውስጥ ባለ የሀገር መከላከያ ሚኒስቴር የምዕራብ ዕዝ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ካምፕ ውስጥ ተይዘው እንደሚገኙ ከዚህ በፊት አስታውቆ ነበር።
ለደህንነታቸው ሲሉ ማንነታቸውን ከመግለጽ የተቆጠቡ የታሳሪ ቤተሰቦች የምክር ቤት አባላቱ እሁድ እለት ከቀትር በኋላ አዲስ አበባ እንደገቡ ፣ በማግስቱ ከቤተሰብ ጋር በስልክ እንዲደዋወሉ መደረጉን ገልፀዋል።
ሁኔታቸውን ሲገልፁ ተጎሳቁለው እና ጥሩ ባልሆነ ሁኔታ ላይ መሆናቸውን አብራርተዋል። ይህንን ጉዳይ ጠበቃውም ከቤተሰቦቻቸው መስማታቸውን ነግረውናል።
ከታላቁ ሩጫ ማግስት የተያዙ ወጣቶች ስለመለቀቃቸው
በተያያዘ ዜና አዲስ አበባ ውስጥ ሁከት እና ብጥብጥ ለማስነሳት መሞከራቸው ተጠቅሶ ታስረው የነበሩ የታላቁ ሩጫ ተሳታፊዎች ከእሥር መለቀቃቸውን ጠበቃ ሰለሞን ገዛኸኝ አስታውቀዋል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጆ በሚቆይበት ጊዜ ሰዎችን ከማሰቃየት ተግባር የመቆጠብ፣ በሕይወት የመኖር መብትን የማስከበር እና በገለልተኛ አካል የመዳኘት መብትን የመሳሰሉ መብቶች መከበር እንዳለባቸው እና በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የሚፈቀዱ እርምጃዎች ቢኖሩ እንኳን የሕጋዊነት፣ የአስፈላጊነት እና የተመጣጣኝነት መርህን ማክበር እንደሚገባ ኢሰመኮ ከዚህ በፊት ማስታወቁ ይታወሳል። በአማራ ክልል ለስድስት ወራት የተደነገገውን የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ ተከትሎ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የታሰሩ ሲሆን ዐዋጁ ከሳምንት በኋላ ስድስት ወራት ይሞላዋል።
ሰለሞን ሙጬ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
አዜብ ታደሰ