1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

እየተባባሰ የመጣው የሰብአዊ መብት ጥሰት በኢትዮጵያ

እሑድ፣ መስከረም 27 2016

በሀገሪቱ ያለተጠያቂነት እያደር እያሽቆለቆለ መሄዱ የሚገለጸው የሰብአዊ መብቶች አያያዝ አሳሳቢ ደረጃ መድረሱን ሁኔታውን የሚከታተሉ የመብት ተቆርቋሪዎች በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን መድረክም አቅርበዋል።

https://p.dw.com/p/4XDnw
ፎቶ ከማኅደር፤ የታሠሩ ሰዎች ተምሳሌት
ኢትዮጵያ ውስጥ የሰብአዊ መብት ጥሰት እየባሰበት መምጣቱን በቅርቡ ይፋ የወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ። ፎቶ ከማኅደር፤ የታሠሩ ሰዎች ተምሳሌትምስል Kim Ludbrook/dpa/picture alliance

ያለተጠያቂነት እየተባባሰ የመጣው የሰብአዊ መብት ጥሰት በኢትዮጵያ

የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ኢትዮጵያ ውስጥ እየተባባሰ መምጣቱን የመብት ተሟጋች ተቋማት ደጋግመው እያሳሰቡ ነው። በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ለሚፈጸሙ ጥቃቶች እና የመብት ጥሰቶች ተጠያቂነት አለመስፈኑ፤ ሰብአዊ መብቶችን ለማስከበር ቁርጠኝነት አለመታየቱ ችግሩ ተባብሶ ለመቀጠሉ በምክንያትነት ይጠቀሳሉ። በሰሜን ኢትዮጵያ በተደረገው ጦርነት ሂደት በሀገር ውስጥ እና ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተቋማት የምርመራ ውጤት መፈጸማቸው ለተገለጸው ዘርፈ ብዙ የመብት ጥሰቶች እስካሁን ተጠያቂነት አለመስፈኑ፤ በአማራ ክልል በቀጠለው ውጊያ እና ግጭትም ተመሳሳይ ችግር ለመኖሩ አሳሳቢ መሆኑም እየተገለጸ ነው። በአማራ ክልል የተደነገገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን ተከትሎም ከክልሉ ውጪ እየተተገበረ በርካቶች መታሰራቸውን የተለያዩ የሰብአዊ መብትተሟጋች ተቋማትን በተደጋጋሚ አሳውቀዋል። የወጡት ዘገባዎችም በሚወሰደው መጠነ ሰፊ እርምጃ በአዲስ አበባ እና በአዳማ/ናዝሬት/ን በመሳሰሉ ከተሞች የጅምላ እስር መፈጸሙን፣ ያለ ክስ በርካቶች መታሰራቸውን፤ ታሳሪዎቹን ስለመሰወር፣ ከሚኖሩበት አካባቢም አርቆ ማሰር፣ ታሳሪዎቹ የህክምና አገልግሎት እንዳያገኙ ማድረግ እና የመሳሰሉት የመብት ጥሰቶች መፈጸማቸውን ያሳያሉ። ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ የሕግና የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሊደነገግ የሚችለው አሳሳቢ ብሔራዊ ስጋት ሲከሰት እና በመሳሰሉ ወሳኝ ወቅቶች ለአጭር ጊዜ መሆኑን በማመልከት ኢትዮጵያ ውስጥ መደጋገሙን ያመለክታሉ። «እርግጥ ነው የአስቸኳይ ጊዜ ድንጋጌ ወቅት ተጠርጣሪዎችን ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ የመያዝ አጋጣሚዎች እንዲከናወኑ ሊያደርግ ይችላል» የሚሉት የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ማዕከል ዋና ዳይሬክተር አቶ ያሬድ ኃይለ ማርያም፤ የሚታየው ግን አዋጁን ከሚገባው በላይ በመለጠጥ ለፖለቲካ አላማ የማዋል ነገር እንደሆነ ያመለክታሉ። ዶቼ ቬለ «በኢትዮጵያ ያለተጠያቂነት እየተባባሰ ስለመጣው የሰብአዊ መብት ጥሰት» በተመለከተ የሕግ እና የሰብያዊ መብቶች ባለሙያዎችን በመጋበዝ ውይይት አካሂዷል።

ፎቶ ከማኅደር፤ የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን አርማ
የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽንን ጨምሮ የተለያዩ የመብት ተሟጋች ድርጅቶች በተደጋጋሚ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በየደረጃው ስለተፈጸሙ የመብት ጥሰቶች ዘገባዎች እያቀረቡ ነው። ፎቶ ከማኅደር፤ የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን አርማምስል Ethiopian Human Rights Commission

የውይይቱ ተሳታፊዎች አቶ አምሀ መኮንን የሕግ ባለሙያ እና የሰብያዊ መብቶች ባለሙያ እንዲሁም የሕግ ባለሙያዎች ለሰብአዊ መብቶች የተባለው ሀገር በቀል ሲቪክ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ፤ አቶ ተስፋዬ ገመቹ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ ምክትል ዋና ዳይሬክተር፤ እንዲሁም አቶ ያሬድ ኃይለ ማርያም የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ናቸው።  በዚህ ውይይት የመንግሥትን ሃሳብ እንዲያካፍሉ ከመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ባለሥልጣናት እንዲሁም ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በኢሜይል ጠይቀን ምላሽ እንዳላገኘን ለመግለጽ እንወዳለን።

ሙሉውን ውይይት ለማድመጥ የድምጽ ማዕቀፉን ይጫኑ።

ሸዋዬ ለገሠ