የፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት አፈፃፀምና ትችቱ
ሰኞ፣ ጥር 13 2016የፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት የእስካሁኑ አፈፃፀም የዘገየ ነው ሲሉ በትግራይ የሚገኙ ፖለቲከኞች፣ ሲቪል ማሕበራት እና ሌሎች አካላት ወቀሱ። ከሰላም ስምምነቱ አንድ ዓመት በኃላም የጦርነቱ ተፈናቃዮች ወደቦታቸው አልተመለሱም፣ በሕገመንግስቱ መሰረት የትግራይ አስተዳደር ግዛት ወደቀድሞ ሁኔታው አልተመለሰም የሚሉት እነዚህ ተቺዎች አደራዳሪ አካላት የውሉ ተፈፃሚነት እየተከታተሉ አይደለም ብለዋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ የሰላም ስምምነቱ አፈፃፀም ለመግምገም ፥ አደራዳሪው የአፍሪካ ሕብረት ልኡካን ወደ መቐለ እንደሚመጡ የአፍሪካ ሕብረት ፀጥታ ምክርቤት አስታውቋል።«የሰላም ስምምነቱ በምልዓት ገቢራዊ አልሆነም »ህወሓት
በጦርነቱ ጅማሮ ከምዕራብ ትግራይ ዞን የተፈናቀሉት እና አሁን ላይ በዓብይ ዓዲ የተፈናቃዮች መጠልያ የሚኖሩት አቶ ብርሃነ ታፈረ፥ ጥቅምት ወር 2015 ዓመተምህረት በኢትዮጵያ መንግስት እና ህወሓት መካከል ጦርነቱ ያስቆመ የሰላም ስምምነት ሲፈረም በደስታ እንደተቀበሉት ያስታውሳሉ። ይሁንና ከተፈናቃይነት እና እርዳታ ጠባቂነት ሊገላግላቸው፣ ወደመደበኛ ሕይወት ሊመልሳቸው የጠበቁት የፕሪቶርያ የሰላም ስምምነት እንዳሰቡት አልሆነም። ከጦርነቱ መቆም 14 ወራት በኃላም ቢሆን እርዳታ ጠባቂ ሆነው ከስድስት የቤተሰባቸው አባላት ጋር በተፈናቃይ መጠልያ ኑሮአቸው ይገፋሉ። አቶ ብርሃነ የውሉ ፈራሚዎች ስምምነቱ እየተገበሩ አይደለም በማለት የሚተቹ ሲሆን ከዚህ በዘለለም አደራዳሪ የነበሩ አካላት ለምን የውሉ ትግበራ በቅርበት አይከታተሉም በማለት ይወቅሳሉ።
ሌላው የሰላም ስምምነቱ ተፈራራሚዎች የጠበንጃ ድምፅ ከማስቀረት ባለፈ የሚጠበቁ በርካታ ተግባራት አልከወኑም በማለት የሚወቅሱ ደግሞ በትግራይ የሚንቀሳቀሱ ሲቪክ ማሕበራት ሕብረት ነው።አንድ ዓመት የሞላው ግጭት የማቆም ስምምነት የትግራይ ሲቪክ ማሕበራት ሕብረት እንደሚለው ከሰላም ስምምነቱ በኃላ የሚጠበቁ ስራዎች እስካሁን አልተተገበሩም። የሕብረቱ ስራ አስኪያጅ አቶ ያሬድ በርሃ "የፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት ከተፈረመ በኃላ የትግራይ ህዝብ ከጦርነት ወጥቶ፣ የነበሩት ሰው ሰራሽ እና ተፈጥሮአዊ ችግሮች ተቀርፈው፣ በአጭር ግዜ ወደቀድሞ ኑሮው ተመልሶ ሊያገግም ተስፋ አድርገን የነበረ ቢሆንም ይህ አልሆነም። ከስምምነቱ በኃላ ቢሆን የትግራይ ህዝብ በችግር ላይ ችግር እየተደራረበበት፣ ለተፈናቃዮችና ስደተኞች መፍትሔ ሳይሰጥ፣ ከባባድ ሰው ሰራሽና ተፈጥሮአዊ ችግሮች እያስተናገደ ይገኛል" ይላሉ።
የሰላም ስምምነቱ ከነግድፈቶይ ቢሆን ተቀብለነዋል የሚለው የትግራይ ነፃነት ፓርቲ በበኩሉ ይሁንና የውሉ ትልልቅ ጉዳዮች አሁንም ድረስ አለመፈፀማቸውን ተከትሎ የትግራይ ህዝብ መከራ ቀጥሏል በማለት ይገልፃል። የፓርቲው ህዝብ ግንኙነት ሐላፊ አቶ ገብረስላሴ ካሕሳይ "ውሉ ታጣቂዎች ከትግራይ ግዛት መውጣት አለባቸው ይላል። ሁለተኛ ደግሞ በሕገመንግስቱ መሰረት የትግራይ የግዛት አንድነት እንዲረጋገጥ ይጠበቅ ነበር። ከዚህ በተጨማሪ በጦርነቱ ምክንያት የተፈናቀሉ ወደ ቤታቸው ሊመለሱ ይገባ ነበር። ይሁንና አሁንም ታጣቂዎች በትግራይ አሉ፣ በሕጉ መሰረት የትግራይ የግዛት አንድነት አልተከበረም። በዚህም ምክንያት ተፈናቃዮች ወደቀዬአቸው ሊመለሱ አልቻሉም" ይላሉ።
ዉሉ እንዲፈረም ጥረት ያደረጉ አካላት አፈፃፀሙ እየተከታተሉ እንዳይደለ በማለት ቃል አቀባዩ ጨምረው ይገልፃሉ። "ውሉ የፈረሙ አካላት ውሉ የሚተገብሩ ቢሆን በተግባር ባየነው ነበር። እነሱ ብቻ ሳይሆን አደራዳሪዎቹም ጭምር በትክክል ሐላፊነታቸው እየተወጡ አይደለም። የኢትዮጵያ ዉጪ ጉዳይ ሚንስቴር ሥለ ግጭት የማቆም ስምምነቱ አንደኛ ዓመትየውሉ ተፈፃሚነት ተፈናቃዮች በመመለስ፣ ታጣቂዎች በማስወጣት እና በመሳሰሉት ነው የሚለካው። ባለው ሁኔታ ግን ምንም እየተሰራ እንዳልሆነ ነው የሚገባኝ" በማለት አቶ ገብረስላሴ አክለዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የአፍሪካ ሕብረት የሰላምና የፀጥታ ምክር ቤት የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት አፈጻጸም ለመገምገም ከጥር 18 ቀን 2016 ዓመተምህረት ጀምሮ ለሁለት ቀናት በትግራይ ጉብኝት እንደሚያደርግ ተገልጿል። የአፍሪካ ሕብረት የሰላምና የፀጥታ ምክር ቤት በትግራይ በሚያካሂደው ጉብኝት ከክልሉ ግዝያዊ አስተዳደር፣ ከሲቪክ ማሕበራት አመራሮች እና በጦርነቱ ከተፈናሉት ጋር በመቐለ እንደሚገናኝ አስታውቋል።ከዚህ በተጨማሪም የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት አፈፃፀምንና ሌሎች አጀንዳዎች ይገመግማል ተብሎ እንደሚጠበቅ፥ አማኒ አፍሪካ የተባለ የፀጥታ ምክር ቤቱ ተባባሪ ገለልተኛ የምርምር ተቋም ባወጣው መረጃ አስታውቋል።
ሚሊዮን ኃይለሥላሴ
ኂሩት መለሰ